የዕውቀት ሰንሰለት

0
114

ትምህርት የነገን ትውልድ ለመቅረጽ፣ ሀገርን ለማሻገር እና የዜጎችን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የሚያስችል ዋነኛ ማኅበራዊ መሠረት ነው። የዚህ ትምህርታዊ ሂደት ዐቢይ የደም ዝውውር ደግሞ የመማሪያ መጽሐፍት በወቅቱና በተሟላ ሁኔታ በተማሪዎች እጅ መድረስ ነው።

መማሪያ መጽሐፍ ከቀላል የትምህርት መሣሪያነት በላይ የዕውቀት በር፣ የነጻ አስተሳሰብ ማዕቀፍ እና የተማሪውን የፈጣን ዕድገት አቅጣጫ የሚወስን መሠረታዊ ግብዓት ነው። አንድ ተማሪ መጽሐፉን እጁ ላይ አግኝቶ ወደ ቤቱ ሲመለስ በክፍል ውስጥ የተማረውን በድጋሚ የመገምገም፣ የቤት ሥራውን በራሱ ጥረት የመሥራት እና ለቀጣዩ ቀን እንዲዘጋጅ ያደርጋል።

መጽሐፍ በሌለበት ሁኔታ ግን ይህ የመማር ሰንሰለቱ እክል ይገጥመዋል፤ ተማሪውም በመምህሩ ማብራሪያ ላይ ብቻ እንዲመረኮዝ ይገደዳል። መማሪያ መጽሐፍ ተደራሽ ሲሆን ደግሞ ተማሪዎች ራሳቸውን ችለው የማንበብ አቅማቸውን እንዲያዳብሩ፣ የቤት ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሠሩ፣ በክፍል ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ እንዲጨምር እንዲሁም በመምህርና በተማሪ መካከል የሚደረገው የዕውቀት ቅብብል እንዲፋጠን ትልቅ ፋይዳ አለው።

በአንጻሩ የመማሪያ መጻሕፍት በወቅቱ ሳይቀርቡ ሲቀሩ፣ የችግሩ ጫና በተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይወሰን በመምህራንም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። መምህራን አብዛኛውን የትምህርት ጊዜያቸውን በጥቁር ሰሌዳ ላይ በመጻፍ እና ተማሪዎች እንዲገለብጡ በማድረግ ያሳልፉታል። ይህ ሁኔታ ለማብራራት፣ ለመወያየት፣ ለጥያቄና መልስ እንዲሁም ለተማሪዎች የተለያዩ የመማር ዘዴዎችን ለመተግበር የሚውለውን ጊዜ በመሻማት የትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።

አቶ የሺዋስ አናጋው በሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፤ በወረዳው ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ 60 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ለበኩር በስልክ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በመሠረታዊ ክፍሎች የመማሪያ መጽሐፍ እጥረት መኖሩን አክለዋል። ችግሩንም ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ መፍትሔ እንዲሰጥበት እየተነጋገሩ መሆኑን አቶ የሺዋስ አናጋው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የተለዬ ሁኔታ የሚታይ ሲሆን፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል መጽሐፍት ታትመው አንድ ለአንድ ለተማሪዎች መድረሳቸውን የከተማው ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትበይን ባንቲሁን ለበኩር በስልክ ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር በተገናኘ በኩር በከተማ አስተዳደሩ በሚገኘው የፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት ምልከታ አድርጋለች፤ በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር ደረጀ ከፋለ በትምህርት ቤቱ ምንም አይነት የመጽሐፍ እጥረት አለመኖሩን እና ለተማሪዎችም በአግባቡ መሰራጨቱን ነው የገለጹት።

የመጻሕፍት እጥረት አለመኖሩ ደግሞ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠት አቅም እንደሆናቸው ነው ምክትል ርእሰ መምህሩ የተናገሩት፤ መምህራን እና ተማሪዎችም ጊዜያቸውን እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል።

የትምህርት መምሪያው ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትበይን አክለውም ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ነባር የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መጽሐፍ እንደደረሳቸው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ ከሰሜን ጎጃም (ከባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ) 29 ትምህርት ቤቶች ወደ ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተካለዋል፤ እነዚህ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ መጻሕፍታቸው በተለያዩ ምክንያቶች ወድመውባቸዋል፤ የመፍትሔ አማራጮች እየተፈለጉም ይገኛሉ። ለግል ትምህርት ቤቶች ተዘጋጅተው የነበሩ መጻሕፍትን ካልወሰዷቸው ለእነዚህ የተቸገሩ ትምህርት ቤቶች እንደሚሰራጩ ወ/ሮ ትበይን ገልጸዋል።

የመማሪያ መጽሐፍ ለተማሪ ሲደርስ ተማሪው በቤት ውስጥ ራሱን ችሎ የመማር፣ የማንበብ ልምዱን የማጠናከር እና የቤት ሥራውን የመሥራት አቅም ያገኛል።

በመሆኑም የመጽሐፍ ማተም፣ ማከፋፈልና በወቅቱ ተማሪዎች እጅ ማድረስ ከትምህርት ዘርፉ ቀዳሚ ተግባራት መካከል ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም ዛሬ በእጁ የደረሰ መጽሐፍ ነገ በተማሪው ዕውቀት የሚታይ እውነተኛ ለውጥ ነውና፡፡

አማርኛ በአማርኛ

አለ  —- ለመነ

ሠዐለ —- ሣለ

አመት — አገልጋይ

ዐመት — ዘመን

ገአዘ — ጀመረ

ግእዝ — መጀመሪያ

ገዐዘ — ተጓዘ

ግዕዝ — ነፃ

(ሰናይት በየነ)

በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here