የመልክ መመሳሰል ያስከተለው መዘዝ

0
19

በአሜሪካ የቴኔሲ ከተማ ኗሪዋ የ50 ዓመቷ አንጄላ ሊኘስ በሰሜን ዳኮታ የባንክ ማጭበርበር ሲፈፀም በቁጥጥር ካሜራ ከተነሳ ምስል ጋር ፊታቸው በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመመሳሰሉ ለእስር መዳረጋቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::

አምስት የልጅ ልጆቻቸውን በመንከባከብ በቴኔሲ ህይወታቸውን የገፉት አንጄላ ሊኘስ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር በሚርቅ ግዛት ወንጀል ፈፅመዋል በሚል  ተጠርጥረው ነው ከመኖሪያ ቤታቸው በወጣባቸው ማዘዣ በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በ2025 ግንቦት ወር::

የወንጀሉ ፈፃሚ ሴት ስትሆን ሀሰተኛ የአሜሪካ ወታደር መታወቂያ ተጠቅማ በአስር ሺህ የሚቆጠር ዶላር ማውጣት ችላለች:: የድርጊቱን ፈፃሚ ለመያዝ በወጣው ማዘዣ በቁጥጥር መከታተያ ካሜራ የተነሳው ፎቶ ግራፍ ለማመሳከሪያነት ውሏል:: ወንጀሉ የተፈፀመበት ከተማ የፖሊስ መምሪያ በፊት ገጽ መለያ የኮምፒውተር ኘሮግራምን በመገልገል ባደረገው ማጣራት የአንጄላ ምስል ከወንጀል ፈፃሚዋ ጋር በእጅጉ መቀራረቡን ይለያል:: በዚህም አንጀላን ለመያዝ በቂ ማስረጃ ነው ብሎ በማመኑ ሴትዮዋ በቁጥጥር ስር ይውላሉ::

አንጄላ ሊኘስ በቴኔሲ ሦስት ወራት ከዚያም ወንጀሉ በተፈፀመበት ሰሜንዳ ኮታ ሦስት ወራት በእስር ያሳልፋሉ::

የተጠርጣሪዋ ጠበቃ የተጠርጣሪዋን መከራከሪያ ነጥቦች እና ማስረጃዎት አሰባስበው ያቀርባሉ:: በዚህም አንጄላ ሊኘስ ከሚኖሩበት ቴኔሲ ከተማ ውጪ ወጥተው እንደማያውቁ እና ተጠርጣሪዋ 1ሺህ 200 ማይል በሚርቀው ከተማ እንደነበሩ ባቀረቡት ማስረጃ ያሳምናሉ::

ዳኞችም የጠበቃዋን የክርክር መነሻ እና ማስረጃ ግራ ቀኙን አገናዝበው በነፃ እንዲለቀቁ መወሰናቸውን ድረ ገጹ በማጠቃለያነት አስነብቧል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here