የጥበበኞቹ መክሰም

0
18

በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ እንደ “10 ቁጥር” ማሊያ ክብር እና ሞገስ ያገኘ ሌላ ቁጥር የለም። ይህ ቁጥር የቡድኑ የልብ ትርታ እና የፈጠራ ምንጭ ለሆኑ ተጫዋቾች የሚሰጥ ልዩ ማዕረግ ነበር። ይሁን እንጂ በዘመናዊ እግር ኳስ ይህ  ቁጥር እና የመለያው ሚና ተረት እየሆነ መጥቷል። ዚነዲን ዚዳን በምህታተኛ እግሮቹ በሜዳው ሲፈነጥዝ፣ ካካ በፈጣን እግሮቹ ሜዳውን ሲያቆራርጥ ወይም ሮናልዲንሆ በውብ ክህሎቱ ተከላካዮችን ሲያሸብር ያየ ትውልድ ዛሬ ላይ ትልቅ የባዶነት ስሜት ይሰማዋል።

በፈጠራ ብቃቱ የሚታወቀው ሜሱት ኦዚል በ2015/16 የውድድር ዘመን ለአርሰናል 19 ግብ የሆኑ ኳሶችን ሲያመቻች የነበረው አስደናቂ  እይታ የዚህ ሚና መደምደሚያ ይመስል ነበር። በዘመናዊው እግር ኳስ የታክቲክ አብዮት የ “10 ቁጥር” ሚና ውስጥ ሙሉ በሙሉ እየጠፋ መጥቷል። ይህ ለውጥ እግር ኳስ በጥበብ ከሚመራ ስፖርትነት ወደ ከባድ አካላዊ ፉክክር እና የቡድን ጨዋታ እንዴት እንደተሸጋገረ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ዘ ጋርዲያን አስነብቧል።

የ”10 ቁጥር” ሚና ከመደበኛ የእግር ኳስ ስልት በላይ የኪነጥበብ መገለጫ ሆኖ የኖረ ነው። እነ ዚነዲን ዚዳን እና ሁዋን ሮማን ሪኬልሜ ሜዳ ላይ ሲንቀሳቀሱ ጨዋታውን ሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ያደርጉት ነበር። የእነሱ ዋና ኃላፊነት መከላከል ወይም መሮጥ ሳይሆን ኳስ ሲያገኙ አስደናቂ የግብ እድሎችን መፍጠር ብቻ ነበር። ቡድኑ በሙሉ ለእነሱ ሽፋን ይሰጣቸዋል፤ እነሱ ደግሞ ጨዋታውን በጥበባቸው ያሸንፋሉ።

የቀድሞው የአርሰናል አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ሲናገሩ “ዘመናዊው እግር ኳስ ፍጥነትን እና አካላዊ ጥንካሬን በማስቀደሙ የ10 ቁጥር ተጫዋቾችን አጥፍቷቸዋል” ብለዋል። ይህ የታክቲክ አምባገነንነት ላለፉት ዐስር አመታት እግር ኳስን ከግለሰብ ክህሎት ይልቅ ወደ ቡድን ጨዋታ እንዲያደላ አድርጎታል። ለዚህ ደግሞ የፔፕ ጋርዲዮላ ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት እና የዩርገን ክሎፕ ተጭኖ የመጫወት ስልት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።

በዘመናዊ ታክቲክ የኋላ ክፍሉ በጣም ወደ መሃል ስለሚለጠጥ በተከላካይና በአማካኝ መካከል ያለው የቦታ ክፍተት ጠቧል። ይህ ደግሞ ለ10 ቁጥር ተጫዋች ኳስ ተቀብሎ የሚያስብበት አንድ ሴኮንድ እንኳ ፋታ አይሰጠውም። በተጨማሪም ዛሬ ላይ አጥቂዎችም ሆኑ አማካኞች ተከላካዮች ሆነዋል። ያለ ኳስ የማይሮጥ እና የማይከላከል ተጫዋች በአሰልጣኞች እንደ ሰነፍ ይቆጠራል።

ሜሱት ኦዚል ከአርሰናል ጋር  የተለያየው በክህሎት ችግር ሳይሆን በመከላከሉ  ስለማይሳተፍ  እንደሆነ የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አመልክቷል፡፡ የአውሮፓ ትልልቅ ቡድኖች የ 4-2-3-1 ስልትን ትተው ወደ 4-3-3 መቀየራቸውም ለዚህ ሚና መክሰም ሌላው ታክቲካዊ ምክንያት እንደሆነ የዘጋርዲያን መረጃ ይነግረናል።

