ፈዋሿ ሙዚቃ

0
119

በዘመናዊው የነርቭ ሳይንስ (Neuroscience) የሙዚቃ ፈዋሽነት በቤተ ሙከራ ከመረጋገጡ ከብዙ ዓመታት በፊት አንጋፋዎቹ የኢትዮጵያ ድምጻውያን  ሙዚቃ ለነፍስ መድኀኒት፣ ለብቸኝነት አጋር እና ለጭንቀት ማስታገሻ መሆኑን በዜማዎቻቸው ነግረውናል። ካሳ ተሰማ፣ አስቴር አወቀ፣ ታምራት ሞላ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ተዘራ ኀይለ ሚካኤል፣ ነዋይ ደበበ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ተስፋዬ ገብሬ እና ሌሎችም ድምጻዉያን ስለ ሙዚቃ መንፈስን አረጋጊነት አዚመዋል።

ሄንሪ በኒውዮርክ ብሩክሊን በሚገኝ “ኮብል ሂል”  የተባለ የአረጋውያን እና የሕሙማን መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ የሚኖር አዛውንት ነበር::  ለዓመታት በዘለቀ የከፋ የመርሳት (የአልዛይመር) በሽታ ምክንያት ማንነቱን ሙሉ በሙሉ ረስቶ ነበር:: ቀኑን ሙሉ በተሽከርካሪ ወንበሩ ላይ አንገቱን ደፍቶ ከማንም ጋር ሳይነጋገር ይውላል። ለውጫዊው ዓለም ምንም አይነት ምላሽ አይሰጥም። የልጁን ስምም ሆነ ፊቷን አያስታውስም:: እርሱን ለማናገር የሚሞክሩ የሕክምና ባለሙያዎችን  ከማየት በቀር ምላሽ አይሰጥም።

አላይቭ ኢንሳይድ በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ላይ እንደታየው የነርቭ ሳይንቲስቶች እና የሙዚቃ ሕክምና ባለሙያዎች በሄንሪ ላይ አንድ አስደናቂ ሙከራ አደረጉ:: ሄንሪ በወጣትነቱ ማዳመጥ ይወዳቸው የነበሩትን በተለይም የካብ ካሎዋይ  የጃዝ እና የሪትም ኤንድ ብሉዝ (R&B) ሙዚቃዎችን በጆሮ ማዳመጫ አደረጉለት::

ውጤቱ የሕክምና ባለሙያዎቹን ጭምር ያስገረመ የሳይንስ ተዓምር ነበር:: ሄንሪ ሙዚቃውን መስማት ሲጀምር በቅጽበት አንገቱን ቀና አደረገ፤ የፈዘዙት ዓይኖቹ በረቱ። የሰውነቱ አቋም ተስተካከለ። ከሙዚቃው ሪትም ጋር እጆቹን እና እግሮቹን ማንቀሳቀስ ጀመረ:: ከዓመታት የዝምታ እስር ቤት ወጥቶ ሙዚቃውን አብሮ በለሆሳስ መዘመር ጀመረ:: ይበልጥ አስገራሚው ነገር ደግሞ የጆሮ ማዳመጫው ከወለቀለት በኋላ የተፈጠረው ክስተት ነበር:: ሄንሪ ለተወሰነ ጊዜ ንግግሩ ተመልሶ ስለ ወጣትነት ትዝታዎቹ፣ ስለሚወዳቸው የሙዚቃ ሰዎች እና ስለ ሕይወቱ አቀላጥፎ መተረክ ቻለ::

ከሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ታሪክ አንጻር የሳይንስ ሊቃውንት ሙዚቃን ሲተነትኑት የሰው ልጅ ቋንቋን ፈጥሮ መናገር ከመጀመሩ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በድምጽ ቃና እና በሪትም ተግባብቷል ይላሉ:: ታላቁ የዝግመተ ለውጥ አጥኝ ቻርለስ ዳርዊን “የሰው ልጅ የንግግር ቋንቋን ከመፍጠሩ በፊት ፍቅርን ለመግለጽ እና ጠላትን ለማስፈራራት ሙዚቃዊ ቃና ያላቸውን ድምጾች ይጠቀም ነበር” ብሎ ያምናል:: ሙዚቃ በቀጥታ ከሰውነታችን የልብ ምት፣ ከትንፋሻችን እና ከነርቭ ስርዓታችን ጋር የተቆራኘ ተፈጥሯዊ ቀመር እና የስሜት ውሕደት ነው:: ለዚህም ነው ሙዚቃ ቋንቋን፣ ብሄርን እና የባህል ድንበርን ተሻግሮ የሰውን ልጅ  ስሜት መንካት  የሚችለው::

የሙዚቃ ሕክምና (Music Therapy)  የነርቭ ሳይንስ እና የስነ-ልቦና ጥናት ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፋዊ የሕክምና ዘርፍ ነው::

