የዝውውር ወጪ፣ የደመወዝ ክብረወሰን እና የዋንጫ ፉክክር

0
68

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዲሱ የውድድር ዓመት በ18 ክለቦች ተጀምሯል፡፡ ከባለፈው ዓመት የ20 ክለቦች እና የሁለት ምድብ አወቃቀር ወደ አንድ ወጥ የውድድር ስርዓት መሸጋገሩ የዘንድሮውን ሊግ ከሚለዩት ዋና ዋና ለውጦች አንዱ ነው። በውድድር ዓመቱ 306 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

ጨዋታዎችም በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ በባሕር ዳር፣ በሀላባ እና በአቢይ ኤርሳሞ ከተሞች እንደሚካሄዱ አወዳዳሪው አካል አሳውቋል፡፡ ይህም ክለቦች ደጋፊዎቻቸው ባሉባቸው እና በሚቀርቧቸው ከተሞች እንዲጫወቱ ያደርጋል፡፡ ይህ መሆኑ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ የጉዞ ዝግጅትን፣ የተጫዋቾችን አካላዊ ዝግጁነት እና የማገገሚያ ጊዜን በአግባቡ እንዲያግዙ ይረዳቸዋል፡፡

የዘንድሮው ውድድር ሜዳ ላይ የሚኖረው ፉክክር ብቻ አይደለም ትኩረት የሚስበው። ይልቁንስ የክለቦች የዝውውር እንቅስቃሴ፣ የተጫዋቾች ደመወዝ፣ የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ተሳትፎ እና የክለቦች የፋይናንስ አቅምም የውድድሩን አቅጣጫ ሊወስኑ እንደሚችሉ መረጃዎች አመልክተዋል። በተለይ በዝውውር ወቅቱ የታዩት ብዙ ፊርማዎች እና ከፍተኛ የደመወዝ ክፍያዎች የዘንድሮውን ሊግ የተለየ ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አቡበከር ናስር በደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከቆየ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለመቻል መፈረሙ ከዘንድሮው የዝውውር ገበያ ትልቅ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡ የእሱ መመለስ የመቻል ቡድንን የፊት መስመር ለማጠናከር እድል ሊፈጥር እንደሚችል ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ለ55 ቀናት ያህል ክፍት ሆኖ የቆየው የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት መቻል ብቻ ሳይሆን በርካታ ክለቦች ስብስባቸውን እንዲያጠናክሩ እድል ሰጥቷል፡፡ ከ140 በላይ አዳዲስ ዝውውሮች ተፈጽመዋል፤ ከ137 በላይ ተጫዋቾች ደግሞ ከነበሩበት ክለብ ጋር ውላቸውን እንዳራዘሙ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ከ40 በላይ የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ወደ ተለያዩ ክለቦች መቀላቀላቸውን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የማህበራዊ የትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዘንድሮው የዝውውር ገበያ ትልቅ እንቅስቃሴ ካሳዩ ክለቦች መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጠቀሳል፡፡ ክለቡ 11 የሀገር ውስጥ እና አራት የውጭ ሀገር ተጫዋቾችን በማስፈረም 15 አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡ በተጨማሪም የ15 ቁልፍ ተጫዋቾቹን ውል አራዝሟል፡፡ ባንኮች ለተጫዋቾች ዝውውር ያወጡት ገንዘብ በሜዳ ላይ ወደ ውጤት መቀየሩ ሂደት የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቡና 11 አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም ቅዱስ ጊዮርጊስ አስር፣ ባሕር ዳር ከተማ ዘጠኝ እና መቻል 10 ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል፡፡ ኢትዮጵያ መድን እና ሸገር ከተማ እያንዳንዳቸው 12 ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፡፡ ይህ የተጫዋቾች ዝውውር ክለቦች ለአዲሱ የውድድር ዘመን ያላቸውን ዝግጅት ያሳያል፡፡

