የማይበገረዉ  ታይገር

0
92

ጎልፍ ለዘመናት በጸጥታ፣ በተረጋጋ እርምጃ እና በሹክሹክታ የሚከናወን የሀብታሞች መዝናኛ ተደርጎ ይቆጠር እንደነበር የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ ነገር ግን እ.አ.አ በ1990ዎቹ አጋማሽ ይህን በድንገት የሰበረ አንድ ትልቅ አውሎ ንፋስ ብቅ አለ፤ ስሙም ታይገር ውድስ ይባላል፡፡ የታይገር ውድስ የጎልፍ ስፖርት ስኬት ዋንጫዎችን መሰብሰብ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የራሱን ስፖርት ሕግጋት እስከመቀየር፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾችን ከወንበራቸው እስከማስነሳት እና መላውን ዓለም በአንድ የጎልፍ ዱላ እስከማስተዳደር የደረሰ አስገራሚ ታሪክ ነው፡፡

ማይክል ጆርዳን በቅርጫት ኳስ፣ ሙሀመድ አሊ በቡጢ ስፖርት እና ፔሌ በእግር ኳስ ያመጡት ዓይነት መዋቅራዊ ለውጥ እና የበላይነት ታይገር ውድስ በጎልፍ ስፖርት ላይ አምጥቷል፡፡ እ.አ.አ በ1996 ታይገር ውድስ ወደ ፕሮፌሽናል የጎልፍ ዓለም ሲቀላቀል ሄሎ ዓለም በሚል ቃል ነበር ራሱን ያስተዋወቀው፤ እ.አ.አ በ1997  የተካሄደው የማስተርስ  ውድድር የታይገርን ልዕለ ሰብዓዊ ችሎታ ለዓለም ያሳየበት ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡

ገና በ21 ዓመቱ በዚህ ከፍተኛ ክብር ባለው የስፖርት መድረክ በመሳተፍ አሸንፏል፡፡ ታይገር በወቅቱ ውድድሩን ያጠናቀቀው ተከታዩን ተፎካካሪ በሰፊ ልዩነት በ12 ምቶች እንደነበር የዘ ሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ ድል በውድድሩ ታሪክ ትልቁ የነጥብ ልዩነት ከመሆኑም በላይ ታይገር ይህንን ዋንጫ ያሸነፈ የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ እና ትንሹ ተጫዋች እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ይህም በጎልፍ ዓለም ውስጥ አዲስ ንጉሥ መወለዱን ያበሰረ እንደነበር መረጃው ያስነብባል፡፡

ከዚህ ድል በኋላም ታይገር ውድስን የሚያሸንፈው ተወዳዳሪ ጠፋ፡፡ በተለይም ከ1999 እስከ 2002 እ.አ.አ በጎልፍ ታሪክ አስደናቂ ብቃት ያሳየበት ወቅት እንደነበር ሜል ስፖርት አስነብቧል፡፡ የዚህ ዘመን ማሳያው ደግሞ እ.አ.አ በ2000 እና 2001 የተፈጠረው ታይገር ስላም በመባል የሚታወቀው አስገራሚ ታሪክ ነው፡፡ በፈረንጆች ሚሊኒየም ታይገር አራት ታላላቅ  ውድድሮችን ማለትም የዩኤስ ኦፕን፣ የብሪትሽ ኦፕን እና የፒጂኤ ሻምፒዮንሺፕን በማሸነፍ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡

በአንድ የውድድር ዘመን አራቱንም ታላላቅ ዋንጫዎች ያሳካ በታሪክ ብቸኛው ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡ በተለይም በ2000 እ.አ.አ በፔብል ቢች በተካሄደው የዩኤስ ኦፕን ውድድር ተከታዩን በ15 ምቶች ልዩነት ያሸነፈበት መንገድ በየትኛውም ስፖርት ታሪክ ከተመዘገቡት ታላላቅ የግለሰብ የበላይነቶች አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በዚያ ውድድር ላይ ታይገር ከሌሎቹ ተጫዋቾች ጋር ሳይሆን ከራሱ ጥላ ጋር ብቻ የሚወዳደር እስኪመስል ድረስ ተፎካካሪዎቹን አፍዝዟቸው ነበር፡፡

ታይገር ውድስ በስፖርቱ ዓለም ስሙ በወርቅ ቀለም ከተጻፈላቸው ታላላቅ የጎልፍ ተጫዋቾች አንዱ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን በ2009 እ.አ.አ ማንም ያልጠበቀው እና ዓለምን ያስደነገጠ ክስተት ሲፈጠር የተዋጣለት የጎልፍ ኮከቡ የግል ሕይወት እንደ ካርቶን ቤት ተበላሸ፡፡ የውድቀቱ ማሳያ ደወል የተሰማው በዚያው ዓመት ኅዳር ወር ከቤቱ አጠገብ ያጋጠመውን የመኪና አደጋ ተከትሎ ነበር፡፡ ከዚህ አደጋ በኋላ ከትዳር ውጪ ያደረጋቸው በርካታ ፆታዊ ግንኙነቶች (ቅሌቶች) ለመገናኛ ብዙኃን ግልጽ ሆኑ፡፡ ያከበረው  ዓለም ፊቱን አዞረበት፤ የሁለት ልጆቹ እናት የነበረችው ባለቤቱ  ኤሊን ኖርዲግሬን ጥላው ስትሄድ ትዳሩ ፈረሰ፡፡

