የቤተሰብ ዕቅድ፡- ከግል ጤና እስከ ሀገራዊ ዕድገት

0
102

ወ/ሮ ዓለሚቱ አስማረ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ትዳር መሥርተው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የእነወ/ሮ ዓለሚቱ ወርሃዊ ገቢያቸው ተጨማሪ ልጅ ለማሳደግ በቂ አደለም፡፡ እናም የ12 ዓመቱን ሉፕ የተሰኘ የወሊድ መቆጣጠሪያ ለመጠቀም ስምምነት በማድረግ አገልግሎቱን ለማግኘት ባሕር ዳር በሚገኘው ቤተሰብ መምሪያ ተገኝተዋል፡፡

ሌላዋ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎቱን ለማግኘት ተራዋን ስትጥብቅ ያገኘናት ደግሞ ወ/ሮ ትዕግስት መንግሥቱ ናት፡፡ ወ/ሮ ትዕግስት የመጀመሪያ ልጇን ከወለደች አንድ ዓመት ሆኗታል፡፡ ታዲያ አካሏ ሳይጠነክር እና ልጇ ማግኘት ያለበትን ተገቢውን እንክብካቤ ሳያገኝ ሌላ ልጅ ለአለመውለድ  በክንድ የሚቀበረውን ኢምፕላንት ለማስቀበር ነበር የተገኘችው፡፡

ሁለቱም የነገሩን የሚጠቀሙበትን የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴ ሲመርጡ ለጤናቸው ተስማሚ መሆኑን ከጤና ባለሙያ ጋር በመነጋገር ነው፡፡

ታዲያ የቤተሰብ ዕቅድ ምንድን ነው? መቼ ተጀመረ? ጥቅሙ እና የጎንዮሽ ጉዳት ምንድን ነው? የሚለውን መረጃ ለማግኘት በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማሕበር የባሕር ዳር የሥነ ተዋልዶ ጤና ክሊኒክ ማናጀር አቶ ፍርዱ መኩሪያው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ ማናጀሩ እንዳስረዱት በሀገራችን የሕዝብ ቁጥር እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የቤተሰብ ዕቅድ (Family Planning) አገልግሎት ከጤና ጉዳይነቱ ባሻገር ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ እየሆነ መጥቷል፡፡

የቤተሰብ ዕቅድ ማለት አንድ ቤተሰብ ስለ ልጆች ብዛት፣ መቼ ልጅ መውለድ እንዳለበት እና በልጆች መካከል የሚኖረውን የጊዜ ርቀት በመወሰን ሕይወቱን በሚመች መልኩ ለመምራት የሚያስችል ሳይንሳዊ መንገድ መሆኑንም አቶ ፍርዱ ገልጸዋል፡፡

ታሪካዊ አመጣጥ

በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገትና በከፍተኛ የልደት መጠን ምክንያት የተደቀነውን ስጋት ለመቀነስ እ.አ.አ በ1960ዎቹ ዘመናዊ የቤተሰብ ዕቅድ በሰፊው መተግበር መጀመሩን አቶ ፍርዱ አስገንዝበዋል፡፡ እ.አ.አ በ1960 የመጀመሪያው የእርግዝና መከላከያ ክኒን በሥራ ላይ ሲውል በ1967 ደግሞ የዓለም አቀፍ የሕዝብ ጉዳይ ፈንድ (UNFPA) ተመሠረተ፡፡ እ.አ.አ በ1968 በኢራን ዋና ከተማ በቴህራን በተደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤ የቤተሰብ ዕቅድ ሰብዓዊ መብት ኾኖ በመታወጁ ሰዎች የልጆቻቸውን ቁጥርና  የሚወልዱበትን ጊዜ በነጻነት የመወሰን መብታቸው ተረጋገጠ፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እ.አ.አ በ1966 በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማሕበር (FGAE) አማካኝነት በአዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በአንድ ክፍልና በአንድ ነርስ ተጀመረ፡፡ እ.አ.አ በ1980ዎቹ የጤና ሚኒሥቴር አገልግሎቱን በሰፊው ማዳረስ የጀመረ ሲሆን በ1993 (እ.አ.አ) የወጣው የኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ አገልግሎቱ በሀገር  ደረጃ  እንዲስፋፋ ትልቅ መሠረት ጥሏል፡፡

ባለብዙ ዘርፍ ጥቅሞቹ

የቤተሰብ ዕቅድ ለግለሰብ፣ ለቤተሰብ እና ለሀገር አቀፍ እድገት የሚሰጣቸው ጥቅሞች በርካታ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ፍርዱ ከጥቅሞቹ መካከልም ፡-

