አማራጭ የሌለው ምርጫ

0
80

አሜሪካዊው ባለሀብት እና የማይክሮሶፍት ኩባንያ መሥራች እንዲሁም ባለቤት ቢል ጌትስ “ቴክኖሎጂ ሰውን ለመርዳት ተፈጥሯል፤ ነገር ግን ካልተጠነቀቅን እኛን ሊገዛን ይችላል“ በማለት ስለ ቴክኖሎጂ በጽሑፍ  አስፍሯል:: በዘመናዊው ዓለም ቴክኖሎጂ የሰው ሕይወትን በሁሉም ዘርፎች በጥልቅ በማስተሳር ኑሮን ቀላል እንዲሆን አድርጓል። በትምህርት ዘርፍ ያለው አስተዋፅኦ ደግሞ ከሌሎች ይለያል፤ ምክንያቱ ደግሞ ትምህርት የሁሉም ዘርፎች ዕድገት ቁልፍ በመሆኑ ነው:: የትምህርት ዘርፍ ሲሻሻል ደግሞ ሀገር በሁለንተናዊ ጎዳና ላይ ትራመዳለች።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ምክክር ተካሂዶ ነበር፤ በምክክሩም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ አመራች እና ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል:: የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነትም አድርጓል::

“ስምምነቱ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላለው የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ስትራቴጂ ነው” ተብሏል::

የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው ለበኩር እንዳብራሩት ቴክኖሎጂን መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፤ ክልሉን በሁሉም ዘርፎች ለማልማት የቴክኖሎጂ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም::

ሀገራችን የዲጂታል ዓምን በመቀላቀል የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ በትኩረት እየሠራች ትገኛለች፤ ለአብነትም በዲጂታል 2025 ሲተገበር የቆየው እና በድጅታል 2030 ተጠናክሮ የቀጠለው የቴክኖሎጅ ሥርዓት ይጠቀሳል፤ ይህ ግቡን እንዲመታ ታዲያ በአጋርነት እና በትብብር መሥራት እንደሚገባ አቶ የቻለ አስገንዝበዋል::

“ለዚህ ደግሞ በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ባለድርሻ በማድረግ በቴክኖሎጂ ሽግግሩ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ስምምነት ተፈጥሯል” ነው ያሉት::

አቶ የቻለ እንዳሉት ቢሮው የመንግሥት አገልግሎቶች እንዲሳለጡ እና የቴክኖሎጅ መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ በማድረግ የክልሉን ኢኮኖሚ እና የትምህርት ጥራትን ለመደገፍ ግብ አስቀምጦ እየሠራ ነው::

ኢንተርኔትና ዲጂታል መሣሪያዎች ተማሪዎችን ከተለመደው የመጻሕፍት ዕውቀት አውጥቶ ወደ ሰፊ የግንዛቤ ዓለም አስገብቷል። በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች ዓለም አቀፍ መረጃዎችን በቀላሉ ያገኛሉ፤ በቪዲዮ፣ በምስል እና በአይነት የተለያዩ የመማሪያ መንገዶችን በመጠቀም ትምህርታቸውን ያጠናክራሉ። ይህ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የግል ጥረትን ይጠይቃል።

በሌላ በኩል፣ ቴክኖሎጂ መምህራንን የተሻለ የማስተማር ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ ያግዛል። በፕሮጀክተር፣ በዲጂታል መድረኮች እና በኦንላይን ምንጮች በመጠቀም ትምህርትን የሚያስተላልፉበትን መንገድ ያሻሽላል፤ ይህም ተማሪዎች በቀላሉ እንዲረዱት እና የግል የመማር ፍጥነትን በመከታተል ተማሪዎች ከሌሎች ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ እንዲማሩ ያስችላል።

ከሰሞኑ በነበረው ምክክር ስምምነቱን ካደረጉት መካከል የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ይገኝበታል፤ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ/ር) እንዳሉት ስምምነቱ የጋራ ተግባራትን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለይቶ ለመሥራት የሚያስችል ነው::

በቀጣይም በክልሉ ለሚያስፈልጉ የቴክኖሎጅ ፍላጎቶች በተቀናጀ መልኩ በውጤታማነት ለመተግበር በጋራ ይሠራሉ::

