ውቂያኖሶች

0
59

ሰላም ልጆች! ዛሬ ደግሞ እጅግ በጣም ሰፊና አስገራሚ ወደሆነው የውቂያኖሶች ዓለም ይዘናችሁ እንጓዛለን።

የውቅያኖሶች ዓለም እኛ ከምንኖርበት የየብስ ክፍል በብዙ እጥፍ የሚሰፋ እና እጅግ አስገራሚ ሚስጥሮችን በጉያዉ የያዘ ግዙፍ ዓለም ነው። ምድራችንን ከላይ ሆነን ብንመለከታት ሰማያዊ ሆና የምትታየው በዚሁ በውቅያኖሶች ስፋት ምክንያት ሲሆን ይህም የሆነው ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የምድራችን ክፍል በውኃ የተሸፈነ በመሆኑ ነው።

የውቅያኖሶች ሚስጥር የሚጀምረው ከጥልቀታቸው ነው። ውቅያኖስ ውስጥ በጣም ወደ ታች በወረድን ቁጥር ብርሃን እየጠፋ እና ቅዝቃዜው እየጨመረ ይሄዳል። “ሚድ ናይት ዞን” ወይም የለሊት ቀጠና ተብሎ በሚጠራው ጥልቀት ውስጥ ብርሃን ጨርሶ ስለማይደርስ ዓለሙ ድቅድቅ ጨለማ ነው። በዚህ አስፈሪ በሚመስል ስፍራ የሚኖሩ ዓሳዎች ግን ተፈጥሮ ልዩ ስጦታ ሰጥታቸዋለች። አንዳንዶቹ እንደ ባትሪ ብርሃን በራሳቸው አካል ላይ የሚያበሩ መብራቶች አሏቸው፤ ይህም በጨለማው ውስጥ ወዳጆቻቸውን ለማግኘት ወይም ምግባቸውን ለማደን ይረዳቸዋል።

በውቅያኖስ ውስጥ የሚገኙ ተራራዎችና ሸለቆዎች በየብስ ላይ ካሉት እጅግ ይበልጣሉ። ለምሳሌ “ማሪያና ትሬንች” የተባለው የውቅያኖስ ጥልቀት የዓለማችንን ረጅሙን ተራራ ኤቨረስትን እንኳ ቢጨምሩት የማይሞላው ጥልቀት አለው። እዚያ ውስጥ ያለው የውኃ ጫና በጣም ከፍተኛ ቢሆንም ይህን ተቋቁመው የሚኖሩ አስገራሚ ፍጥረታት መኖራቸው የሳይንስ ሊቃውንትን እስካሁን ያስደምማል።

ሌላው የውቅያኖስ ሚስጥር በውስጡ የያዛቸው ግዙፍና ትናንሽ ፍጥረታት ናቸው። ሰማያዊው ዓሣ ነባሪ በምድር ላይ ከነበሩት ዳይኖሰሮች እንኳ የሚበልጥ ግዙፍ እንስሳ ሲሆን ልቡ ብቻ እንደ አንድ ትንሽ መኪና ያህላል። በሌላ በኩል ደግሞ “ኮራል ሪፍ” የሚባሉት የባሕር ውስጥ የአትክልት ስፍራዎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓሳዎች እንደ ከተማ መጠለያ በመሆን ያገለግላሉ። እነዚህ ኮራሎች ከውኃው ስር ሆነው እጅግ ውብ የሆኑ ቀለማትን እና ቅርጾችን በመፍጠር ውቅያኖሱን ያስውቡታል።

ውቅያኖሶች ለእኛ ለሰዎችና ለምድራችን ሕልውና ወሳኝ ናቸው። በየቀኑ የምንተነፍሰው ኦክስጅን ከግማሽ በላይ የሚመረተው በውቅያኖስ ውስጥ በሚገኙ ጥቃቅን እፅዋት ነው። በተጨማሪም ውቅያኖሶች እንደ ግዙፍ የአየር ማቀዝቀዣ በመሆን የምድራችን ሙቀት ሚዛኑን ጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋሉ። ያለ ውቅያኖሶች ምድራችን ለሕይወት የማይመች በጣም ሞቃት ስፍራ ትሆን ነበር።

ይህ ሁሉ አስደናቂ ሀብትና ሚስጥር ግን ዛሬ አደጋ ላይ ነው። ሰዎች ወደ ውቅያኖስ የሚጥሉት ፕላስቲክና ቆሻሻ በውስጡ የሚኖሩትን ፍጥረታት እያሳመመ ነው።

