የባሕር በር ለኢትዮጵያ የኅልውና ጥያቄ ነው!

0
2

ኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት ታሪኳ እንደሚመሰክረው የተለያዩ የባሕር በሮች ባለቤት የነበረች ታላቅ ሀገር ናት። በቀይ ባሕር አካባቢ የነበሯት የባሕር በሮች በቀደሙት የአክሱም እና የዛጉዌ እንዲሁም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ምሥረታ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ የንግድ፣ የባሕል፣ የፖለቲካ … ግኑኝነቷ ዋነኛ መደላድል ሆነው ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል። የባሕር በሮቿ ኢትዮጵያ ከቀሪው ዓለም ጋር በቀላሉ እንድትገናኝ፣ ምጣኔ ሀብቷ እንዲጎለብት እና የጥንታዊ ሥልጣኔዋ መልካም ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶ እንዲወጣ ሁነኛ ሚና ተጫውተዋል።

ይህ የባሕር በር ባለቤትነቷ ለኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ከማንም ያገኘችው ሥጦታ ሳይሆን በተፈጥሯዊ አቀማመጧ ያገኘችው እንደሆነ ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ በዚህ ተፈጥሮ ባደላት አቀማመጥ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤት ሆና ረዥም ዘመናትን እንዳሳለፈች ታሪክ የሚመሰክረው እውነታ ነው።

ይሁን እንጂ፣ ይህን ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መብት በሂደት በተፈጠሩ ውስጣዊ እንዲሁም ውጫዊ ፖለቲካዊ ሴራዎች፣ ፍትሐዊ ባልሆኑ የተናጠል የጂኦፖለቲካ ውሳኔዎች እና ተገቢነት በሌላቸው ርምጃዎች ተነፍጋ ቆይታለች። ሀገራችን  ፍትሐዊነት፣ ግልጽነት እና ሕጋዊነት በሌላቸው ሴራ የወለዳቸው ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የወደብ ባለቤትነት መብቷን እንድታጣ መደረጓ ታሪክ ይቅር የማይለው ትልቅ ስህተት ነበር።

ኢትዮጵያ በተለይም የ1983 ዓመተ ምሕረትን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ወደብ አልባ መሆኗ በምጣኔ ሀብት ዕድገቷ፣  በደኅንነቷ እና በዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ…  ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

በየዓመቱ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ለወደብ ኪራይ የምታወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ  ለከፍተኛ የምጣኔ ሀብት  ጫና ዳርጓታል፡፡ ፍትሐዊ እንዲሁም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የባሕር በር ማጣቷ  ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ትልቋ ሀገር ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር ለልማቷ እና ዕድገቷ የሚመጥን  እንቅስቃሴ እንዳታደርግ  እንቅፋት ሆኖባት ኖሯል።

ኢትዮጵያ ሕጋዊ እና ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ የባሕር በር ማጣቷ በእጅጉ እንደጎዳት እንዲሁም ይህን ያጣችውን የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳላት የተረዳው የኢትዮጵያ መንግሥትም ኢትዮጵያ ያላግባብ ያጣቻቸውን የባሕር በሮች እንድታገኝ  ሕጋዊ እና ፍትሐዊ ጥያቄ በማቅረብ እንዲሁም  ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይህ የባሕር በር የማግኘት  ጥያቄም ሆነ እንቅስቃሴ የአንድ አካል ወይም የወቅቱ መንግሥት ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡ ይህ የባሕር በሮቿን የማግኘት ጥያቄ  የትውልድን ጥያቄ የሚመልስ፣ የኢትዮጵያን  ዘላቂ ጥቅም እንዲሁም ሕልውና የሚያረጋግጥ፣ የታሪክ ስህተትን የሚያርም፣ ሊደገፍና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግና መርህ መሠረት ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር የማግኘት መብቷ እንዲከበር በቁርጠኝነት  የምታደርገው ጥረት  ፍጹም ፍትሐዊ እንዲሁም ሕጋዊ  ጉዳይ ነው።

በመሆኑም መንግሥት እያደረገ ያለው የባሕር በርን የማስመለስ  ትግል ሕጋዊ፣ ታሪካዊ እና ፍትሐዊ እንደመሆኑ መጠን በምንም ዓይነት ሁኔታ ወደ ጎን ሊባል አይገባውም፤ ጥረቱንም አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡  ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ  ምሁራን የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የኅልውና እና የፍትሕ ጥያቄ  መሆኑን ተረድተው ኢትዮጵያ የባሕር በር ታገኝ ዘንድ  ከመንግሥት ጎን  በመቆም የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ያጣቻቸውን ወደቦቿን ማስመለስና የባሕር በር ባለቤት መሆን ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መብቷ በመሆኑ ይህን መብት ለማስከበር የሚደረገው ትግል ለአፍታም ቢሆን ቸል ሳይባል ተጠናክሮ  መቀጠል ይኖርበታል!

በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here