የውቅያኖስ ውስጥ የሙቀት ሞገዶች ተጽእኖ እስከአሁን ከተጠኑበት ጠባብ ቀጣና እና ካጠረ ጊዜ ምጣኔ ሽፋን ባለፈ በሰፊ ቀጣና ረዘም ላለ ጊዜ ማከናወን ድብቁን እውነታ ገልጦ አሳሳቢነቱን ማሳየት እንደሚያስችል ሳይንስ ዴይሊ ድረገፅ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በአሜሪካ የቨርጂኒያ የባህር ሳይንስ ተቋም በመረጃ ምንጭነት እንዳስነበበው እስከአሁን ሲሰራባቸው የነበሩ ሒደቶች እና መለኪያዎች የጥናት እና የምርምር ውጤቶችን በ150 በመቶ ዝቅ አድርገው ነው ያሳዩት፡፡ የምርምር ተቋሙ ተመራማሪዎች የባህር ሙቀት ማእበል በሚከሰትበት ጊዜ በውስን ቀጣና ብቻ ሳይሆን ከማእበሉ በፊት እና በኋላ ያሉ ሁነቶች ድምር ነው ትክክለኛ ተጽዕኖውን የሚያመላክተው በሚል ባቀረቡት ማስረጃ ነባሩን ሂደት ተችተዋል፡፡በውጤቱም ትክክለኛ ማደማደሚያ ላይ መድረስ እንደሚቻል ማሳመን ችለዋል፡፡
የአዲሱ ጥናት ስልት ደጋፊ ከሆኑት ተመራማሪዎች መካከል ረዳት ፕሮፌሰር ሪካርዶ ኡትዚግ ናርዲ የባህር ሙቀት ተጽእኖን ለመገንዘብ ውስን ቀጣናን በናሙናነት ወስዶ መስራት እውነተኛውን የዓለም ሁኔታ እንደማይወክል፣እንደማያሳይም ነው ያብራሩት፡፡በማደማደሚያቸውም ከሙቀት ማእበሉ በፊት እና በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ የተስተዋሉ ድምር ውጤቶች ግምት ውስጥ መግባት እንደሚኖርባቸው ነው ያሰመሩበት፡፡
ተመራማሪዎቹ የሙቀት ሞገዶች የሚስተዋሉበትን ጊዜ በሁለት ከፍለውታል – አንደኛው በ60 ቀናት ውስጥ፣ ሁለተኛው ደግሞ በ90 ቀናት ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የሚከሰት የሙቀት ማእበል በሚል፡፡ በዚህም የሚካሔዱት ጥናት እና ምርምሮች ረዘም ያለ ጊዜ ድምር ውጤቶችን ማካተት እንደሚኖርባቸው ነው ያደማደሙት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


