የመንግሥት የቤት ሥራዎች

0
131

ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ የክልል እና የፌደራል መንግሥታት ምሥረታ ተካሂዷል፡፡ ይህን አስመልክተውም ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሰላምን  ማስፈን፣ የኑሮ ውድነትን መግታት፣ የመሠረተ ልማት ፍላጎት እና መሰል ማሕበራዊ አገልግሎቶችን ማሟላት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት መንግሥት በትኩረት ሊያከናውናቸው እንደሚገባ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጠይቀዋል፡፡

በተለይ የሰላም መስፈን የቅድሚያ ትኩረት እንዲሆን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ይህ ሲሆን ደግሞ ቤተሰብን መጠየቅ እንደሚቻል፣ አምራቹ እና ነጋዴው ምርቱን እና ሸቀጡን  እንደፈለገ በማንቀሳቀስ  የኑሮ ውድነትን ለመግታት ድርሻው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 7ኛ ዙር 1ኛ ዓመት መሥራችና 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን መስከረም 21 እና 22 ቀን 2019 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ በማካሄድ አዲሱን መንግሥት አዋቅሯል፡፡ በዚሁ ጉባኤ ምክር ቤቱ አቶ አረጋ ከበደን በድጋሚ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል፡፡ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ የአለፉትን አምስት ዓመታት የሥራ ክንውኖች እና የቀጣይ አምስት ዓመታት  የትኩረት  አቅጣጫዎችን አሳውቀዋል፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በይፋ ካነሷቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ቀዳሚው ነው፡፡ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን፣ የፖለቲካ መረጋጋት እንዲመጣ እንዲሁም የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የሕግ ማስከበርና የፖለቲካ ሥራዎች ውጤታማ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በክልሉ ያሉ ሁሉንም አካባቢዎች ለልማት ምቹ ለማድረግ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባ  ርእሰ  መስተዳድሩ      አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም በተለይ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከምሁራን፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ልሂቃን፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶች እንዲሁም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር ሀገር በቀል የሰላም ግንባታ እሴቶችን በመላበስ ሰላም እንዲሰፍን ቀደም ብሎ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡

ሰላም በምኞት ብቻ ሳይሆን በቁርጠኝነት እና በጎ ሐሳብ በአላቸው አካላት የሚገነባ መሆኑን የአነሱት ርእሰ መስተዳድሩ መጪዎቹ አምስት ዓመታት ግጭት፣ የሐሳብ እና የጥቅም ልዩነቶች ማክተሚያ እና የአዲስ ምዕራፍ መክፈቻ እንዲሆኑ አስገንዝበዋል፡፡ ለተግባራዊነቱም መንግሥት እና ሌሎች አጋር ኀይሎች፣ ወጣቶችና መላው የክልሉ ሕዝብ በጋራ መቆም እንዳአለባቸው አሳስበዋል፡፡

የዜጎችን ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የፀጥታ እና የፍትሕ አካላት እንዲሁም ተቋማት ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዱ፣ ሕግን መሠረት አድርገው ሕዝቡን የሚያገለግሉ እና ለሕግ የቆሙ ሙያዊ ተቋማት በመሆን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በትኩረት እንደሚሠራ ተጠቁሟል፡፡

ሕዝብን ማክበር የሚቻለው የሕዝብ እምነት ባላቸው የፍትሕ እና የጸጥታ አካላት መሆኑን የገለጹት ርእሰመስተዳድሩ፤ አሁናዊና የወደፊት ፍላጎት ለመለየት እና የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ አሠራሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል በቀጣይ አምስት ዓመታት በክልሉ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታትና ለማስተናገድ የፖለቲካ ምሕዳሩን የሐሳብ ማዕከል ማድረግ፣ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ያሏቸው ኀይሎች በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚሳተፉበት፣ የተፎካካሪዎች እና የሲቪክ ማኅበራትን ሚና የሚያስከብር አሠራር በመዘርጋት የመንግሥትን ተቀባይነት ለማሳደግ በትኩረት የሚሠራበት ጊዜ እንደሚሆንም ተመላክቷል፡፡ በክልሉና በሌሎች ክልሎች መካከል ያለውን አብሮ የመኖርና የመልማት ባሕል ለማጠናከር የጥላቻ ንግግርና የሐሰት መረጃዎችን የሚመክት የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ በመንደፍ የጋራ ጥቅሞችን እና ትስስሮችን መሠረት በማድረግ የጋራ ገዥ ትርክት ለመገንባት ጥረት እንደሚደረግም ነው በጉባኤው የተጠቆመው፡፡

