በመካከለኛ እድሜ (30 እና 40ዎቹ) የሚገኙ ከፍተኛ የቫይታሚን “ዲ” መጠን ያለቸው ሰዎች ሀምሳዎቹን ሲያልፉ ለአንጐል የጤና እክል የመጋለጥ ደረጃቸው ዝቅተኛ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ሳይንስ ዴ ይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል::
ባንጻሩም የቫይታሚን “ዲ” መጠን ዝቅተኛ መሆን ደግሞ በአእምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ እክል ይፈጥራል ነው ያሉት – ተመራማሪዎቹ::
ተመራማሪዎቹ በጥናቱ በአማካይ 39 ዓመት እድሜ የሆናቸውን 793 ጐልማሶችን አሳትፈዋል:: የተሳታፊዎቹን የአንጐል ሁኔታ ለመቃኘትም የኘሮቲን መጠናቸውን ለክተዋል:: በልኬታውም ከ30 ና ኖግራም በላይ የተለካ ቫይታሚን “ዲ” ከፍተኛ ከዚያ በታች የሆነው ደግሞ ዝቅተኛ መሆኑንም አስምረውበታለ::
ከአጠቃላዩ 34 በመቶ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ዝቅተኛ የቫይታሚን “ዲ” መጠን ነበራቸው፤ ሌሎቹ ከአምስት በመቶ በታች የሆኑት የቫይታሚን “ዲ” ተጨማሪ ምግብ ወይም እንክብል መውሰዳቸውን ሪፖሪት አድርገዋል::
ተመራማሪዎቹ ከፍተኛ የቫይታሚን “ዲ” መጠን ያላቸው ጐልማሶች ከ16 ዓመታት በኋላ የኘሮቲን ቅሪቱ አነስተኛ መሆኑን ነው የተገነዘቡት:: በዚህም በመርሳት በሽታ የመያዝ ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን ነው የጠቆሙት::
የሰዎች የማስታወስ ዓቅም የሚገኝበት የአንጐል ክፍል በኘሮቲን ቅሪት መደፈን መዘጋት የለበትም ያሉት ተመራማሪዎቹ የቫይታሚን መጠንን ለመጨመር ከፀሀይ ብርሃን በተጨማሪ ከዓሳ፣ ከጉበት እና አትክልት በባለሙያዎች ምክር ታግዞ ማሟላት ይገባል ሲሉ ነው ያደማደሙት::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


