በአውሮፓ መካከለኛ ክፍል የምትገኘው ፕራግ የቼክ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ናት። በታሪካዊ ቅርሶቿ፣ በውብ ሕንፃዎቿ፣ በጥበብ ሥራዎቿ፣ በወንዞቿ እና በድልድዮቿ የምትታወቀው ይህች ከተማ የአውሮፓን የታሪክ ጉዞ ከሚያስረዱ አስፈላጊ ሥፍራዎች አንዷ ናት። በአንድ በኩል የመካከለኛውን ዘመን አሻራ በጥንቃቄ ይዛ ስትታይ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመናዊ ከተማ ሕይወትን፣ የሳይንስ እድገትን፣ የኪነጥበብ ፈጠራንና የቱሪዝም እንቅስቃሴን በአንድ ላይ አስተናግዳለች።
ፕራግ በብዙዎች ዘንድ “የመቶ ማማዎች ከተማ” በሚል መጠሪያ ትታወቃለች። ይህ ስያሜ ከተማዋን ከሩቅ ሲመለከቱ የሚታዩትን የቤተ ክርስቲያን ማማዎች፣ የጥንት ሕንፃዎችን ጣሪያዎች እና የታሪካዊ ሕንፃ ግንባታዎችን ውበት ያመለክታል። በተለይም በቭልታቫ ወንዝ ላይ የተዘረጉ ድልድዮች፣ በወንዙ ዳርቻ የተሰሩ የታሪክ ሕንፃዎችና ከፍ ብለው የሚታዩ ማማዎች ለከተማዋ ልዩ ገጽታ ይሰጧታል።
ከተማዋን ለሁለት የሚከፍለውና በታሪኳ ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወተው ቭልታቫ (Vltava) የተባለው ወንዝ ነው። ወንዙ በከተማዋ መሃል እየተጠማዘዘ ሲፈስ በዳርቻዎቹ የተገነቡት ታሪካዊ ሕንፃዎችና ድልድዮች የፕራግን የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ ውበት በአንድ ላይ ያሳያሉ።
ፕራግ የቼክ ሪፐብሊክ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የትምህርት፣ የባህልና የቱሪዝም ማዕከል ናት። የቼክ ሪፐብሊክ መንግሥትና ፓርላማ መቀመጫ ከመሆኗ በተጨማሪ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሙዚየሞች፣ ቲያትር ቤቶች፣ የሙዚቃ ማዕከላትና የንግድ ተቋማትም ይገኙባታል።
የከተማዋ ልዩ ገጽታ ከታሪካዊ ሕንፃዎች ብቻ አይመነጭም። አረንጓዴ ፓርኮቿ፣ የእግረኛ መንገዶቿ፣ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎቷ ሁሉ ለውበቷ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። የተለያዩ ባህሎች የሚገናኙባት ዓለም አቀፍ መዳረሻም ሆናለች። የፕራግ ታሪክ አንድ ሺህ ዓመትን ተሻግሯል።
በመካከለኛው ዘመን ፕራግ የቦሄሚያ መንግሥት ዋና ማዕከል ሆነች። ንግድ እየተስፋፋ፣ ከተማዋም እየተለወጠች ስትሄድ፣ አዳዲስ ሰፈሮች፣ ቤተ ክርስቲያናት፣ ድልድዮችና የአስተዳደር ሕንፃዎች ተገነቡ። ከአውሮፓ የተለያዩ ክፍሎች የመጡ ነጋዴዎች፣ ምሁራንና አርቲስቶች በከተማዋ ውስጥ መስፈራቸውም የባህል ልውውጥን አጠናከረ።
የፕራግ ታሪክ ከተለያዩ የአውሮፓ የፖለቲካ ለውጦች ጋር ተያይዞ የዘለቀ ነው። ከቦሄሚያ መንግሥት ዘመን ጀምሮ እስከ ቅዱስ የሮማ ግዛት፣ ከሃብስበርግ ሥርወ መንግሥት አገዛዝ እስከ ዘመናዊ ቼክ ሪፐብሊክ ድረስ፤ ከተማዋ ብዙ የታሪክ ምዕራፎችን አሳልፋለች። እነዚህ ለውጦች በሥነ ሕንፃዋ፣ በሃይማኖታዊ ተቋማቷ፣ በቋንቋዋና በባህላዊ ልማዶቿ ላይ የሚታዩ አሻራዎችን አስቀርተዋል።