ታዋቂው የነርቭ ሐኪም፣ ተመራማሪ እና ጸሐፊ ዶ/ር ኦሊቨር ሳክስ  “ሙዚኮፊሊያ: ቴልስ ኦፍ ሚዩዚክ ኤንድ ዘ ብሬይን”  በተሰኘው  መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ “ሙዚቃ በአዕምሯችን ውስጥ የሚሠራው ሥራ ከማንኛውም የሰው ልጅ ተመክሮ የተለየ ነው:: ሌላው ቀርቶ ቋንቋን የሚያስተናግደው የአዕሯችን ክፍል በአደጋ ወይም በስትሮክ (Stroke) ምክንያት ቢጎዳ ሙዚቃ ግን በአንድ የአዕምሮ ክፍል ላይ ብቻ ስለማይወሰን የተጎዳውን አዕምሮ በሌላ አቅጣጫ ፈውሶ ንግግርን ሊመልስ ይችላል።”

ዘመናዊ የአዕምሮ ምስል ማንሻ ቴክኖሎጂዎች ( FMRI እና PET Scans) እንዳረጋገጡት የሰው ልጅ የሚወደውን ሙዚቃ ሲያዳምጥ አዕምሮው ልክ እንደ ርችት በየአቅጣጫው ይበራል:: በካናዳው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ የነርቭ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት እና “ዚስ ኢዝ ዩር ብሬይን ኦን ሚዩዚክ”  የተሰኘው  መጽሐፍ ደራሲ ዶ/ር ዳንኤል ሌቪቲን ባደረጉት ጥናት መሠረት ሙዚቃ በሚቀጥሉት ቁልፍ የአዕምሮ ክፍሎች ላይ ፈጣን ለውጥ ያመጣል።

ሀ.  ሚግዳላ (Amygdala)፦ ይህ ስሜትን፣ ፍርሃትን እና ማስጠንቀቂያን የሚያስተናግደው ጥልቅ የአዕምሮ ክፍል ነው:: ለስላሳ፣ ዘገምተኛ እና የሚያረጋጋ ሙዚቃ (በተለይም በመሣሪያ ብቻ የተቀናበረ ሙዚቃ) ስናዳምጥ አሚግዳላ ይረጋጋል። የጭንቀት መጠንም ወዲያውኑ ይቀንሳል::

ለ. ሂፖካምፐስ (Hippocampus)፦ ይህ የሰው ልጅ የማስታወስ ችሎታ ማዕከል እና የትዝታ ማሕደር ነው:: በመግቢያው ላይ ያየነው ሄንሪ የተባለው አዛውንት ሙዚቃው የማስታወስ ክፍሉን (Hippocampus) በጥልቅ ስለቀሰቀሰው ነው የጠፋው ትዝታው በቅጽበት የተመለሰለት::

ሐ. ሞተር ኮርቴክስ እና ሴሬብለም (Motor Cortex and Cerebellum)፦ ሙዚቃ ስናዳምጥ ሰውነታችንን የምናንቀሳቅሰው እነዚህ የሰውነት እንቅስቃሴን የሚቆጣጠሩ የአእምሮ ክፍሎች በሙዚቃው ሪትም (Rhythm) ስለሚነቃቁ ነው:: ይህ ክስተት ፓርኪንሰንስ (የመንቀጥቀጥ ሕመም) ላለባቸው ታካሚዎች የመራመድ ችሎታቸውን እንዲመልሱ በሕክምናው ዓለም ትልቅ ጥቅም እየሰጠ ይገኛል::

የሙዚቃ ሕክምና በዋነኝነት የሚሠራው በአዕምሮ ውስጥ ያሉ ኬሚካሎችን (Neurotransmitters) በማመጣጠን ነው:: አዕምሯችን ደስ የሚል ዜማ ሲሰማ “ዶፓሚን” የተባለውን የደስታ እና የሽልማት ሆርሞን በከፍተኛ መጠን ያመነጫል:: በተቃራኒው ደግሞ “ኮርቲሶል” (Cortisol) የተባለውን እና የሰውን ልጅ ለደም ግፊት እና ለስኳር በሽታ የሚያጋልጠውን የጭንቀት ሆርሞን በከፍተኛ ፍጥነት ይቀንሳል:: ከዚህም ባሻገር ህመምን በራሱ ማስታገስ የሚችለውን “ኤንዶርፊን”  የተባለ ኬሚካል እንዲመነጭ ያደርጋል::

የአሜሪካ የሙዚቃ ሕክምና ማህበር እንደሚያስረዳው የሙዚቃ ሕክምና ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶችን ለመጠገን፣ ድብርትን ለመዋጋት እና አካላዊ ህመሞችን ለማስታገስ ትልቅ መሣሪያ ነው::