በዚህ የአሰላለፍ ስልት ውስጥ የተለየ የ10 ቁጥር ቦታ የለም፤ ይልቁንም የመሃል አማካኞች ሜዳውን ከጫፍ እስከ ጫፍ በሩጫ እንዲሸፍኑ ይገደዳሉ። እንደ ዴክላን ራይስ ያሉ የዘመኑ የዘመኑ ተጫዋቾች በአማካይ በአንድ ጨዋታ እስከ 11 ኪሎ ሜትር የሚሮጡ ሲሆን ይህ ቁጥር ከሃያ አመት በፊት ከነበረው አማካኝ የሩጫ ርቀት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን መረጃዎች አስነብበዋል።

ይህ ማለት ግን የፈጠራ ጥበቡ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ማለት ሳይሆን ራሱን ለውጦ በሌላ ሚና ተተክቷል እያልን ነው። ዘመናዊው እግር ኳስ የ10 ቁጥርን ሚና ወደ ተለያዩ ቦታዎች አሰራጭቶታል። የመጀመሪያው ዝግመተ ለውጥ ወደ መሃል አማካኝ (Box-to-Box Playmaker) መለወጥ ነው። የዚህ ሚና ትልቁ ማሳያ ቤልጂየማዊው የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ ኬቨን ዲ ብሩይን ነው። ዲ ብሩይን የ10 ቁጥር ድንቅ ክህሎት ያለው ቢሆንም በአካላዊ ጥንካሬው እና ሜዳውን በሙሉ የሚሸፍንበት ብቃቱ ግን ከ10 ቁጥር ይለየዋል።

አዲሱን የ10 ቁጥር ሚና በሪያል ማድሪዱ ባለተሰጥኦ ጁድ ቤሊንግሃም እየተመለከትነው እንገኛለን። እሱ የፈጠራ ብቃትን እና ግብ የማስቆጠር ክህሎትን በአንድ ላይ ያዋሃደ ተጫዋች ነው። ሁለተኛው ለውጥ ደግሞ ብዙዎቹ  የ10 ቁጥር ጥበበኞች ከመሃል ተገፍተው ወደ ክንፍ (Inverted Winger) መውጣታቸው ነው። እንደ ማርቲን ኦዴጋርድ እና በርናርዶ ሲልቫ ያሉ ተጫዋቾች ከመሃል የሚደርስባቸውን ጫና ለመሸሽ ወደ ክንፍ ይወጣሉ፤ ከዚያ ኳስ ይዘው ወደ ውስጥ በመግባት እድሎችን ይፈጥራሉ።

አሁን ባለንበት የ2020ዎቹ አጋማሽ ደግሞ እንደ ጀማል ሙሲያላ እና ፍሎሪያን ቪርትዝ ያሉ ወጣት ተጫዋቾች የ 10 ቁጥር ክህሎትን ከከፍተኛ ፍጥነት ጋር በማዋሃድ አዲስ ተስፋ እየፈነጠቁ ይገኛሉ። ይህ የታክቲክ ዝግመተ ለውጥ ቡድኖችን ውጤታማ ቢያደርጋቸውም ከእግር ኳስ ላይ ግን ውበትን ቀምቷል።

የድሮው እግር ኳስ የተጫዋቾች ግለሰባዊ ነጻነት የሚታይበት እና ያልተጠበቁ አስደናቂ ክህሎቶች የሚስተናገዱበት መድረክ ነበር። ዛሬ ግን ጨዋታዎች በጥበብ ሳይሆን በዳታና በአካላዊ ጥንካሬ ላይ የተመሰረቱ ሆነዋል። አካዳሚዎች የሚፈልጉት ጥበበኛ ሳይሆን ሳይታክት የሚሮጥ እና እንደ ቡድን የሚስቡ ተጫዋቾችን ነው።

ይሁን እንጂ ይህ ለውጥ እግር ኳስን ይበልጥ ፈጣን እና ብዙ ግቦች የሚቆጠሩበት በማድረግ የራሱ የሆነ አዲስ ውበት አምጥቷል። ዛሬ ላይ ሁሉም ቡድኖች ተመሳሳይ የሮቦት መሰል የታክቲክ አወቃቀር ሲከተሉ ይህንን አሰልቺ መንገድ ሰብሮ ለመውጣት ድጋሚ የፈጠራ ብርሃን ማምጣቱ አይቀሬ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁመሉ።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here