ጤና ይስጥልን አንባቢያን! የዛሬው እንግዳችን አባት አርበኛ ዳኝነት አያሌው ናቸው፡፡ በመምህርነት፣ በዳይሬክተርነት፣ በወረዳ እና አውራጃ አስተዳድሪነት፣ በመምሪያ ሀላፊነት እና “የራዛ ዘመቻ” በሚባለው መንግሥታዊ ተልእኮ ደግሞ በአርበኝነት ሀገራቸውን ከ30 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ አያታቸው ፊታውራሪ መኮንን ከዓድዋ አርበኞች አንዱ ሲሆኑ አባታቸው ቢትወደድ አያሌው መኮንን ደግሞ በኢጣሊያ ወረራ ለአምስት ዓመታት የአቸፈርን፣ አለፋጣቁሳን እና የአካባቢውን አርበኞች አስተባብረው ጣሊያንን መውጫ መግቢያ ያሳጡ አርበኛ ነበሩ፡፡
የአርበኞቹ ልጅ አርበኛ ዳኝነት አያሌው ጡረታ ከወጡ በኋላም እንኳ እነሆ በ89 ዓመታቸው በኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር የአማራ ክልል ሊቀ መንበር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዛሬ በሀገር ፍቅር እና የሰንደቅ ዓላማ ክብር ላይ እንግዳ አድርገናቸዋል መልካም ንባብ!
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዜጐቿ ዕይታ እንዴት ይገለፃል?
ሰንደቅ ዓላማችን ብሔራዊ ኩራታችን ናት፤ ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያ ኩሩ ሕዝቦች መገለጫ ናት፤ ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያ ሕዝብ እኩልነት እና አንድነት መገለጫ ነች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰንደቅ ዓላማው ከፍተኛ ፍቅር እና አክብሮት አለው፡፡ ሀገር በተወረረበት ጊዜ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ሀገራቸውን ከውርደት ለማዳን ከየብሔረሰቡ ተወጣጥተው ወደ ጦር ግንባር በሚሄዱ ጊዜ ይህችን የሀገር ኩራት የሆነች ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርገው እያውለበለቡ ነው የሚጓዙት፡፡
ለምሳሌ ወደ ዓድዋ በዘመቱ ጊዜ ሰንደቅ ዓላማቸውን እያወለበለቡ ነው የሄዱት፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ከ1928 እስከ 1933 በነበረው የአርበኝነት ተጋድሏቸው ሰንደቅ ዓላማቸውን አንግበው ነው የተዋጉት፡፡ ዘማች ሰራዊት ድል አድርጐ በተመለሰ ቁጥር ሰንደቁን ከፍ አድርጐ እያውለበለበ፣ እየዘመረ እና እየፎከረ ነው የሚመጣው፡፡ ይህ ደግሞ ከጥንት አባቶቻችን ጀምሮ አሁን እስካለነው ልጆቻቸው ድረስ ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማችን ያለንን ከፍተኛ ፍቅር እና አክብሮት ያሳያል፤ የሰንደቅ ዓላማችን ፍቅር ከደማችን ጋር የተዋሀደ ነው፡፡
ቀደም ሲል የነበረው የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር እንዴት ይገለጽ ነበር?
ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማቸው ያላቸውን ፍቅር እና ክብር የሚያንፀባርቁባቸው በርካታ መንገዶች ነበሩ፤ አሉም፡፡ ለምሳሌ ከት/ቤቶች ብንጀምር በሁሉም የሀገራችን ዘመናዊ ት/ቤቶች ውስጥ ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ የውዴታ ግዴታ ሲሆን የመስቀል እና የማውረድ ሥርዓቱም ዘፈቀዳዊ ሳይሆን የት/ቤቶቹ ማህበረሰብ በሙሉ በተጠንቀቅ ቆሞ በኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ታጅቦ የሚፈፀም ነው፡፡
ይኸው ሥርዓት እንደ አዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ደብረማርቆስ፣ ጎንደር እና በመሳሰሉት ታላላቅ ከተሞችም በአብያተ መንግሥታት፣ በአደባባዮች እና በፖሊስ መምሪያ ጽ/ቤቶች ላይ ዘወትር ጧት እና ማታ ላይ ይከወናል፡፡ ሲከዎን ታዲያ ጥሩንባ አልያም ፊሽካ ሲነፋ ተሽከርካሪ ቆሞ፣ በበቅሎና ፈረስ ይጓዝ የነበረም ወርዶ፣ የተከናነበ ሰው ክንንቡን አውርዶ በተጠንቀቅ በመቆም ብሔራዊ መዝሙር ይዘምራል፡፡
ከዚህም ባለፈ ዛሬም ድረስ በተለይ በገጠሩ ክፍል ጐልቶ የሚስተዋለው በሠርግ ጊዜ ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ፣ በለቅሶ ጊዜም ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ፣ በተለያዩ ሃይማኖታዊ የንግሥ በዓላት ጭምር ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማችን ያለንን ክብር እና ፍቅር ፍንትው አድርጐ የሚያሳይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአፍሪካውያን ዘንድስ እንዴት ይታያል?
ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ቅኝ ያልተገዛችው ደግሞ በአጋጣሚ ወይም በተዓምር ሳይሆን ለሀገራቸው፣ ለዳር ድንበራቸው፣ ለሰንደቅ ዓላማቸው… ከማዋደቅ ወደ ኋላ የማይሉ አርበኛ ልጆች ስለ ነበሯት እና ስላሏት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይ አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት በተቀራመቱ ጊዜ ኢትዮጵያም ከቅኝ ገዥዎቹ አንዷ በሆነችው ፋሽሽት ኢጣሊያ ከመወረር አላመለጠችም ነበር፡፡
ይሁንና የማይበገሩት ኢትዮጵያውያን ድንበር ጥሶ የገባውን ከ300 ሺህ በላይ የፋሺሽት ኢጣሊያ ዘመናዊ ጦር በጋሻና ጦር እየተፋለሙ በግማሽ ቀን ጦርነት ድባቅ መትተው አድዋ ላይ ባስመዘገቡት ድል ለመላው አፍሪካውያን እና ቅኝ ተገዥ ሀገራት ሁሉ ድንቅ የነፃነት ተምሳሌት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ አናብስት ከ40 ዓመታት በኋላ የተፈፀመባቸውን የፋሽስት ኢጣሊያ ዳግም ወረራ በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ ማክሸፋቸውም የቅኝ ገዥዎችን ህልም ያኮላሸ እና መላ አፍሪካንም ለነፃነት ያነሳሳ አኩሪ ገድል ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት ሀገራችን የአፍሪካ ኩራት ሆና 15 ያህል ሀገራት የሰንደቅ ዓላማቸውን ቀለማት የነፃነት ተምሳሌት ከሆነችው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ጋር አመሳስለዋል፤ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ክብር አና ፍቅርም ገልፀውበታል፡፡
የሰንደቅ ዓላማችን ክብር እና ፍቅር ከዓለም አቀፍ አኳያስ ምን ያህል ነው?
ታሪክ የሚነግረን ብዙ ማሳያ አለ፤ ለምሳሌ ያህል ከ1914 እስከ 1918 (እ.አ.አ) በነበሩት ዓመታት ዓለም በሁለት ጐራ ተከፍሎ 1ኛውን የዓለም ጦርነት አካሄደ፤ በዚያ ጦርነት 10 ሚሊዮን ሰው ሲያልቅ ወደ 20 ሚሊዮን ያህል ደግሞ ቆሰለ፡፡ ጦርነቱ ሲጠናቀቅ እንደዚያ አይነት ህዝብ ጨራሽ አስከፊ ጦርነት ደግሞ እንዳይካሄድ ለማድረግ ድል አድራጊዎቹ ሀገራት ተሰባሰቡና ሊግ ኦፍ ኔሽንስ የተባለውን ማህበር አቋቋሙ፡፡ ያኔ ታዲያ ኢትያጵያ ነፃ ሀገር ነበረችና የማህበሩ አባል ሆና በመመዝገቧ ሰንደቅ ዓላማዋ ከሀያላኑ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ጋር እኩል መውለብለብ ቻለ፡፡
ከ1939 እስከ 1945 በተካሄደው 2ኛው የዓለም ጦርነትም አንድ መቶ አሥር ሚሊዮን የታጠቀ ሰራዊት በሁለት ጐራ ተሰልፎ በመጨፋጨፉ ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዘብ አለቀ፡፡ ጦርነቱ በ1945 ሲጠናቀቅ የአሁኑ የዓለም መንግሥታት ድርጅት (ዩናይትድ ኔሽን ተቋቋመ፤ ልክ በዓመቱ ይኸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን በለንደን ሲያካሂድ ኢትዮጵያም መሥራች አባል ሆና ተገኘች፡፡ ያኔ ግብጽም ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ወጥታ ስለነበር የጉባኤው አባል የመሆን እድል በማግኘቷ አፍሪካን ወክለው በጉባኤው የተሳተፉት ኢትዮጵያና ግብፅ ብቻ ሆነው ሰንደቅ ዓላማቸው በክብር ተውለብልቧል፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን በካረቢያን ደሴቶች ውስጥም ትልቅ ክብር አለው፤ ጀማይካውያን የሰንደቅ ዓላማችንን ቀለማት በሰንደቅ ዓላማቸው ብቻ ሳይሆን በባህላዊ ኮፍያዎቻቸውና አልባሳት ጭምር በመጠቀም ለኢትዮጵያና ሰንደቅ ዓላማዋ ያላቸውን ክብር እና ፍቅር አሳይተዋል፤ እያሳዩም ቀጥለዋል፡፡
ሰደንቅ ዓላማ የሀገር መታወቂያ እና የክብር ምልክት ነው ካልን በዜጐች ዘንድ ሊወደድ እና ሊከበር ይገባዋልና ይህ እውን እንዲሆን ከማን ምን ይጠበቃል?
“የሀገሩን ታሪክ የማያውቅ ከብዙ ሴቶች መካከል ያለች ወላጅ እናቱን መለየት የማይችል ህፃን ማለት ነው” የሚል የእውቅ ደራሲ ጽሁፍ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ትውልዱ የሀገሩን ታሪክ በሚገባ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ሀገር እዚህ የደረሰችው በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ አርበኞች መስዋእትነት ከፍለውላት መሆኑን ከተገነዘበ ሀገሩን ይወዳል፤ ሀገሩን የሚወድ ሰንደቋን ያከብራል፡፡
ታሪክን እና የሀገር ፍቅርን የማስተማር ኃላፊነት ደግሞ የት/ቤቶች እና የወላጅ ድርሻ ነው፡፡
እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(ጌታቸው ፈንቴ)
በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


