የሥነ ሕዝብ ጥናት – ከአሃዝ ባሻገር

0
98

የሥነ-ሕዝብና የጤና ጥናት ለሀገር ዕድገት እና ለኅብረተሰብ ጤና መሠረት ከሆኑት ወሳኝ ዘርፎች አንዱ ነው። የሰው ልጅ ሕልውና እና ጤና ደግሞ በየጊዜው ከሚለዋወጡ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኖሎጅያዊ ሁኔታዎች ጋር የተሳሰሩ ናቸው። የሕዝብ ቁጥር ዕድገት እና ስርጭት ከቀድሞው ፈጣን በሆነ መልኩ እየተቀየረ ነው፤ ይህ የለውጥ ሂደት ለአንድ ሀገር የዕድገት ጎዳና ትልቅ አቅም ከመሆን ባሻገር በጤና አጠባበቅ፣ በሥራ ፈጠራ እና በማሕበራዊ አገልግሎቶች ላይ የራሱን ፈተናዎች እና ዕድሎች ይዞ ይመጣል።

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆን፣ የከተሞች መስፋፋት እና የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚደረጉ ዲጂታል ሽግግሮች የሥነ-ሕዝብና የጤና ጥናትን ወሳኝ ያደርጉታል። የሕዝብን የዕድሜ መዋቅር፣ የቤተሰብ እቅድ አጠቃቀም፣ የእናቶችና ህጻናት ጤና ሁኔታ እንዲሁም ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን በማቀናጀት የሚደረግ ጥናት፤ ፖሊሲ አውጪዎች ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ድርሻው የጎላ ነው።

ከሰሞኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የባሕር ዳር ቅርንጫፍ የክልሉን ሥነ-ሕዝብና ጤና የተመለከለተ ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለውሳኔ ሰጪዎች ዋና ግብዓት እንደሚሆን የጥናት ውጤቱ ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ይፋ በተደረገበት ወቅት ተመላክቷል፤ ከስምንት ወራት ጊዜን የወሰደው ጥናቱ ያጋጠሙ ፈተናዎችን በሳይንሳዊ አሠራርና ከኅብረተሰቡ ጋር በተደረገ ውይይት በማለፍ የተሰበሰበ መረጃ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ጤናው እንደገለጹት ተቋሙ መረጃዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የመሰብሰብ፣ የመተንተን እና የማሰራጨት ሕጋዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ አምስተኛው ዙር ጥናት ደግሞ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ባለ ሁለት ደረጃ የናሙና አመራረጥ ሥነ-ዘዴን የተከተለ ነው፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ 805 የቆጠራ ቦታዎች ሲሸፈኑ፤ በአማራ ክልል ደግሞ ከ60 በላይ የቆጠራ ቦታዎች በጥናቱ ተካተዋል፡፡ ጥናቱንም በክልሉ የሚገኙ አራቱም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች (የባሕር ዳር፣ የጎንደር፣ የደሴ እንዲሁም የደብረ ብርሃን ማዕከላት) በቅንጅት መርተውታል፡፡ “በእያንዳንዱ የቆጠራ ቦታ በከተማ ከ150 እስከ 200፣ በገጠር ደግሞ ከ100 እስከ 150 አባወራዎች ካሉበት መንደር ውስጥ 28 አባወራዎች በሳይንሳዊ ዘዴ እየተመረጡ ተጠይቀዋል፡፡ ይህም ጥናቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ሊወክል የሚችል አስተማማኝ መረጃ እንዲይዝ አድርጎታል” ነው ያሉት፡፡

አቶ ሀብታሙ ተቋማቸው ያከናወናቸው ብሔራዊ የተቀናጀ ቤተሰብ ጥናት፣ የፍልሰት እና የሥራ ስምሪት ስታትስቲክስ መረጃዎች ቀደም ሲል ይፋ መደረጋቸውን ጠቁመዋል፤ የግብርና ናሙና ቆጠራ እና የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ውጤቶችም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል፡፡

ሰሞኑን ይፋ የተደረገው መረጃ መፍትሔ የሚያመጣው በተግባር ሲተረጎም ብቻ ነው፤ ያለበለዚያ በመደርደሪያ ላይ የሚቀመጥ ወረቀት ሆኖ ይቀራል፡፡ በመሆኑም የስታትስቲክስ ጽ/ቤት ይፋ ያረገው የጥናት ውጤት በመያዝ የት ላይ ችግሮች አሉ? ምን መደረግ አለበት? የሚሉትን ለመመለስ የሚመለከተው አካል እንደየ ድርሻው ወስዶ ሊጠቀምበት ይገባል ተብሏል፡፡

