የሳንባ ምች ምንነት እና መከላከያዎቹ

0
139

የሳንባ ምች በዓለም ላይ በዓመት ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሕይወት ያሳጣል::  በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት ተላላፊ የሞት መንስኤም ሆኖ ተመዝግቧል:: የሳንባ ምች ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በበለጠ ሕጻናትን ይገድላል:: በዓለም ደረጃ በየዓመቱ ከ 700ሺህ በላይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ሕይዎት እንደሚቀጥፍ ዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሕዳር 2025 ባወጣው መረጃ አስታውቋል::

መረጃው እንደሚያመላክተው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ሕፃናት ላይ በሳንባ ምች ምክንያት የሚደርሰውን ሞት በመቀነስ ረገድ ያለው እድገት ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች አንፃር ሲታይ በጣም አዝጋሚ ነው::

 

ለመሆኑ ሳንባ ምች ምንድን ነው?

በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ፣ የሳንባ እና የጽኑ ሕሙማን ሕክምና ሳብ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ብሩክ ሙላት ስለ ሳንባ ምች ሕመም ምንነትና መከላከያዎቹ ለበኵር ጋዜጣ ማብራሪያ ሰጥተዋል:: ዶ/ር ብሩክ እንዳስረዱት የሳንባ ምች ወይም ኒሞኒያ (Pneumonia) ሳንባ በተለያዩ ጥቃቅን ሕዋሳት ሲጠቃ የሚከሰት በሽታ ነው:: ይህንን በሽታ የሚያመጡት በዋናነት ሳንባን በሚያጠቁ ባክቴሪያ እና ቫይረስ ሕዋሳት አማካኝነት ነው::

የሳንባ ምች  የሳንባ አየር ከረጢቶች (alveoli) በፈሳሽ ወይም በንፍጥ እንዲሞሉ ያደርጋል:: ይህ ሁኔታ ሳል፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ የትንፋሽ ማጠር እና የደረት ሕመም ያስከትላል:: በተለይ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው የደከሙ ሰዎችን ክፉኛ ያጠቃል:: በሽታው  እንደ መንስኤው በአንቲባዮቲክስ ወይም በፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ይድናል::

የሳንባ ምች ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ አጋጠሚ ያለው ሲሆን እርጥበት አዘል በሆነ አየር ውስጥም ይተላለፋል:: ሌላው  ከሆድ፣ ፣ከጉሮሮ እና  ከአፋ የሚወጡ ተኅዋሲያን ወደ ሳንባ የመውረድ እድል ይኖራቸዋል፤ ወደ ሳንባ ከወረዱ በኋላ ሳንባችን ውስጥ ይራባሉ::  በዚህ ጊዜ የሰውነታችን የበሽታ ተከላካይ ስርዓቱ ለዚህ ወረራ የሰጠው ከፍተኛ ምላሽ በአየር ከረጢቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ እብጠት ያስከትላል፤ በዚህም ምክንያት ሕመም፣ ፈሳሽ  መጨመር እና የመተንፈስ ችግር ያስከትላል::

 

እነማን ተጋላጭ ናቸው?

ዶ/ር ብሩክ እንደሚሉት የሳንባ ምች በአብዛኛው የሚያጠቃው ሕጻናትን እና በእድሜያቸው ከፍ ያሉ ሰዎችን ነው:: በተለይም እድሜያቸው ከ65 እና  ከዛ በላይ የሆናቸው ሰዎች ለሳንባ ምች የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው:: ከዛ ውጪ ጉንፋን ፣ የተለያየ የመተንፈሻ አካል  በሽታ እና  ተጓዳኝ ከበድ ያለ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች  ለሳንባ ምች የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው:: ለአብነትም የስኳር ታካሚዎች፣ ስር የሰደደ የኩላሊት ሕክምና የሚያደርጉ፣ የኤች አይቪ ታካሚዎች እንዲሁም ደግሞ የተለያዩ የሳንባ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ለሳንባ ምች በቀላሉ ተጋላጭ ይሆናሉ::

አስም እና የቆየ የሳንባ ጠባሳ ያለባቸው ሰዎችም በቀላሉ ባክቴሪያዎች እና ቫይረሶች ሳንባቸው ላይ ኢንፌክሽን የመፍጠር እና የበሽታ ምልክት የማምጣት እድል ይኖራቸዋል::

