ይብቃን!

0
116

በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ “መቻል” የሚባል የተቀደሰ መርዝ አለ።

ስንቶቻችን ነን በየጓዳችን የገዛ ነፍሳችንን ሬሳ ተሸክመን፣ በሰው ፊት ግን እንደ ጤነኛ ሰው ፈገግ ለማለት ጥርሳችንን ነክሰን የምንኖረው?

በባህላችን “ታግሶ ነው” የሚባለው የይሉኝታ ሰንሰለት፣ ስንቱን ሰው ከሚጠላውና ከሚመርዘው ሰው ጋር በሕይወት እያለ ወደ ገሃነም እንደከተተው ስናስበው ያስፈራል።

ሽማግሌው፣ ቤተሰቡ፣ የሰፈር ይሉኝታው… ሁሉም ተባብረው እጃችንን በሚቆርጠው እሾህ ላይ ተጨማሪ የጨዋነት ቋጠሮ ያበጁበታል። “ትዳርና ወዳጅነት መከራን መቻል ነው” እየተባለ የተነገረን ተረት የገዛ ማንነታችንን በቁም አክስሞ ወደ ባዶ ጥላነት እንድንቀየር ፈርዶብናል።

ውጩ ሲታይ የተከበረ ማዕድ፤ ውስጡ ሲበረበር ግን ማለቂያ የሌለው የቃላት ጦርነትና የድካም አዙሪት!

እርስ በርስ እየተላለቅን፣ በየሰከንዱ እየደማን፤ ነገር ግን የበሰበሰውን በር ለመክፈት ከነጻነቱ ይልቅ ስቃዩን መርጠን እዚያው እንቀመጣለን። ለመሆኑ መቼ ነው መታገስ ወደ ራስን ማጥፋት፣ ጨዋነት ደግሞ ወደ ፍጹም ፈሪነት የተቀየረው?

እስከ መቼስ ነው በሐሰተኛ ታጋሽነት ስም የገዛ ሕይወታችንን በቁም እየቀበርን የምንኖረው? አንዳንዴ ትልቁ ጀግንነት እጅን በሚያደማ ገመድ ላይ ሙጥኝ ማለት ሳይሆን ደም የጠማውን አዙሪት ሰብሮ በክብር “ይብቃን!” ማለት ነው።

በሁለት ሰዎች እጅ መካከል የተወጠረ የእሾህ ገመድ ይታይህ።

ሁለቱም እጆቻቸው ደምተዋል፤ ሁለቱም በሕመሙ ምክንያት ሌት ተቀን ይጮሃሉ፤ ሁለቱም እርስ በርሳቸው ይጠላላሉ፤ ነገር ግን አንዳቸውም ገመዱን ለመልቀቅ እጃቸውን አይዘረጉም።

በየቀኑ ንትርክ፣ በየሰዓቱ ንዝንዝ፣ ማለቂያ የሌለው ውግዘትና ጩኸት… ይሁን እንጂ አንደኛውም “በቃኝ!” ብሎ ዞር ለማለት አይደፍርም።

ለምንድን ነው የሰው ልጅ ከሚጠላውና ከሚጎዳው ሰው ጋር በገሃነም ውስጥ እየነደደ አብሮ መኖርን የሚመርጠው? ለምንድን ነው ራስን ከሚመርዝ ግንኙነት በሰላም ራስን ማግለል እንዲህ የተራራ ያህል የከበደው?

ታዋቂው የህልውና ፈላስፋ ዣን ፖል ሳርተር “ዝግ በር” በተሰኘው ዝነኛ ተውኔቱ ውስጥ የሰውን ልጅ እንግዳ ባሕርይ የሚያሳይ አንድ አስደንጋጭ ክስተት አቅርቧል።

በታሪኩ ውስጥ ያሉ ገጸ-ባህሪያት በአንድ ክፍል ውስጥ ተዘግቶባቸው ሌት ተቀን እርስ በርሳቸው በቃላት ይተላለቃሉ፤ አንዱ የሌላው ገሃነም ሆኖ ሕይወታቸውን ያመሰቃቅሉታል።

በመጨረሻ ግን ያ ለዓመታት ተቆልፎ የነበረው በር ወለል ብሎ ክፍት ሲሆንና ነጻ የመውጣት ሙሉ ዕድል ሲያገኙ አንዳቸውም ክፍሉን ጥለው ለመውጣት አይደፍሩም!