“ቴክኖሎጂን በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ማዋሃድ የዛሬ ምርጫ ሳይሆን የነገ ህልውና ጉዳይ ነው” ያሉን ደግሞ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጡት ማርሸት ግርማይ (ዶ/ር) ናቸው፤  ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጅ ዘርፉ ለሚሠራቸው ተግባራት፣ የፖሊሲ እና የስትራቴጂ አቅጣጫዎችን ተከትሎ ለመፈጸም ስምምነቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል:: በተለይም በቴክኖሎጅ የታገዘ የስራ እድል ፈጠራ ላይ ዩኒቨርሲቲው ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ትብብሩ አቅም እንደሚሆን አመላክተዋል::

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ምንጭ ናቸው፤ ይህ ደግሞ ተማሪዎች ወደ ማሕበረሰቡ በሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተግባር ይተረጉሙታል:: ሀገርም በሁሉም ዘርፎች በተሸለ የዕድገት ጎዳና ላይ እንድትገኝ ቁልፍ ድርሻ ይኖረዋል:: ከሰሞኑ የተካሄደው ምክክር እና የተደረገው ስምምነት ታዲያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከመፍጠር ባለፈ ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚያስችል ነው የተጠቆመው::

የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ/ር) በክልሉ የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ስትራቴጂ  እንደሆነ የታመነበት ስምምነቱ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ  እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን ግንኙነት በማጠናክር ወደ ተቀናጀ ሽግግር የሚወስድ መሆኑን ተናግረዋል።

ዶክተር ስቡህ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የሚሳካው የመንግሥት አሥፈጻሚ አካላት እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአንድነት ሲሠሩ ነው። ክልሉ ካለው የልማት ፍላጎት አንጻርም ቴክኖሎጂን መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ስለመሆኑ አንስተዋል።

 

ዜና

የቴክኖሎጅ መዘመን ለትምህርት ያለው አበርክቶ

የቴክኖሎጂ መዘመን በትምህርት ዘርፍ ላይ ያመጣው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ እና መሠረታዊ የሚባል ነው። በአሁኑ ጊዜ መማር ማስተማር በአራት ግድግዳዎችና በጥቁር ሰሌዳ ብቻ የተገደበ መሆኑ ቀርቶ በዲጂታል አማራጮች እየተቀየረ ይገኛል።

የቴክኖሎጂ ዋና ዋና አበርክቶዎች በሚከተሉት ነጥቦች ሊጠቃለሉ ይችላሉ፡-

የመረጃ ተደራሽነት

ቀደም ባሉት ጊዜያት መረጃ ለማግኘት ወደ ቤተ-መጽሐፍት መሄድ ግድ ይል ነበር። አሁን ግን፡-

በየትኛውም ቦታ እና ሰአት ተማሪዎች የፈለጉትን የትምህርት ዓይነት በኢንተርኔት አማካኝነት ባሉበት ሆነው ማግኘት ይችላሉ።

ክፍት የትምህርት ግብዓቶችን ፡ እንደ ዩቲዩብ (YouTube)፣ ካን አካዳሚ (Khan Academy) እና የተለያዩ የኢ-መጽሐፍት ድረ-ገጾች ከፍተኛ እውቀትን በነፃ ያጋራሉ።

ግለሰባዊ ትምህርት:-ቴክኖሎጂ ተማሪዎች እንደየራሳቸው የመረዳት ፍጥነትና ፍላጎት እንዲማሩ ይረዳቸዋል፡-

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI): የተማሪዎችን ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት ለእነሱ የሚስማማ የትምህርት ይዘት የሚያቀርቡ መተግበሪያዎች ተፈጥረዋል።

ተማሪዎች ያልገባቸውን ትምህርት ደጋግመው ለማየትና ለመለማመድ ዕድል ይሰጣቸዋል።

የተሻሻለ የመማር ማስተማር ዘዴን በመጠቀም ትምህርት አሰልቺ እንዳይሆን ቴክኖሎጂ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡-

ትምህርቶች በቪዲዮ፣ በምስል እና በድምፅ የታጀቡ በመሆናቸው ግንዛቤን ይጨምራሉ።

ተማሪዎች ሳይንሳዊ ሙከራዎችን ወይም የታሪክ ቦታዎችን ባሉበት ሆነው በምናብ እንዲጎበኙና በተግባር እንዲለማመዱ ያስችላቸዋል።

ቴክኖሎጂ በትምህርት ላይ ትልቅ አበርክቶ ቢኖረውም፣ እንደ ኢንተርኔት መቆራረጥ፣ የመሣሪያዎች እጥረት እና ተማሪዎች ለሌላ ዓላማ (ለምሳሌ ለሱስ) የመጋለጥ ዕድላቸው እንደ ትልቅ ተግዳሮት ይታያል።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሚያዚያ 5  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here