ዋናው ጥያቄ ግን አዲስ የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር ምን ያህል በፍጥነት ይላመዳሉ የሚለው ነው፡፡ የተጫዋቾች ብዛትም የቡድን ጥራትን አይወስንም፡፡ ታዲያ ውጤታማ ለመሆን ብዙ ተጫዋቾችን ማስፈረም ብቻ ሳይሆን ስብስቡን በሚገባ ማዋሃድ፣ የተጫዋቾችን ሚና በግልጽ ማስቀመጥ፣ ጥሩ የቡድን መንፈስ መፍጠር እና ግልጽ የሆነ የአጨዋወት ስልት መከተል  ያስፈልጋል። በውድድር ዓመቱ  የመክፈቻ ጨዋታዎች አንዳንድ ያልተጠበቁ ውጤቶችን አስመዝግበዋል፡፡ አዲስ አዳጊው ሸገር ሲቲ በካሌብ በየነ ግብ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፏል፡፡

መቻልም በቢኒያም ተክሉ የ83ኛው ደቂቃ ግብ ሀዋሳ ከተማን ረቷል፡፡ አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክን፣ የኢትዮጵያ መድን ደግሞ ጋሞ ጨንቻን እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምረዋል፡፡

ባሕር ዳር ከተማም ከሜዳው ውጪ ወደ ሆሳዕና ተጉዞ ሀድያ ሆሳዕናን በአንተነህ ተፈራ ግብ አሸንፏል፡፡ ይህ ድል ለክለቡ ጠቃሚ ጅማሮ ሲሆን በተቃራኒው ለሀድያ ሆሳዕና በሜዳው ላይ ያጣው ነጥብ የውድድር ዓመቱን በጥንቃቄ እንዲጀምር የማንቂያ ደወል ይሆነዋል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች ሀላባ ከተማ እና ወልዋሎ ዓዲግራት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ነጌሌ አርሲ እንዲሁም ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ በአቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል፡፡

ይህ የመጀመሪያ ሳምንት ውጤት ብቻውን የዋንጫ ፉክክሩን ለመተንበይ ባይበቃም ባለፈው ዓመት ዋንጫውን ያነሳው ሲዳማ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መቻል፣ ባሕር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ከወዲሁ ለዋንጫ የታጩ ክለቦች  ናቸው፡፡

እነዚህ ክለቦች ለዋንጫ የሚኖራቸው እድል የሚወሰነው ግን ባላቸው የስብስብ ጥራት ብቻ ሳይሆን በተጫዋቾች ጤና፣ በአሠልጣኞች የጨዋታ ስልት፣ የቡድኑ መረጋጋት እና በጫና ውስጥ ውጤት በማስመዝገብ ብቃታቸው ጭምር ነው። አዲስ አዳጊዎች እና መሀል ሰፋሪ ክለቦችም ቀላል  ግምት  የሚሰጣቸው ክለቦች አይደሉም፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር በመጀመሪያው ሳምንት ባስመዘገባቸው ውጤቶች በአንዳንድ ክለቦች ላይ የወራጅነት ስጋት የሚያስነሱ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ በተለይም ወደ ሊጉ አዲስ ያደጉት ጋሞ ጨንቻ፣ አላባ ከተማ  እና  በመጀመሪያው ጨዋታ ውጤት ማስመዝገብ ያልቻሉ ክለቦች በቀጣይ መርሐ ግብሮች የሚያሳዩት አቋም ትኩረት ሳቢ ሆኗል፡፡

ጋሞ ጨንቻ የመጀመሪያ ጨዋታውን በኢትዮጵያ መድን ሁለት ለባዶ  በመሸነፍ መጀመሩ በቡድኑ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ ክለቡ ከፕሪሚየር ሊጉ የውድድር ደረጃና ፍጥነት ጋር ለመላመድ በቀጣይ ጨዋታዎች የተሻለ አቋም ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም የመከላከያ አደረጃጀቱን ማጠናከርና የሚፈጥራቸውን የግብ ዕድሎች በተሻለ ሁኔታ መጠቀም ለውጤቱ መሻሻል ወሳኝ ይሆናል፡፡