ምንጭ፡- ናሽናል ኦሺን ሰርቪስ

ተረት

ሰባቱ ግልገሎች

ከዕለታት አንድ ቀን ሰባት ግልገሎች ያሏት አንዲት እናት ፍየል ነበረች። አንድ ቀን ወደ ጫካ መኖ ለመፈለግ ስትሄድ ልጆቿን ጠርታ “ልጆቼ ሆይ! እኔ እስክመለስ በሩን ዘግታችሁ ተቀመጡ፤ ተኩላው መጥቶ እንዳይበላችሁ ተጠንቀቁ። እርሱ ተንኮለኛ ነው፤ ነገር ግን በጎርናና ድምፁ እና በጥቁር እግሮቹ ልታውቁት ትችላላችሁ” ብላ አስጠነቀቀቻቸው።

እናት ፍየል እንደሄደች ተኩላው መጥቶ በሩን አንኳኳና “ልጆቼ በሩን ክፈቱልኝ፤ እናታችሁ ነኝ” አለ። ግልገሎቹ ግን “አንከፍትም! የእናታችን ድምፅ ቀጭን እና ለስላሳ ነው፤ ያንተ ግን ጎርናና ነው፤ አንተ ተኩላ ነህ!” አሉት። ተኩላው ሄዶ ድምፁን የሚያለሰልስ ነገር በልቶ ተመለሰ እና ደግሞ አንኳኳ። በዚህ ጊዜ ግልገሎቹ ጥቁር እግሮቹን በመስኮት በኩል አይተው “አንከፍትም! እናታችን ነጭ እግር አላት፤ ያንተ ግን ጥቁር ነው!” አሉት።

ተኩላው ተመልሶ ሄዶ እግሩ ላይ ዱቄት በመነስነስ ነጭ አስመስሎ መጣ። በዚህ ጊዜ ግልገሎቹ ድምፁም ስለለሰለሰ፣ እግሩም ስለነጣ እናታችን ናት ብለው በሩን ከፈቱለት። ተኩላውም ዘሎ በመግባት ስድስቱን ግልገሎች በአንድ ጊዜ ዋጣቸው፤ አንዲቷ ትንሽ ግልገል ግን ግድግዳ ላይ በተሰቀለ ሰዓት ውስጥ ተደብቃ ተረፈች።

እናት ፍየል ስትመለስ ቤቱ ተመሰቃቅሎ እና ልጆቿ ጠፍተው አገኘች። የተደበቀችው ትንሿ ግልገል ወጥታ የሆነውን ሁሉ ነገረቻት። እናት ፍየል በጣም አዝና ተኩላውን ፍለጋ ሄደች። ተኩላው ብዙ በልቶ በዛፍ ሥር ተኝቶ አገኘችው። ሆዱ ውስጥ ግልገሎቹ ሲንቀሳቀሱ ስላየች ተኩላው ሳይነቃ በቢላ ሆዱን ቀዳ ስድስቱንም ግልገሎች በሕይወት አወጣቻቸው። በምትካቸውም ሆዱ ውስጥ ከባድ ድንጋዮችን ሞልታ መልሳ ሰፋችው።

ተኩላው ከእንቅልፉ ሲነቃ በጣም ጠምቶት ውሃ ሊጠጣ ወደ ምንጭ ሄደ። ሆዱ ውስጥ ያሉት ድንጋዮች ስለከበዱት ወደ ውኃው ውስጥ ዘንበል ሲል ተያይዞ በመግባት ሰመጠ። እናት ፍየል እና ሰባቱ ግልገሎችም በደስታ እና በሰላም መኖር ቀጠሉ። የተረቱ መልዕክት ተንኮለኛ ሰው መጨረሻው ጥፋት ነው፤ ትናንሽ ልጆችም ሁልጊዜ የወላጆቻቸውን ምክር መስማት እና ለማያውቁት ሰው በር መክፈት የለባቸውም።

ምንጭ፡- የሕዝብ ተረት፡፡

 

በምድራችን ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ ትልቁ እና ልቡ ትንሽ መኪና የሚያክለው እንስሳ ማን ይባላል?

  1. በጣም ቀዝቃዛ የነበረ ውሃ ሲፈላ ወደ ምንነት ይለወጣል?
  2. ሲሄድ  ውሎ ሲሄድ   የሚያድር

መልስ

  1. አሳ ነባሪ
  2. ትነት
  3. ወንዝ

ነገር በምሳሌ

  • • “ከሕፃን እስከ አዛውንት፣ ይተጋል እንደ ጉንዳን”

 እንደ ጉንዳን ሁልጊዜ ታታሪና ሠራተኛ መሆንን ያሳያል።

 

  • “ድመት በሌለበት፣ አይጥ መንግሥት ናት”

ጠባቂ ወይም ተቆጣጣሪ በሌለበት ቦታ ሥርዓት አልበኝነት ሊነግሥ እንደሚችል ያስረዳል።

 

  • ትዕግስት ካለ ተራራ ይናዳል።

ታጋሽ ሰው የቱንም ያህል ከባድ የሆነን ነገር ማሸነፍ ይችላል

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሚያዚያ  12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here