ይልቁንም ክፍት በሩን በፍርሃት ተመልክተው መልሰው ይዘጉታል፤ እርስ በርሳቸው ወደሚሰቃዩበት የታወከ አዙሪትም ይመለሳሉ።

ይህ የፈጠራ ተረት ብቻ አይደለም። ታዋቂው የማኅበራዊ ሥነ-ልቦና ሊቅ ኤሪክ ፍሮም ከነጻነት መሸሽ በተሰኘው ጥልቅ የምርምር ሥራው ላይ እንደሚያስረዳው የሰው ልጅ ትልቁ ድብቅ ፍርሃት “ነጻ መሆን” ነው።

ራሱን የቻለ የውስጥ ሰላም መገንባት ያቃተው አእምሮ ከሚጎዳው ሰው ጋር “መርዛማ ጥገኝነት” ይፈጥራል።

ስቃዩን፣ ንትርኩንና ጭቅጭቁን እንደ መኖሪያ ቤት ያደርገዋል፤ ምክንያቱም ያንን የለመደውን የየዕለት ጦርነት ማጣት ወደማያውቀው የብቸኝነት ባዶነት መውደቅ ሆኖ ስለሚሰማው ነው። የሚያውቁት ስቃይ ከማያውቁት ነጻነት ይቀላል ብሎ ያምናል።

በእኛ በኢትዮጵያዊው ማኅበራዊ አውድ ደግሞ ይህ ችግር ይበልጥ ሥር የሰደደ ነው። በባህላችን መቻል፣ ማጎንበስ፣ ዝም ብሎ መበላትና መከራን እንደ ጽድቅ መቁጠር “ጨዋነት” ተደርጎ ይወደሳል።

“ትዳር/ወዳጅነት ታግሶ ነው” የሚለው ምክር መርዛማና ሕይወት አጥፊ ግንኙነቶችን ሳይቀር በሐሰተኛ ታጋሽነት እንድንሸከም አስገዶናል።

በዚህም የተነሳ ሰዎች በክብር ተለያይተው የነፍስ ሰላም ከማግኘት ይልቅ በሰዎች ፊት አብረው እንዳሉ ለማስመሰል ሲሉ በየጓዳው እርስ በርስ ነፍሳቸውን ሲያደሙ ይኖራሉ።

ታዲያ አንድ ግንኙነት መሞቱንና መለየት እንዳለብን በምን እንመርምር?

የታሪክ፣ የፍልስፍናና የሥነ-ልቦና ድርሳናት ሦስት የማይሳሳቱ መመርመሪያዎችን ያስቀምጣሉ፡-

የማንነት መኮሰስ፡-

የጀርመኑ ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ “ከአውሬ ጋር ስትታገል ራስህ አውሬ እንዳትሆን ተጠንቀቅ” ብሏል። አብረኸው ባለኸው ሰው ምክንያት የዋህነትህ ወደ ቁጣ፣ ደግነትህ ወደ ተንኮል፣ ሰላምህ ወደ ዘወትር ጥርጣሬ እየተቀየረ ከሆነና ራስህን በመስታወት ስታየው መጥላት ከጀመርክ ያ ግንኙነት ጓደኝነት ሳይሆን የነፍስህ እስር ቤት ነው።

የኃይል መሟጠጥ፡-

ጤናማ ግንኙነት ኃይል ያድሳል፤ መርዛማ ግንኙነት ግን የሰውን ጉልበት እንደ ደረቅ ስፖንጅ ይመጥጣል። ከእርሱ/ከእሷ ጋር በምትሆንበት ጊዜ የምትጠነቀቀው እያንዳንዱ ቃል፣ የምትፈራው እያንዳንዱ አተነፋፈስና የሚሰማህ የማያቋርጥ ድካም የግንኙነቱ መሠረት መበስበሱን የሚያሳይ ቀዳሚ ምልክት ነው።