የፕራግ ካስትል (Prague Castle) ከከተማዋ ታዋቂ መለያዎች አንዱ ነው። ይህ ሰፊ የቤተ መንግሥት፣ የሃይማኖት፣ የአስተዳደርና የታሪክ ሕንፃዎች ስብስብ ከተማዋን ከፍ ብሎ በሚመለከት ሥፍራ ይገኛል። በታሪክ ውስጥ የቦሄሚያ ነገሥታት፣ የቅዱስ የሮማ ግዛት ንጉሠ ነገሥታትና የተለያዩ የቼክ መሪዎች የሥልጣን ማዕከል ሆኖ አገልግሏል።
የካስትሉ የሕንፃ አቀማመጥ የተለያዩ ዘመናትን ያካትታል። ጎቲክ፣ ሮማኒስክ፣ ረነሳንስና ባሮክ የሥነ ሕንፃ ጥበቦች በአንድ ሥፍራ ተዋህደው ይታያሉ። ይህም በከተማዋ ውስጥ የተካሄዱትን የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የጥበብ ለውጦችን በአካል የሚያሳይ ሙዚየም እንደሆነ ያስቆጥረዋል።
በካስትሉ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ቪቱስ ካቴድራል (St. Vitus Cathedral) የከተማዋ ከፍተኛ የሥነ ሕንፃ ስኬቶች መገለጫ ነው። በረጃጅም ማማዎቹ፣ በተዋቡ የቀለም መስታወቶቹ፣ በድንጋይ ላይ በተቀረጹ ሥዕላዊ ጌጦቹና በሰፊው የውስጥ አዳራሹ የሚታወቀው ይህ ካቴድራል፣ የቼክ ሕዝብን ሃይማኖታዊና ብሔራዊ ታሪክ ይወክላል።
ካስትሉ ዛሬም የቼክ ፕሬዚዳንት ዋና የሥራ ማዕከል ከሚገኝባቸው ሥፍራዎች አንዱ ነው። በዚህ ምክንያት የጥንት ዘመንን የሚወክል ቅርስ ብቻ ሳይሆን፣ የዘመናዊ መንግሥት ተቋም ማዕከልም ነው።
የቻርልስ ድልድይ (Charles Bridge) በቭልታቫ ወንዝ ላይ የተገነባ የጥንት ድንጋይ ድልድይ ሲሆን ከፕራግ በጣም ዝነኛ የታሪክ ቅርሶች አንዱ ነው። ድልድዩ በንጉሥ ቻርልስ አራተኛ ዘመን በአሥራ አራተኛው መቶ ዓመት የተገነባ ነው።
ድልድዩ በረጅም የድንጋይ መስመሩና በሁለቱ ጫፎቹ ባሉት የታሪክ ማማዎች ይታወቃል። በላዩ የተቀመጡት የቅዱሳን ሐውልቶችም ለሥነ ጥበብ ውበቱ ተጨማሪ ድምቀትን ይሰጣሉ። እነዚህ ሐውልቶች የክርስትናን ታሪክ፣ የአውሮፓን የሐውልት ጥበብና የታሪካዊ ማስታወሻ ባህል ያንጸባርቃሉ።
በፕራግ ውስጥ የሚገኘው ጆሴፎቭ (Josefov) የተባለው የአይሁድ ታሪካዊ ሰፈር፣ የአውሮፓ የአይሁድ ማኅበረሰብ ታሪክን ለመረዳት አስፈላጊ ሥፍራ ነው። በዚህ አካባቢ ጥንታዊ ምኩራቦች፣ ታሪካዊ መቃብርና የባህል ማስታወሻዎች ይገኛሉ።
የአይሁድ ማኅበረሰብ በፕራግ ውስጥ ለብዙ ዘመናት ኖሯል። የንግድ፣ የሃይማኖት፣ የሥነ ጽሑፍና የአእምሯዊ ሕይወት አስተዋጽኦውም በከተማዋ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ አለው።
በፕራግ ከተማ የሚገኘው የጥንታዊው አዲስ-አሮጌ ምኩራብ (Old-New Synagogue) በአውሮፓ ከሚገኙ ጥንታዊ ምኩራቦች መካከል አንዱ ነው። ይህ ሕንፃ የአይሁድን ሃይማኖታዊ ባህልና የረጅም ዘመናት ቀጣይነት ይወክላል። በአካባቢው የሚገኙት ታሪካዊ ቦታዎችም የሰው ልጅ ልዩነትን ማክበርና ከታሪክ መማር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስታውሳሉ።