የሳንባ ምች ምልክቶች

ዶ/ር ብሩክ እንደሚሉት ምልክቶቹ ከቀላል እስከ ከባድ ሊደርሱ ይችላሉ:: የሳንባ ምች ሲከሰት  የመጀመሪያው ምልክት ሳል ነው፤ ሳሉ አክታ ያለው ሊሆን ይችላል፤ የአክታው አይነትም ከሰው ሰው ሊለያይ ይችላል:: አንዳንዴ ደም የመቀላቀል ሁኔታ ሊኖር ይችላል:: ነጭ ወይም ቢጫ አክታ ሊሆንም ይችላል:: በዋናነት ከፍ ያለ ትኩሳት አለው:: የሰውነት መቆራረጥ፣ ጥሩ ስሜት አለመሰማት፣ ድካም፣ የደረት ሕምም፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ ትንፋሽ ማጠር እና የመሳሰሉ ምልክቶችም ሊኖሩት ይችላሉ:: እንዲሁም በጨቅላ ሕጻናት እና ልጆች ላይ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ማስታወክ፣ የኃይል እጥረት፣ብስጭት ወይም እረፍት ማጣት  ሊታይባቸው ይችላል:: ብዙ ጊዜ የሳንባ ምች ምልክቶች ከ14 ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ::

ሕክምናዎቹ

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ አንድ ሰው የሳንባ ምች እንዳለበት  የሚታወቀው በምርመራ ብቻ ነው:: ግለሰቡ ምልክቶቹ ከታዩበት በኋላ በዋናነት የራጅ እና የደም ምርመራ ያደርጋል::  አንዳንዴም የአልትራ ሳውንድ ምርመራዎች ሊታዘዙለት ይችላሉ::

በመሆኑም ሕክምናው ባለበት የሕመም ደረጃ ይወሰናል:: በጣም ከፍ ያለ ኦክስጅን የሚፈልግ ፣ ከፍ ያለ ትኩሳት ያለው ግለሰብ ሕመሙ ከሳንባ አልፎ ኩላሊትን ስለሚጎዳ  በሕክምና ተቋማት ተኝቶ እንዲታከም ይደረጋል:: ተኝቶ መታከም የማያስፈልገው ከሆነ ደግሞ በሚዋጡ መድሃኒቶች ይታከማል:: የበሽታው ምልክቶች እንደታዩ ቀደም ብሎ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ መታከምም ከበሽታው በፍጥነት ለመዳን ይረዳል::

 

መከላከያዎቹ

በዋናነት የሳንባ ምችን የምንከላከለው አልኮልን በማስወገድ፣ የስኳር ታማሚዎች ስኳር መድኃኒታቸውን በትክክል በመውሰድና መጠኑን በማስተካከል፣ ደካማ የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ያላቸው እንዲሁም ኤች አይቪ ኤድስ በደማቸው የተገኘባቸው የሰውነታቸውን በሽታ የመከላከል አቅም በመገንባት ለነዚህ ባክቴሪያዎች እና ቫይረሶች ላለመጋለጥ ጥንቃቄ ማድረግ ይችላሉ::

ዶ/ር ብሩክ እንዳስረዱት በጊዜ ያልታከመ የሳንባ ምች የሚያስከትላቸው ጉዳት ከፍተኛ ነው:: ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የሳንባ ምች  በቀላሉ አየር ለማስወጣት እና ለማስገባት ስለሚያስቸግር ለመተንፈስ የሚረዱ አጋዥ የሕክምና  መሳሪያዎች ያስፈልጉታል:: በተጨማሪም ባክቴሪያው ወደ ደም በመሄድ የኩላሊትን ሥራ ሊያዛባ ይችላል:: ልብ ላይም ጫና ሊፈጥር ይችላል፤ ከዚያም ባለፈ ሕይዎትን ሊነጥቅ ይችላል:: በመሆኑም  ማሕበረሰቡ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል::

 

መረጃ

 

ሳንባ ምች

  • ሰዎች ለመተንፈስ ሲቸገሩ፣ በከንፈራቸው እና በጣታቸው ላይ ሰማያዊ ቀለም ሲያዩ፣ የደረት ሕመም ሲኖራቸው፣ ከፍተኛ ትኩሳት ወይም ፈሳሽ ያለው ሳል ሲያጋጥማቸው በፍጥነት የሕክምና ርዳታ ማግኘት እንዳለባቸው  የአሜሪካ የሳንባ ማኅበር መረጃ ይጠቁማል፡፡
  • የሳንባ ምች በተለያዩ መንገዶች ሊሰራጭ ይችላል፡፡ በልጆች አፍንጫ ወይም ጉሮሮ ውስጥ በብዛት የሚገኙት ቫይረሶች እና ባክቴሪያዎች ወደ ውስጥ ከገቡ ሳንባን ሊበክሉ ይችላሉ፡፡
  • ሳንባ ምች ከታመሙ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት ውስጥ ይሻላቸዋል፡፡
  • ክትባቶች በሳንባ ምች ባክቴሪያ ወይም በጉንፋን ቫይረስ የሚመጣውን የሳንባ ምች ለመከላከል ይረዳሉ፡፡ ንጽሕናን (እጅን አዘውትሮ መታጠብ)፣ መጠበቅ፣ ማጨስን ማቆም እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል ሥርዓትን መገንባት፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እና ጤናማ አመጋገብን መከተል በሳንባ ምች የመያዝ አጋጣሚን ይቀንሳሉ፡፡

ምንጭ፡- unicef.org/t፣ ቢቢሲ ፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here