የመፍትሔ አልባነት ዑደት ፡-

አንድን ችግር ለመፍታት መቶ ጊዜ ተነጋግራችሁ፣ መቶ ጊዜ ተጣልታችሁ፣ መቶ ጊዜ እዚያው አዙሪት ውስጥ የምትመለሱ ከሆነ ውይይቱ መፍትሔ አምጪ ሳይሆን የንትርክ ሱስ (ትራውማ ቦንዲንግ) ሆኗል።

ምን ማድረግ ይሻላል? የመሸኘት ጥበብ ምንድን ነው?

የማይስማሙትን ሰው መሸኘት ጦርነት ማወጅ ሳይሆን የቀዶ ጥገና ሕክምና ማድረግ ነው። ሐኪም የበሰበሰውን የሰውነት ክፍል ሲቆርጥ በቁጣ ወይም በበቀል ስሜት አይደለም፤ የተቀረውን ሕይወት ለማዳን ሲል በታላቅ ጥንቃቄና ቁርጠኝነት እንጂ። ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለብን እንመልከት:-

አንደኛ ድፍረቱን ከፍርሃትህ ማዶ መፈለግ

ለመለያየት ሌላኛው ሰው እስኪቀየር ወይም ተስማምቶ እስኪሰናበትህ አትጠብቅ። መርዛማ ሰው በፍጹም በፈቃዱ አይለቅህም። ውሳኔው የአንተ ብቻ መሆን አለበት። “ይኼ መንገድ ለእኔ አይበጅም፤ እኔና አንተ እዚህ ጋር አብቅቶልናል” የሚለውን ቃል ያለ ጩኸት፣ ያለ ማብራሪያ ጋጋታና ያለ ድርድር በጽናት ተናገር።

ሁለተኛ የማሸነፍን አባዜ መተው

ብዙ ሰዎች ከመለያየት የሚያመነቱት “የመጨረሻውን ቃል ተናግሬ፣ አሸንፌው/አዋርጄው ልለይ” በሚል ቂም ነው። ፈላስፋው ሴኔካ እንደሚያስተምረን ከመርዝ ጋር የምታደርገው ብቸኛው ድል መርዙን ጥሎ መሸሽ እንጂ መርዙን ለመበቀል መሞከር አይደለም። ላለመስማማት መስማማት፣ ከዚያም ክርክሩን ማቆም ትልቁ ድል ነው።

ሦስተኛ በፍቅርና በምርቃት ድንበር ማበጀት

መሸኘት ማለት መርገም ማለት አይደለም። “በሕይወቴ ውስጥ ስለነበረሕ ጊዜ አመሰግናለሁ፤ ካንተ የተማርኩትን ወስጃለሁ፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ በአንድ መንገድ መቀጠል አንችልም” ብለህ በልብህ የፍቅር ማህተም አትመው፤ በሩ ላይ ግን የማይናወጥ መዝጊያ አብጅለት።

ሕይወት አጭር ናት። በየቀኑ በንትርክ የሚባክን እያንዳንዱ ሰከንድ ነገ በጸጸት የሚታወስ የሕይወት ዕዳ ነው። ፈረስ ካረጀና ካልተስማማ እረፍቱን መስጠት እንደሚገባው ሁሉ ያከተመለት ግንኙነትም በክብር መቆም አለበት።

ልብ ልንለው የሚገባው ነጥብ ሰውን “ይብቃን” ብሎ በሰላም መሰናበት የጭካኔ ምልክት አይደለም፤ የራስን የተሰበረ ሕይወት እና የሌላውን ሰው ጊዜ የማዳን የመጨረሻው የጀግንነት እርምጃ እንጂ።

እጃችንን ያደማውን የእሾህ ገመድ ዛሬውኑ እንልቀቀው፤ ባዶ የሚቀረው እጅ ነገ ንጹሕ ሰላምንና እውነተኛ ወዳጅነትን ለመጨበጥ ክፍት ይሆን ዘንድ! ሕይወት እንደገና ይቀጥላል!፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥቅምት 2  ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here