ጤናማ  ሕብረተሰብ  ለመገንባት፡- እናቶች ከወሊድ በኋላ አካላቸው ወደ ነበረበት ለመመለስ  ቢያንስ ሁለት ዓመት ያስፈልጋቸዋል፡፡

የቤተሰብ ዕቅድ በእርግዝና መካከል በቂ ጊዜ እንዲኖር በማድረግ የእናቶችን እና የሕፃናትን ጤና ያሻሽላል፤ ያልታቀደ እርግዝናንም ይቀንሳል፡፡

ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ እፎይታ፡- በቂ ዝግጅት አድርጎ እና አቅዶ  መውለድ የቤተሰብን የምግብ፣ የጤና እና የትምህርት ወጪ በዐቅም ለመሸፈን ይረዳል፡፡ ሕፃናት በቂ እንክብካቤ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የሴቶችን የትምህርት እና የሥራ ተሳትፎ በማሳደግ የቤተሰብ ደኅንነትን ያረጋግጣል፡፡

ሀገራዊ እድገት እና ዘላቂ ልማት፡- በሀብት እና በሕዝብ ቁጥር መካከል ተመጣጣኝነት እንዲኖር በማድረግ በመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ (እንደ ጤና እና ትምህርት) ላይ የሚፈጠረውን ጫና ይቀንሳል፡፡

የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴዎች እና  የጎንዮሽ ጉዳቶች፦

እንደ ባሕር ዳር ሥነ-ተዋልዶ ጤና ክሊኒክ ማናጀር አቶ ፍርዱ መኩሪያው ማብራሪያ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴዎች ጥቅማቸው እንዳለ ኾኖ የጎንዮሽ ጉዳቶቹም ከሰው ሰው ሊለያይ ይችላል፡፡  ነገር ግን የጎንዮሽ ጉዳቶች ሲያጋጥሙ ከጤና ባለሙያ ጋር በመመካከር ማስተካከያ መድኃኒት በመውሰድ ወይም ወደ ሌላ የቤተሰብ ዕቅድ ዜዴ በመቀየር ማስተካከል ይቻላል፡፡ የሚሰጡትን ጥቅም እና ያላቸውን የጎንዮሽ ጉዳትም በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡

ኮንዶም (Condom):- እርግዝናን፣ ኤች አይቪ/ኤድስን እና ሌሎች የአባላዘር በሽታዎችን ይከላከላል፡፡ ኮንዶም ሆርሞን የለውም፤ ኾኖም ሊቀደድ ወይም ሊንሸራተት ስለሚችል በዚህ ጊዜ እርግዝናንም ኾነ በሽታዎችን ሊከላከል አይችልም፡፡ በአንዳንድ ሰዎች ላይም የላቴክስ አለርጂ ሊያስከትል ይችላል፤  መከላከያው ውጤታማ እንዲሆንም የጥንዶችን የጋራ ትብብርን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም  በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡

ክኒን (Pills):- የሚዋጥ እንክብል ሲሆን ሌላው የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ነው፡፡

በተጨማሪም በወር አበባ ጊዜ የሚሰማ ሕመምን ሊቀንስ ይችላል፡፡ ኾኖም በየቀኑ መውሰድ ያስፈልጋል፤ አንዳንድ ሴቶች ላይ ፊታቸው ላይ ማዲያት ሊያወጣ ይችላል፡፡ ማቅለሽለሽ፣ ራስ ምታትና የወር አበባ ለውጥም ሊኖረው ይችላል፡፡

መርፌ(injectables):- በመርፌ የሚሰጠው የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴ በየቀኑ ማስታወስ አያስፈልገውም፡፡ እስከ ሦስት ወራትም እርግዝናን ይከላከላል፡፡ ይሁንና የወር አበባ ሊያዛባ፣ ክብደት ሊጨምር እና ለረጅም ጊዜ ከተወሰደ ደግሞ እርግዝናን ሊያዘገይ ይችላል፡፡

ኢምፕላንት(Implants):- ይህ ዘዴ በክንድ የሚቀበር ሲሆን ረጅም ዓመታት ማለትም ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ያገለግላል፡፡ ይህንም በየቀኑ ማስታወስ አያስፈልግም፡፡ ይሁንና የወር አበባ ሊያዛባ ይችላል፡፡ መከላከያው መሰጠት እና መውጣት  ያለበትም  በጤና ባለሙያ ነው፡፡