ፕራግ በዚህ መልኩ የአንድ ሕዝብ ታሪክ ብቻ የምትወክል ከተማ አይደለችም። የቼክ፣ የጀርመንና የአይሁድ ማኅበረሰቦች በተለያዩ ዘመናት በከተማዋ ሕይወት ውስጥ የነበራቸው ሚና የብዙ ባህሎች መገናኛ መሆኗን ያሳያል።
ከከተማዋ ጋር በጥልቅ የተያያዘው የሥነ ጽሑፍ ሰው ፍራንዝ ካፍካ (Franz Kafka) ነው። ካፍካ በፕራግ ተወልዶ ያደገ ሲሆን በዘመናዊ ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ ብቸኝነት፣ የቢሮክራሲ ጫና፣ የማንነት ጥያቄና የሕይወት እንግዳነትን የሚያሳዩ ሥራዎችን ጽፏል። ሥራዎቹ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉመው በዓለም ዙሪያ ይነበባሉ። የካፍካ ስም ዛሬም ከፕራግ የባህል መለያዎች አንዱ ነው።
በከተማዋ የሚገኙት የኦፔራ ቤቶች፣ የሙዚቃ አዳራሾች፣ ቲያትሮችና የሥነ ጥበብ ማዕከላት የባህል ሕይወቷን ያበለጽጋሉ። በተለይም የክላሲካል ሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ የጃዝ ዝግጅቶችና የዘመናዊ ሥነ ጥበብ ኤግዚቢሽኖች ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ሰፊ የባህል ምርጫ ይሰጣሉ።
ፕራግን ከሌሎች ከተሞች የሚለያት ቁልፍ ባህርይ ከተለያዩ ዘመናት የመጡ የሥነ ሕንፃ አሻራዎች በአንድ ላይ መኖራቸው ነው። የሮማኒስክ ዘመን ቅርሶች፣ የጎቲክ ማማዎች፣ የረነሳንስ ቤተ መንግሥቶች፣ የባሮክ ሕንፃዎች፣ የአርት ኑቮ ጌጣጌጦችና የዘመናዊ ሕንፃ ንድፎች በከተማዋ ውስጥ በቅርብ ርቀት ይገኛሉ።
የጎቲክ ሥነ ሕንፃ ረጃጅም ማማዎችን፣ ሹል ቅስቶችንና ወደ ላይ የሚያመሩ ቅርጾችን ይጠቀማል። በፕራግ ውስጥ የሚታዩት እነዚህ ቅርጾች የሃይማኖታዊ ሕንፃዎችን ክብርና የጥንት ሠራተኞችን የግንባታ ብቃት ያሳያሉ። የባሮክ ሕንፃዎች ደግሞ የተጠማዘዙ ቅርጾችን፣ የተዋቡ ጌጦችንና ከፍተኛ የውበት አገላለጾችን ያካትታሉ።
በከተማዋ ውስጥ የዘመናዊ ሥነ ሕንፃ ምሳሌዎችም ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል በቭልታቫ ወንዝ ዳርቻ የሚገኘው ዳንሲንግ ሃውስ (Dancing House) ተጠቃሽ ነው። ይህ ሕንፃ በተለየ የተጠማዘዘ ቅርጹ ከጥንታዊ ሕንፃዎች የተለየ መልክ ይዞ ይታያል። የድሮና የአዲስ የሥነ ሕንፃ አሻራዎች አብረው መኖራቸው ፕራግ በታሪክ ውስጥ የቆመች ከተማ ሳትሆን በየዘመኑ እየተለወጠች የምትሄድ ሕያው መሆኗን ያሳያል።
በ1992 እ.አ.አ የፕራግ ታሪካዊ ማዕከል በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተመዘገበ። ይህ እውቅና ከተማዋ በሥነ ሕንፃ፣ በከተማ እድገትና በታሪካዊ ቀጣይነት ያላትን ልዩ እሴት ያረጋግጣል።
ቱሪዝም ለፕራግ ኢኮኖሚ ወሳኝ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከተማዋ በታሪካዊ ቅርሶቿ፣ በሙዚየሞቿ፣ በሙዚቃ ዝግጅቶቿ፣ በአረንጓዴ ሥፍራዎቿና በልዩ የከተማ ገጽታዋ ምክንያት ከዓለም የተለያዩ ክፍሎች ጎብኚዎችን ትስባለች።
