የዓለም ኢኮኖሚ ፈተናዎች

0
100

ባለንበት ዘመን የዓለም ኢኮኖሚ ከአንድ ቀውስ ሲወጣ ሌላ ቀውስ ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው የአቅርቦት መዛባት፣ የኑሮ ውድነት፣ የዕዳ ጫናዎች ገና ሳይረሱ የጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች እና የአየር ንብረት አደጋዎች በኢኮኖሚው ላይ አዲስ ውጥረት እየፈጠሩ ነው፡፡

ግጭት እና የአየር ንብረት ቀውስ ተለያይተው የሚከሰቱ ችግሮች ብቻ አይደሉም፡፡ አንዱ የፈጠረውን ጫና ሌላው ያባብሰዋል፡፡ ድርቅ የምግብ ምርትን ይቀንሳል፤ ግጭት ደግሞ የንግድ መንገዶችን ያስተጓጉላል፤ የነዳጅ ዋጋን ይጨምራል፤ ይህም የምግብን እና የሸቀጦችን ዋጋ ያንራል፡፡

የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እ.አ.አ የ2026 መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአውሮፓ (በዋናነት በዩክሬን እና ሩሲያ) ያሉ ግጭቶች የዓለምን የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ሁለት ነጥብ አምስት በመቶ ዝቅ አድርገውታል፡፡

አፍሪካ

አፍሪካ በዓለም አቀፍ የንግድ ትስስር ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሰለባ ሆናለች፡፡

የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ዕድገት በአንድ ነጠብ አምስት በመቶ ገድቦታል፡፡ የነዳጅ፣ የጋዝ እና የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ አማካይ የዋጋ ንረት ወደ አምስት በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ስለአፍሪካ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው እንደ ኢትዮጵያ፣ ማላዊ እና ሴራሊዮን ያሉ ነዳጅ አስመጪ ሀገራት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡ ከ29 በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ገንዘብም ከአሜሪካ ዶላር አንጻር የመግዛት አቅሙ ወርዷል፡፡

አፍሪካ ለዓለም የበካይ ጋዝ ልቀት ያላት ድርሻ ከአራት በመቶ በታች ነው፤ ይሁን እንጂ የአየር ንብረት ለውጥ እየፈተናት ይገኛል፡፡ በቅርብ ጊዜ የወጡ የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በአህጉሪቱ በደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የኢኮኖሚ ኪሳራ ደርሶባታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ20 በመቶ በታች የሚሆነው ብቻ በኢንሹራንስ የተሸፈነ በመሆኑ ቀውሱ በመንግሥታት በጀት ላይ ከባድ ጫናን ፈጥሯል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ አስከፊ ድርቅ እና ጎርፍ እንዲሁም በደቡባዊ አፍሪካ የሚከሰተው ማዕበል (በባሕርና ውቅያኖስ ላይ ተነስቶ ወደ የብስ የሚሻገር፣ ከፍተኛ ውድመት የማድረስ አቅም ያለው ታላቅ የነፋስና የዝናብ ማዕበል) የግብርናውን ዘርፍ ክፉኛ ጎድተውታል፡፡ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ የአፍሪካ ሀገራት እ.አ.አ እስከ 2050 ድረስ የኢኮኖሚ ዕድገታቸውን እስከ አራት በመቶ ሊቀንሰው እንደሚችል የዓለም ባንክ አስጠንቅቋል፡፡