ሆርሞን የሌለው ሉፕ (IUD):- ይህ የመከላከያ ዘዴ ከሆርሞን ነጻ ሲሆን ለረጅም ዓመታት ማለትም እስከ 12 ዓመታት ይሠራል፤ ኾኖም በወር አበባ ጊዜ ሕመም ሊኖር እና መጠኑ ሊጨምር ይችላል፡፡

ሆርሞን ያለው ሉፕ (IUD):- ይህ ዘዴ ለረጅም ዓመታት (እስከ 12 ዓመት) እርግዝናን ይከላከላል፤ የወር አበባን መጠንም ሊቀንስ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ አካባቢ የወር አበባ ሊያዛባ የሚችል ሲሆን መከላከያው መደረግ ያለበት በባለሙያ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሉፑ ማስወጣት ሲፈልጉም  የባለሙያ  እገዛ ያስፈልገዋል፡፡

የወንድ ቋሚ የወሊድ መከላከያ (Vasectomy):- ይህ ዘዴ እጅግ ውጤታማ ቋሚ የወሊድ መቆጣጠሪያ ነው፡፡ ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ አንዴ ከተሠራ በኋላ ወደ ነበረበት መመለስ አለመቻሉን ነው፤ ከሂደቱ በኋላ ለጊዜው ሕመም ወይም እብጠት ሊኖረው ይችላል፡፡

የማሕፀን ቱቦ መቋጠር (Tubal sterilization):- ቋሚና ውጤታማው የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ነው፡፡ ይሁንና አንዴ ከተሠራ በኋላ ወደ ነበረበት መመለስ አይቻልም፡፡ ከቀዶ ሕክምና ጋር ተያይዞ ጊዚያዊ ሕመም ሊኖር ይችላል፡፡

የአደጋ ጊዜ ክኒን:- ይህ ዘዴ ያልታቀደ ግንኙነት ከተፈጠረ በኋላ እርግዝናን ለመከላከል ይረዳል፡፡ ኾኖም ማቅለሽለሽ፣ ድካምና የወር አበባ ጊዜያዊ ለውጥ የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖሩት ይችላል፡፡

ማስተዋል ያለበዎት የአደጋ ጊዜ ክኒን በተቻለ መጠን ከግንኙነት በኋላ ቶሎ ሲወሰድ የበለጠ ውጤታማ መሆኑን ነው፡፡

ይሁንና የአደጋ ጊዜ ክኒንን እንደ መደበኛ የቤተሰብ ዕቅድ መጠቅም አይመከርም፡፡

ልብ ሊባል የሚገባው ነገር በማለት አቶ ፍርዱ እንደገለጹት ከላይ ከተጠቀሱት የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴዎች መካከል ኮንዶም ብቻ እርግዝናን ከመከላከል በተጨማሪ ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና ከአባላዘር በሽታዎች የመጠበቅ ልዩ ጥቅም አለው፡፡

በጥቅሉ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴዎች የጎንዮሽ ተፅዕኖ በሁሉም ሰው ላይ እኩል አይከሰትም፡፡

ለእርስዎ ተስማሚ የሆነውን ዘዴ ለመምረጥ እንደ ዕድሜ፣ የጤና ሁኔታ እና የወደፊት የወሊድ ፍላጎት ባሉ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርተው ከጤና ባለሙያ  ጋር  መማከር  ተገቢ  እና አስፈላጊ  ነው፡፡

 

መረጀ

የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን መውሰድ ያለባቸው እነማን ናቸው?

*ልጅ መውለድ የሚፈልጉ ነገር ግን በልጆች መካከል በቂ የጊዜ ርቀት (Spacing) እንዲኖር የሚፈልጉ እናቶች መጠቀም ይችላሉ፡፡

*የፈለጉትን ያህል ልጅ ወልደው ያጠናቀቁ ጥንዶች፤

*ወደፊት ልጅ የመውለድ እቅድ ያላቸው ነገር ግን አሁን ላይ ዝግጁ ያልሆኑ ጥንዶች ፤

*በትምህርት፣ በሥራ፣ በኢኮኖሚ ወይም በሌሎች ማሕበራዊ ምክንያቶች እርግዝናን ለጊዜው ማቆየት የሚፈልጉ ወጣቶች እና ጥንዶች፡፡

*እርግዝና ለጤናቸው አደገኛ የሆኑ እናቶች፤

*ከእርግዝና በተጨማሪ እራሳቸውን ከአባላዘር በሽታዎች መጠበቅ የሚፈልጉ ሴቶች ናቸው፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት  2  ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here