ሌላው በቀጣይ ሊስተካከል የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ የሙስና ችግር መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ሙስና ዋነኛ የመልካም አስተዳደር ዕንቅፋት በመሆኑ ፍትሐዊነትን እና እኩልነትን የሚያጓድል እንዲሁም የሕዝቡን የልማት ዕድገት ወደ ኋላ የሚመልስ የለውጥ ጠንቅ መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል። ችግሩን በመገንዘብም በቁርጠኝነት መጋፈጥ እና መፍትሔ ማስቀመጥ ወቅቱ የሚጠብቀው ኃላፊነት መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል። በተለይ ከመሬት አስተዳደር፣ ከመንግሥት ግዥና አፈጻጸም እንዲሁም ከፕሮጀክት አሠራሮች ጋር የተያያዙ የሙስና ችግሮችን መፍታት ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት ናቸው።

ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፉት መልዕክት “በሀገራችሁ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ባይታወር ተደርጋችሁ የምትቆጠሩበት ዘመን አብቅቷል” ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራቸውና በክልላቸው በንቃት እንዲሳተፉ በመደረጉ የክልሉ መንግሥት ደስተኛ መሆኑን ገልጸው ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሎ ፍሬ እንዲያፈራም ያላቸውን ሐሳብ ለክልሉና ለሀገረ መንግሥቱ ልማት መረጋገጥ እና ለሰላም መስፈን እንዲያውሉት አሳስበዋል፡፡

አቶ አረጋ በተጨማሪም በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኀይሎች መልዕክት አስተላልፈዋል፤ ላለፉት ሦስት ዓመታት በተደረገ ትግል አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ አለመኖሩን ጠቅሰው በውስጣቸው ቅሬታ ቢኖርም መፍትሔው በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ማድረግ ብቻ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በሀገራችን ታሪክ ውስጥ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የማይተካ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት ርእሰ መስተዳድሩ ይህንን ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። ምሁራንም ሀገር በስሜት ሳይሆን በዕውቀት፣ በምክንያት እና በሳይንሳዊ መንገድ መመራት እንደአለባት በመገንዘብ መፍትሔ አመንጪዎች በመሆናቸው ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል። በተለይ በክልሉ ሰላም እና ዕድገት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ነጻ እና ሚዛናዊ ሆነው በጥናት ላይ የተመሠረተ የመፍትሔ   ሐሳብ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሴቶች የቤተሰብ መሠረት እና ለሀገር ግንባታ ቁልፍ የማኅበረሰብ ክፍል ናቸው፤ በግጭት እና በሰላም እጦት ወቅት ደግሞ ቀጥተኛ እና ዋና  ተጠቂዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ቁልፍ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡”የሀገር ፍቅር የሚጀምረው በእናት እቅፍ ነው” የሚለውን አባባል በማስታወስ ሴቶች በቤተሰብ ደረጃ የሰላም እና የፍቅር ድባብ እንዲፈጥሩ፣ ልጆቻቸውን ከጥላቻ እና ግጭት አርቀው በበጎ ሥነ ምግባር ቀርጸው እንዲያሳድጉ አቶ አረጋ ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቶችም በክልሉና በሀገሪቱ ሁለገብ የልማት ተሳትፎ በማድረግ ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውንና ሀገራቸውን ለመጥቀም በንቃት እንዲሳተፉ እና ለሀገር የበላይነትና ለሰላም ግንባታ ዘብ እንዲቆሙ ተጠይቋል፡፡

 

መረጃ

አዲስ የመንግሥት ምሥረታ ምን ማለት ነው?

ሕዝብ በምርጫ የሰጠውን ውክልና መነሻ በማድረግ፣ ሀገሪቱን ለሚቀጥለው የሥራ ዘመን (በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት) የሚመራ አዲስ አስፈፃሚ አካል፣ ጠቅላይ ሚኒሥትር እና ሚኒሥትሮች በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የሚዋቀሩበት ሂደት ነው።

የመንግሥት አወቃቀር

  • የሥልጣን ምንጭ:- የመንግሥት ሥልጣን በቀጥታ ከሕዝብ ድምጽ እና ፍላጎት ይመነጫል።
  • የሕገ-መንግሥት ሂደት:- በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባኤ ይካሄዳል።
  • ዓላማው:- የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች ማስቀጠል፣ ሰላምን ማረጋገጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ እና የፍትሕ ተቋማትን ማጠናከር ነው።

 

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here