ሌላኛው አዲስ አዳጊ ክለብ አላባ ከተማ በሜዳው ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር አንድ አቻ በመለያየት አንድ ነጥብ አስመዝግቧል፡፡ በሜዳው ያገኘው ነጥብ ለቡድኑ ጥሩ ጅማሬ ቢሆንም በሊጉ ለመቆየት በቀጣይ ጨዋታዎች የውጤት ቀጣይነት ማሳየት ያስፈልገዋል፡፡ ለሁለቱም አዲስ አዳጊ ክለቦች የሊጉን ደረጃ መላመድ፣ የተጫዋቾችን ጥምረት ማጠናከር እና ነጥብ በተከታታይ ማስመዝገብ ዋነኛ ፈተናቸው ይሆናል፡፡

ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያ ጨዋታውን በአዳማ ከተማ አንድ ለባዶ ተሸንፏል፡፡ ክለቡ የቆየ የስፖርት ታሪክ ቢኖረውም በሊጉ የመቆየት ዕድሉ በሚያሳየው የውድድር አቋም ይወሰናል፡፡ በቀጣይ መርሐ ግብሮች የቡድን ጥምረቱን ማጠናከርና የግብ ዕድሎችን ወደ ውጤት መቀየር ካልቻለ በውድድሩ ውስጥ ከፍተኛ ፈተና ሊገጥመው ይችላል፡፡

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአላባ ከተማ ሜዳ አንድ አቻ በመለያየት አንድ ነጥብ ይዞ ውድድሩን ጀምሯል፡፡ ይህ ውጤት በጅማሬው ነጥብ ቢያስገኝለትም፣ በሊጉ ውስጥ የተረጋጋ አቋም ለመያዝ በቀጣይ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡

ባለፈው የውድድር ዘመን የወራጅነት ስጋት ውስጥ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናና ሀዋሳ ከተማ የዘንድሮውን ውድድር በአንድ ሽንፈት መጀመራቸው በክለቦቹ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ የመጀመሪያው ሳምንት ውጤት ብቻ የወራጅነት ስጋታቸውን ባያረጋግጥም በቀጣይ ጨዋታዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዘንድሮው የሊግ ውድድር ሰባት ክለቦች አሰልጣኝ ቀይረው መጀመራቸው ሌላው ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው፡፡ አዲስ አሰልጣኝ ወደ ቡድን ሲመጣ የጨዋታ ስልትን ለማስተዋወቅ እና ከተጫዋቾች ጋር የተረጋጋ ጥምረት ለመፍጠር ጊዜ ሊያስፈልገው ይችላል፡፡ ሆኖም በሊጉ ያለው የውድድር ጫና የተሻለ ውጤት በአጭር ጊዜ እንዲመጣ ይጠይቃል፡፡

በዘመናዊው እግር ኳስ የመረጃ አጠቃቀም፣ ተጫዋቾች  ሜዳ ላይ የሚሸፍኑት  ርቀት እና የታክቲክ ዝግጅት እየጨመሩ መጥተዋል። እነዚህ አቀራረቦች የጨዋታ ፍጥነትን፣ የቡድን ቅንጅትን እና የተጫዋቾችን አፈጻጸም ለማሻሻል እንደሚረዳ የጎል ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥም የታክቲክ ዝግጅት የሚኖረው ሚና ዘንድሮ ሊታይ እንደሚችል ይጠበቃል። ከዚህ ባሻገር የተጫዋቾች የግል ብቃት ፣ ፈጠራ፣ ውሳኔ  እና ፍጥነትም የጨዋታውን ውበት ሊወስኑ እንደሚችሉ አያጠያይቅም።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here