ፕራግ ታሪክን በሙዚየም ውስጥ ብቻ አታስቀምጥም፤ በጎዳናዎቿ፣ በድልድዮቿ፣ በአደባባዮቿና በሕንፃዎቿ ውስጥ የሚነበብ ታሪክ አድርጋ አቆይታለች። የቻርልስ ድልድይ የጥንት የግንባታ ጥበብን ያስታውሳል፤ የፕራግ ካስል የፖለቲካና የመንግሥት ታሪክን ይወክላል፤ የአይሁድ ሰፈር ደግሞ የባህል ብዝሃነትንና ከታሪክ የሚወሰደውን ትምህርት ያስታውሳል።
ፕራግ የቼክ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን፤ የአውሮፓን ታሪክ፣ የሥነ ሕንፃ እድገት፣ የሳይንስ፣ ታሪክና የኪነጥበብ ብልጽግና በአንድ ላይ የምታሳይ ድንቅ ከተማ ናት። የቭልታቫ ወንዝ፣ የቻርልስ ድልድይ እና የፕራግ ካስል፣ የድሮዋ ከተማ አደባባይ የከተማዋን ልዩ ገጽታ ከሚያሳዩ ታዋቂ ምልክቶች መካከል ናቸው።
የቼክ ሪፐብሊክ ብሔራዊ የቱሪዝም ድርጅት፣ የቼክ ሪፐብሊክ የዩኔስኮ ኮሚሽን እና የፕራግ ከተማ የጎብኝዎች ድረገጾችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።
****
ቼክ ሪፐብሊክ
ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ
ቼክ ሪፐብሊክ በመካከለኛው አውሮፓ ትገኛለች። በምዕራብ ከጀርመን፣ በሰሜን ከፖላንድ፣ በምሥራቅ ከስሎቫኪያ፣ በደቡብ ደግሞ ከኦስትሪያ ጋር ትዋሰናለች። ወደ ባሕር የማትወጣ አገር (Landlocked Country) ናት።
መሠረታዊ መረጃዎች
የአገሪቱ ስም ቼክ ሪፐብሊክ (Czech Republic) ሲሆን በአጭሩ ቼኪያ (Czechia) ተብላም ትጠራለች። ዋና ከተማዋ ፕራግ ናት። የመሬት ስፋቷ 78,871 ካሬ ኪሎ ሜትር ነው። የሕዝብ ብዛቷ 10.9 ሚሊዮን ደርሷል። ይፋዊ ቋንቋዋ ቼክኛ (Czech) ሲሆን፤ የምትጠቀመው ገንዘብ ደግሞ የቼክ ክሮና (Czech Koruna — CZK) ነው።
የመንግሥት ሥርዓቷ የፓርላማ ሪፐብሊክ ሲሆን፤ አገሪቱ በአስተዳደር ወደ 14 ክልሎች ተከፋፍላለች።
ታሪካዊ መገለጫዎች
የቼክ ሪፐብሊክ ታሪክ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ከቦሄሚያና ሞራቪያ ክልሎች ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ ክልሎች ለአገሪቱ የፖለቲካ፣ የባህልና የኢኮኖሚ ምስረታ አስፈላጊ ሚና ተጫውተዋል።
እ.ኤ.አ. በ1918 ከኦስትሪያ-ሃንጋሪ ግዛት መፍረስ በኋላ ቸኮዝሎቫኪያ (Czechoslovakia) የተባለች አገር ተመሠረተች። በ1948 ኮሚኒስት አገዛዝ ሥልጣን ያዘ። በ1968 ደግሞ የፕራግ ጸደይ (Prague Spring) በመባል የሚታወቀው የፖለቲካ ለውጥ ሙከራ ተካሄደ። ይህ ሙከራ በሶቪየት መራሹ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ተገታ።
በ1989 እ.አ.አ በተካሄደው ቬልቬት አብዮት (Velvet Revolution) የኮሚኒስት አገዛዝ ተጠናቀቀ። በጥር 1 ቀን 1993 ቸኮዝሎቫኪያ በሰላማዊ ሁኔታ በሁለት ነፃ አገሮች ተከፈለች፤ እነሱም ቼክ ሪፐብሊክና ስሎቫኪያ ናቸው።
(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