ሀ. ለቀዶ ጥገና (Surgery) ታካሚዎች ፈውስ፦ የአሜሪካ ስነ-ልቦና ማህበር ባሳተመው አንድ ሰፊ ጥናት ከባድ ቀዶ ጥገና ከማድረጋቸው በፊት የሚያረጋጋ ሙዚቃ ያዳመጡ ታካሚዎች፣ ሚዳዞላም (Midazolam) የተባለውን ከባድ የጭንቀት ማስታገሻ መድኀኒት ከተሰጣቸው ታካሚዎች ይልቅ የተሻለ እርጋታ ታይቶባቸዋል ይላል:: በተጨማሪም ከቀዶ ጥገና በኋላ የሕመም ማስታገሻ መድሃኒት ፍላጎታቸው በእጅጉ ቀንሶ ተገኝቷል::

ለ.  ለድኅረ-አደጋ ስነ-ልቦናዊ ቀውስ (PTSD) ቴራፒ፦ በጦርነት፣ በአደጋ ወይም በከባድ ኀዘን ምክንያት የስነ-ልቦና ቀውስ የገጠማቸው ሰዎች ሙዚቃን እንደ ደኅንነት መጠበቂያ ይጠቀሙበታል:: ታካሚዎች ቃላት ሊገልጹት የማይችሉትን በውስጣቸው የታመቀ አስፈሪ ስሜት የሙዚቃ መሣሪያ (ለምሳሌ ከበሮ ወይም ጊታር) በመጫወት እንዲያወጡት ይደረጋል:: ይህ ‘Active Music Therapy’ በመባል የሚታወቀው ዘዴ አዕምሮ ራሱን በራሱ እንዲጠግን  ያግዘዋል::

ሐ. ያለ ጊዜያቸው ለተወለዱ ህጻናት (NICU)፦ በዘመናዊ የሕጻናት ማቆያ ክፍሎች ውስጥ ያለ ጊዜያቸው ለተወለዱ (Premature) ህጻናት የእናቶቻቸውን የልብ ምት የሚመስሉ እና ለስላሳ የሕጻናት ማጫወቻ ዜማዎች  እንዲሰሙ ይደረጋል:: ጥናቶች እንዳረጋገጡት ይህን የሙዚቃ ህክምና ያገኙ ሕጻናት የልብ ምታቸው ይስተካከላል። የእንቅልፍ ሰዓታቸው ጤናማ ይሆናል። እንዲሁም በፍጥነት ክብደት የመጨመር እድላቸው ከፍተኛ ነው::

ሙዚቃ ለጆሮ የሚሰጥ መዝናኛ ብቻ አይደለም፤ በውስጡ መድኀኒትነትን ያዘለ፣ በአየር ላይ የሚጓዝ የነፍስ እና የስጋ ሀኪም ነው:: የጀርመኑ ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ “ያለ ሙዚቃ ህይወት ስሕተት ትሆን ነበር” እንዳለው የነርቭ ሳይንስ ዛሬ ይህንን የፈላስፋውን ቃል በቤተ-ሙከራ አረጋግጦታል::

 

 

መረፊያ

ካሳ ተሰማ የሙዚቃ ሞገስ

ከሰማይ የመጣሽ የእግዚአብሔር ስጦታ

የኑሮ ደጋፊ የመንፈስ አለኝታ

ስሜት የምትሰጪ ሆነሽ መድኃኒት

ሙዚቃ ነሽ እኮ ለሰው አብነት፡፡

በስጭት ጭቅጭቅ ኀዘን ወይ ትካዜ

ይረቃሉ ከሰው አንቺ ባለሽ ጊዜ

ይረቃሉ ከሰው አንቺ ባለሽ ጊዜ፡፡

ሰው ኀዘን ሲወረው ቸግሮት መሸሻ

አንቺ ነሽ ምሽጉ እስከመጨረሻ፡፡

በልዩ አጋጣሚ ደስታ ሲያገኘው

የሰው ልጅ ስሜቱን የሚገልጽ በአንቺ ነው፡፡

በፍቅር ተነድፎ መንፈሱ ሲነካ

ባንቺ ነው የሰው ልጅ ልቡን የሚያረካ፡፡

ትካዜ ሲይዘው ሰው ባንቺ ይጽናናል

እስኪ እንዳንቺ ፈዋሽ ከወዴት ይገኛል?

ነፍሴ የወደደችሽ ጥሩነትሽን አውቃ

የዓለም መድኃኒት ፈዋሽ ነሽ ሙዚቃ፡፡

ሥራሽን ተዘርዝሮ ብዙ ነው መቼ ያልቃል

ሙዚቃ ስሜት ነሽ ብንልሽ ይበቃል፡፡

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዚያ 5  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here