ውሻ አከራይ እና ተከራይን የሚያገናኘው

0
47

በቻይና በበየነ መረብ/ኦን ላይን ፕላት ፎርም/ ውሻ አሳዳሪዎችን በሰዓት በሚሰላ ክፍያ ከተከራይ ተገልጋዮች ጋር ማገናኘት ያስቻለው ዋንግፉ የተሰኘው መድረክ በከፊሎች በስራ ፈጠራው ቢወደስም ከከፊሎቹ በአጋጠመው ነቀፌታ ውዝግብ ማስነሳቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረገፅ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡

የቤት እንስሳት በተለይም ዉሾችን ከሰዎች ስሜት፣ በቀረቤታ  የሚያሳዩት ታማኝነት አንጻር ጠቀሜታቸው ቢታወቅም ብዙዎች በሀላፊነት እንስሳቱን ለመንከባከብ ሀላፊነት ሲወስዱ አይስተዋልም፡፡እነዚህን መሰል ሰዎች ታዲያ የቤት እንስሳቱን በመከራየት ለዘለቄታቸው ሳይጨነቁ ለሰዓታት በጓደኝነት መደሰት ችለዋል- በኪራይ፡፡

ዋንግፉ የተሰኘው ውሻ አሳዳሪዎችን ከተከራይ ተገልጋዮችጋር የሚያገናኘው መድረክ በ2026 መጋቢት ወር በቤጂንግ፣ሻንጋይ እና ሺንዚንን በመሳሰሉ ከተሞች ስራውን መጀመሩን ድረገጹ አስነብቧል፡፡ በመድረኩ ለመገልገል ተከራይም ሆነ አከራዮች /አገልግሎት ሰጪውም ሆነ አገልግሎት ፈላጊው/መመዝገብ ግድ ይላቸዋል፡፡ ተከራዮች የሚፈልጉትን የውሻ ዝርያ ፣ቀለም ወዘተ መግለጽ፤ አከራዮችም የውሻውን ፎቶግራፍ መለጠፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ተከራዮች በሰዓት ለአንድ ውሻ ከ10 እስከ 60 “የን” /የቻይና ገንዘብ/ ወይም ከ1.5 እስከ 9 “ዶላር” አስቀድመው መክፈል ግዴታቸው ሆኖ በሚፈራረሙት ውል ላይ ይሰፍራል፡፡ተከራዩ የተከራየው ውሻ በየትኛው አካባቢ እንደሚንሸራሸር ቀድሞ አከራዩ ማወቅ አለበት፡፡ይህም ውሻው በማያውቀው አካባቢ ሄዶ ያልተለመደ ባህርይ እንዳያሳይ እና ከተከሰተም መፍትሄ ለመሻት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በመጨረሻም በሚፈራረሙት ውል መሰረት ተከራይ በውሉ ላይ በሚጠቀሰው ጊዜ ተገልግሎ ውሻውን ካነሳበት ቦታ የመመለስ ግዴታ እንዲሁም በማንኛውም መልኩ ለሚደርስ አደጋ ወይም ጉዳት አገናኙ ዋንግፉ መድን/ኢንሹራንስ/እንደሚገባ ነው በማጠቃለያነት የሰፈረው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here