በተጨማሪም ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የነበራቸውን የስፖንሰርሺፕ ውል አቋረጡበት፡፡ ውድስ ክብሩን፣ ቤተሰቡን እና ዝናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጣ፡፡ የታይገር ችግር በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ የስነ ልቦና ጫናው በጤናው ላይ ከባድ ጉዳት ይዞ መጣ፡፡ እ.አ.አ ከ2014 ጀምሮ ተደጋጋሚ የጀርባ ህመም ስላጋጠመው አራት ጊዜ ከባድ ቀዶ ሕክምና አደረገ፡፡ መራመድ እና ከልጆቹ ጋር መጫወት እስከሚያቅተው ድረስ በህመም ተሰቃየ፡፡ ችግሩ ይበልጥ የከፋው ደግሞ በ2017 እ.አ.አ በመኪናው ውስጥ ራሱን ስቶ ሲገኝ ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ ከፍተኛ ውድቀት የታይገር የመጨረሻ ምዕራፍ አልነበረም፤ እጅ ለመስጠትም አላሰበም። የሕክምና እርዳታ በማግኘት  ቀስ በቀስ ወደ ውድድር በመመለስ እ.አ.አ በ2019 ማንም ያልጠበቀውን ተአምር ሠራ፡፡ ከ11 ዓመታት በኋላ ያገኘው ይህ ትልቅ ድል በስፖርቱ ታሪክ ከተመዘገቡት ታላላቅ ወድቆ መነሳት  ታሪኮች አንዱ ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ዛሬ ላይ ታይገር የጎልፍ ሻምፒዮን ብቻ ሳይሆን፣ የህይወት ፈተናን ያሸነፈ ጀግና ስፖርተኛ ጭምር ነው፡፡

የታይገር ውድስ በጎልፍ ስፖርት ህይወቱ  82 የፒጂኤ ቱር ውድድሮችን በማሸነፍ ከታላቁ ሳም ስኒድ ጋር ክብረ ወሰኑን ይጋራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 15 ታላላቅ ዋንጫዎችን በማንሳት ከጃክ ኒክላውስ (18 ዋንጫዎችን አንስቷል) በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ታይገር ውድስ በጎልፍ ስፖርት ዘመኑ ለ683 ሳምንታት (ከ13 ዓመታት በላይ ማለት ነው) የዓለም ቁጥር አንድ የጎልፍ ተጫዋች ሆኖ ቆይቷል፡፡

ከዚህ ውስጥ ደግሞ ለ281 ተከታታይ ሳምንታት ማንም ከዙፋኑ ሊያወርደው እንዳልቻለ መረጃዎች ይነግሩናል፡፡ የ50 ዓመቱ አሜሪካዊ ለዐስርት ዓመታት ስፖርቱን በብቸኝነት የገዛ የጎልፍ ንጉሥ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመሰክሩለታል፡፡ ቀይ መለያ ለብሶ ወደ ሜዳ ላይ ሲገባ ተቀናቃኞቹ በስነ ልቦና ቀድመው ይሸነፉ እንደነበር ይነገራል፡፡

ከታይገር መምጣት በፊት ጎልፍ ብዙ አካላዊ ብቃት የማይጠይቅ፣ ተጫዋቾች ሆዳቸውን አሳብጠው የሚጫወቱት ስፖርት ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ ታይገር ግን ይህንን ቀየረው፤ ክብደት ማንሳት ጀመረ፣ እንደ አትሌት መሮጥ እና አካላዊ ጥንካሬን ማዳበር የስፖርቱ አካል እንዲሆንም አደረገ፡፡ ኳስን የሚመታበት አስገራሚ ኃይል እና ፍጥነት የጎልፍ ሜዳዎችን አሰራር ሳይቀር አስቀይሯል፡፡ የውድድር አዘጋጆች ታይገርን ለማስቆም ሜዳዎችን ማራዘም እና አሸዋማ ነገሮችን መጨመር ጀመሩ፤ ይህ አሰራርም በስፖርቱ ዓለም ታይገር ፕሩፊንግ  የሚል ስያሜ አግኝቷል፡፡

የታይገር ተጽዕኖ የጎልፍ ስፖርት የቴሌቪዥን ተመልካች እንዲጨምር እና ስፖንሰሮች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ማፍሰስ እንዲጀምሩ አድርጓል፡፡ ታይገር ወደ ስፖርቱ ሲገባ ጥቂት መቶ ሺህ ዶላሮች የነበረው የውድድር ሽልማት እርሱ ስፖርቱን ከተቀላቀለ በኋላ ወደ ሚሊዮኖች አደገ፡፡ ዛሬ ላይ ያሉ የጎልፍ ተጫዋቾች ለሚያገኙት ከፍተኛ ገቢ እና ዝና የታይገር ውድስ በስፖርቱ ውስጥ መፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ከበርካታ የጀርባ ቀዶ ሕክምናዎች፣ ከስነ ልቦናዊ ውድቀቶች እና ከእድሜ መግፋት በኋላ ማንም ዳግም ያሸንፋል ብሎ ባልጠበቀበት ሰዓት በ2019 እ.አ.አ በ43 ዓመቱ   የማስተርስ ውድድርን በማሸነፍ 15ኛ ሜጀር ዋንጫውን አነሳ፡፡ ይህ ድል በስፖርት ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት ታላላቅ እና አስገራሚ ወድቆ መነሳት ታሪኮች ቀዳሚው ነው፡፡ እሱ የጎልፍ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን ስፖርቱን ወደ ስነ ጥበብ እና ሳይንስ የቀየረ፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ስፖርተኞች መነሳሳትን የፈጠረ የምንጊዜም ታላቅ ስፖርተኛ ነው፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሚያዚያ 5  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here