መካከለኛው ምሥራቅ

ግጭቶች በቀጥታ በሚካሄዱበት በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ላይ የደረሰው የኢኮኖሚ ውድመት እጅግ ከፍተኛው ነው፡፡ የዓለም ባንክ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው የመካከለኛው ምሥራቅ ኢኮኖሚ በሁለት ነጠብ አንድ በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ በተለይም የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት የነዳጅ ግብይትን (ኤክስፖርት እና ኢምፖርት) በእጅጉ ጎድቶታል፡፡ ቀደም ሲል ጠንካራ ዕድገት የነበራቸው እንደ ሳዑዲ አረቢያ  እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚያቸው ቀንሷል፡፡ በተለይም በቀጣናው ቱሪዝም፣ አቪዬሽን እና የሎጂስቲክስ ዘርፎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተጎድተዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥም በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ እያሳደረ ያለው የኢኮኖሚ ጫና ከባድ ነው፡፡ ቀጣናው ካለበት ተፈጥሯዊ ደረቅ የአየር ፀባይ እና ተደጋጋሚ የጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች ጋር ተዳምሮ ሀገራቱን ለከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ እ.አ.አ በ2026 ባወጧቸው ይፋዊ ሪፖርቶች መሠረት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው የሙቀት መጠን በዕጥፍ (በአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ) እየጨመረ ነው፡፡ ይህ ክስተት በየዓመቱ በቀጣናው ሀገራት የነፍስ ወከፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ የሚደርስ ቀጥተኛ ቅናሽ እያስከተለ ነው፡፡

አውሮፓ

በምሥራቅ አውሮፓ (የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት) እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚነሱ ግጭቶች በአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ላይ ድርብ ጫና ፈጥረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአውሮፓ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ሁለት ነጠብ ሁለት በመቶ ወርዷል፡፡ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት መቆራረጥም በቀጣናው የኃይል ዋጋ እንዲንር ማድረጉ የፋብሪካዎችን ምርታማነት ቀንሷል፡፡ የብድር ወለድ መጨመርም የመንግሥታቱን ዕዳ የመክፈል ዐቅም ፈትኖታል፡፡

በተያያዘም የአውሮፓ የአየር ንብረት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአውሮፓ ከማንኛውም አህጉር በተለዬ የሙቀት መጠን እየጨመረ ነው፡፡ ይህም በኢንዱስትሪዎች ላይ ከባድ የገንዘብ ኪሳራ እያስከተለ ይገኛል፡፡

የአውሮፓ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ የ2026 መረጃ እንደሚያሳየው ከአየር ንብረት መዛባት ጋር በተያያዘ በሚደርሱ አደጋዎች ሳቢያ በአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ውስጥ ከ738 ቢሊዮን ዩሮ በላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ ተመዝግቧል፡፡ በተለይም በበጋው ወራት የሚከሰቱ የሙቀት ማዕበሎች እና ድርቆች የኃይል ማመንጫዎችን ዐቅም ቀንሰዋል፤ የጭነት መርከቦች የሚጓዙባቸውን ወንዞች በማድረቅ የንግድ ትስስርን አግደዋል፡፡ የቱሪዝም እና የግብርና ዘርፉንም አዳክመዋል፡፡

ሰሜን አሜሪካ

የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከሌሎች በተሻለ በዓለም ደረጃ የሚፈጠሩ ግጭቶችን እና የአየር ንብረት ለውጦችን የመቋቋም ዐቅም ቢያሳይም የሀገር ውስጥ ገበያውን ግን አዛብቶታል፡፡ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መናር በአሜሪካ የጭነት መጓጓዣ ወጪን በመጨመር በተጠቃሚዎች ላይ የዋጋ ንረትን አስከትሏል፡፡ ይህም የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔን ከፍ አድርጎ እንዲያቆይ አስገድዶታል፡፡

ከጂኦፖለቲካዊ መከፋፈል ጋር ተያይዞ የአሜሪካ አማካይ የታሪፍ መጠን 13 ነጥብ አምስት በመቶ መድረሱ ከእስያ እና አውሮፓ ጋር ያለውን የንግድ ልውውጥ ወጪ የሚጨምር ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል የዓለም ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆነችው አሜሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጡ የተፈጥሮ አደጋዎች የዋጋ ንረትን እንዲያገረሽ እያደረጉባት መሆኑን የኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ ሳፕለይ ቼይን ትንተና ያመላክታል፡፡ አሜሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የምታጣው የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ዋጋም 36 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ በተደጋጋሚ የሚከሰቱት ሰደድ እሳት፣ ማዕበልና ጎርፍ የሀገሪቱን የትራንስፖርት እና የጭነት ትስስሮች አስተጓጉለውታል፡፡