በመሆኑም ፖሊሲ አውጪዎች፣ የፍትሕ አካላት፣ የጤና ባለሙያዎች እና የማኅበረሰብ መሪዎች እነዚህን መረጃዎች መነሻ በማድግ ዕቅድ ማውጣት፣ ሕጎችን ማስከበር፣ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እና ግንዛቤን ማስፋፋት እና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸውም ሥራ አስኪያጁ አቶ ሀብታሙ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የዋናው ቢሮ ዋና (ሲኒየር) ኤክስፐርት አቶ እንዳሻው ፈለቀ ቁጥራዊ መረጃዎችን አቅርበዋል፤ በዚህም አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ ማኅበራዊና ጤና ነክ እውነታዎችን አመላክተዋል፡፡ በጥናቱ ከተካተቱት በርካታ አመልካቾች መካከል የኤች አይ ቪ ሥርጭት መጠን፣ ስሜታዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት፣ አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች ይገኙበታል፡፡

የኤች አይ ቪ ሥርጭት በሀገር አቀፍ ደረጃ እና በአማራ ክልል የቫይረሱ ሥርጭቱ በመቶኛ ምን ያክል እንደሆነም ተመዝግቧል፡፡ በዚህም በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ በመሆኑ ጉዳዩ አሁንም ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በጥናቱ እንደተመላከተው በሀገራችን ከሦስት ሴቶች አንዷ በገዛ ቤቷ ውስጥ የጥቃት ሰለባ ትሆናለች፤ ይህም በዝምታ ሊታለፍ የማይችል ከባድ ማኅበራዊ ቀውስ መኖሩን ያረጋግጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጥናቱ የውልደት መጠንን፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ አጠቃቀምን፣ የእናቶችና የሕፃናት ጤናን፣ አመጋገብን እንዲሁም ክትባትን የተመለከቱ ዘርፈ-ብዙ ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን አጠቃልሎ መያዙን ነው አቶ እንደሻው ያብራሩት፡፡

የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) እንዳስገነዘቡት የተሰበሰቡት መረጃዎች የክልሉን የ25 ዓመታት መሪ የልማት ዕቅድ ለመከለስ፣ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ለማዘጋጀት፣ የዘላቂ ልማት ግቦችን እና የሰው ልጅ ዕድገት አመልካችን በትክክል ለመለካት ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ አላቸው፡፡ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እነዚህን መረጃዎች ለመመሪያና ለውሳኔ አሰጣጥ በአግባቡ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

መረጃ

ፆታዊ ጥቃት (Sexual Violence) ማለት አንድ ሰው ያለ ፈቃዱ ወይም በግድ፣ በማስፈራራት፣ በማታለል ወይም በሥልጣን አላግባብ በመጠቀም ሌላውን ሰው ለወሲባዊ ድርጊት የሚያጋልጥ ተግባር ነው። በሴቶች፣ በወንዶች፣ በሕፃናትና በማንኛውም ሰው ላይ ሊፈጸም ይችላል።

ፆታዊ ጥቃት ምን ምን ያካትታል?

  1. የወሲብ ድፍረት: -የሌላ ሰውን ፈቃድ ሳያገኙ በግድ ወይም በሌሎች አስገዳጅ ሁኔታዎች የወሲብ ግንኙነት መፈጸም።
  2. ያልተፈለገ የሰውነት ንክኪ: -ያለ ፈቃድ የግል የሰውነት ክፍሎችን መንካት፣ መዳበስ ወይም መሳም።
  3. የወሲብ ትንኮሳ :- የወሲብ ፍላጎት የሚያሳዩ ያልተፈለጉ ንግግሮችን፣ ስድቦችን፣ ምልክቶችን ወይም ድርጊቶችን ማድረግ።
  4. በግድ ወይም በጫና ወሲባዊ ድርጊት ማስፈጸም:- በዛቻ፣ በማስፈራራት፣ በገንዘብ ወይም በሥልጣን ጫና ሰውን ወደ ወሲባዊ ድርጊት ማስገባት።
  5. የወሲብ ብዝበዛ:- የሰውን ድህነት፣ የእርዳታ ፍላጎት፣ የዕድሜ ልዩነት ወይም የሥልጣን አለመመጣጠን በመጠቀም ለግል ጥቅም ወሲባዊ ድርጊት ማስፈጸም።
  6. የሕፃናት ፆታዊ ጥቃት:- ሕፃናትን ለወሲባዊ ድርጊት ማጋለጥ፣ ማስገደድ፣ ማታለል ወይም በወሲባዊ ዓላማ መጠቀም።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የጥቅምት 2  ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here