እስያ

እስያ በከፊል በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ምርት ሳቢያ ኢኮኖሚዋ ቢደገፍም በግጭቶች እና ጦርነቶች ምክንያት የንግድ መስመሮች መዘጋት ግን ስጋት ሆኖባታል፡፡ የባሕር ላይ ትራንስፖርት እና የጭነት መድን ወጪዎች መጨመር የእስያ ሀገራት ምርቶቻቸውን ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ የሚልኩበትን ዋጋ አንሮታል፡፡ በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ትንበያ መሠረት የጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች እና የንግድ መበታተን ካልተገቱ እስያ በአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ ሳቢያ ከፍተኛ የፋይናንስ ኪሳራ ሊገጥማት ይችላል፡፡

የእስያ – ፓስፊክ ቀጣና በአስከፊ የአየር ንብረት መዛባት እና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድመትም እያስተናገደ ይገኛል፡፡ እንደ ዴሎይት (በየዓመቱ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ውድመት፣ የቴክኖሎጂ  ሽግግር እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ያሉ ሪፖርቶችን የሚያወጣ ተቋም) ጥናት ከሆነ እስያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት እርምጃ ካልወሰደች እ.አ.አ እስከ 2070 ድረስ የምታጣው የሀብት መጠን 96 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ በርካታ አካባቢዎች ግጭቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ተለያይተው አይመጡም፡፡ ድርቅ የግብርና ምርት መቀነስን በማስከተል  የምግብ ዋጋን ያንራል፤ ግጭት ካለ ደግሞ የመጓጓዣ ወጪን  ይጨምራል፡፡ ይህም የምግብ ዋጋ እንዲያሻቅብ ያደርጋል፡፡ ሁለቱ አንድ ላይ ሲመጡ ደግሞ የችግሩ ክብደት ይጨምራል፡፡

የዓለም የምግብ  እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት እና የገበያ መዛባት በአንድ ላይ የምግብ ተደራሽነትን እየገደቡ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡

ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ችግር አይደለም፤ የአፍሪካም ችግር ነው፡፡ በምዕራብ አፍሪካና በሳህል አካባቢ (ሴኔጋል፣ ሞሪታንያ ፣ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኒጄር፣ ቻድ እና ሱዳን) ግጭት፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የምግብ ዋጋ መናር እና የሰብዓዊ ድጋፍ እጥረት ተደራራቢ ችግሮች ናቸው፡፡ ፋኦ እንደሚገልጸው እ.አ.አ በ2026 ከሰኔ እስከ ነሐሴ ባሉት ወራቶች በምዕራብ አፍሪካ እና በሳህል አካባቢዎች እስከ 52 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች አጣዳፊ የምግብ እጥረት ገጥሟቸው ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እ.አ.አ በ2026 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚወጣው አንድ ዶላር እስከ 15 ዶላር የሚደርስ የኢኮኖሚ ጥቅምን ያስገኛል፡፡

በመሆኑም ሀገራት ለአካባቢ ጥበቃ እና ለአረንጓዴ ልማት የሚመድቡት በጀት እንደ ወጪ ሳይሆን የዓለምን ኢኮኖሚ ከከፋ ውድቀት የመታደጊያ ዋነኛ ኢንቨስትመንት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው መረጃው ጠቁሟል፡፡

በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶችን ደግሞ ለግጭቱ መነሻ የሚሆኑ ምክንያቶችን ማድረቅ እና ችግሮችን በውይይት መፍታት አማራጭ የማይገኝለት መፍትሔ መሆኑን አመላክቷል፡፡

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 2  ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here