ከትውልድ ወደ ትውልድ በሕዝቦች የተላለፈ የሕይወት ጥበብ እና ልምድ ነው – ሀገር በቀል ዕውቀት። ይህም በመጻፍ ብቻ ሳይሆን በተሞክሮ፣ በባሕል፣ በተለያዩ ልምዶች እና በሕይወት ልምምድ ውስጥ ይገኛል። ከግብርና፣ ከሕክምና፣ ከምግብ ዝግጅት እስከ አካባቢ ጥበቃ ድረስ በብዙ ዘርፎች ከፍ ያለ ዋጋም ያለው ነው።
ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ ጸጋ ከሚታወቁት ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች፤ የፋሲል ዓቢያተ መንግሥታት ሕንጻዎች፣ የላልይበላ ፍልፍል (ውቅር) አቢያተ ክርስቲያናት እና የአክሱም ሀውልት ደግሞ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ በቀደመው ዘመን በዚህ የከፍታ ደረጃ ላይ የነበረው ሀገር በቀል ዕውቀት በአሁኑ ወቅት በሚፈለገው ደረጃ ትኩረት አልተሰጠውም፤ በዚህም ምክንያት ቀደም በነበርንበት የሀገር በቀል ዕውቀት ከፍታ ልክ መጓዝ አልቻልንም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በኩር ከሀገር በቀል ዕውቀት ተመራማሪ እና የታሪክ ምሁር ጋር ሙያዊ ማብራሪያን ተቀብላለች፡፡
ማርሸት ግርማይ (ዶ/ር) ይባላሉ፤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሀገር በቀል ዕውቀት ጥናት ማዕከል አስተባባሪ ናቸው፡፡ ማዕከሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለሀገር ዕድገትና ግንባታ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው እና ተገቢውን ጥቅም ለማስገኘት በምርምር እና በጥናት ተደግፎ በትኩረት እየሠራ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ አስቻይ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ስለመሆኑ ነው ዶክተር ማርሸት ያነሱት። አስተባባሪው እንዳብራሩት ማዕከሉ የሀገር በቀል ዕውቀት ሊያድግ የሚችለው የሀገር በቀል ዕውቀት ባለቤቶቹ ተጠቃሚ ሲሆኑ መሆኑን በጽኑ ያምናል፤ የሚያከናውናቸው ተግባራትም ይህን መሠረት በማድረግ ነው፡፡
በሀገራችን በየአካባቢያቸው ቁሳቁስ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ፣ ከአካባቢያቸው ባሉ ዕፅዋት የተለያዩ መድኃኒቶችን እና መዋቢያዎችን የሚቀምሙ ብዙ ሥራ ፈጣሪዎች አሉ፡፡
እነዚህን የዕውቀቱ ባለቤቶች ተጠቃሚ ማድረግ ደግሞ ዘርፉ ያድጋል፤ ካልሆነ ግን ዕውቀቱ ሊጠፋ እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡
ሀገር በቀል ዕውቀት የሕዝብ ሕይወት መሠረት ብቻ ሳይሆን የጊዜ ፈተናን የተሻገረበት ጥበብ ነው።
“ሥር ያለው ዛፍ አይነቃነቅም” እንደሚባለው የአንዲት ሀገር በሁሉም ነገር የተሻለ መሠረት ላይ እንድትቆም መሠረቱ ሀገር በቀል ዕውቀት ነው፤ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው።
እንደ ጃፓን፤ ታይላንድ፣ ሕንድ እና ቻይና የመሳሰሉ ሀገራት በሳይንስና ምርምር የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከበለጸጉ ሀገራት መካከልም ናቸው፤ ለዚህ ሁሉ መሠረታቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች መሆናቸውን ዘመናዊውን ከሀገር በቀል ዕውቀት ጋር ያለውን ታሪካዊ ትስስር እና ተዛማጅ መረጃዎችን የሚያጋራው ሳይንስ ዳይሬክት (www.sciencedirect.com) ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስገነዝባል፡፡
ኢትዮጵያም የበርካታ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ባለቤት ስትሆን እነዚህን ዕውቀቶች ጠብቆ በማቆየት ደግሞ ቤተ ዕምነቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ባለውለታ ናት፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት ከሰው ልጅ መፈጠር እና ስልጣኔ ጋር አብሮ የመጣ፣ ከሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ጥንታዊ ዕውቀት እንደሆነ ነው የታሪክ ድርሳናት የሚያብራሩት።
የሀገራችን ሀገር በቀል ዕውቀት ከዕድሜው ጋር አብሮ ወደፊት መራመድ ባይችልም በአሁኑ ወቅት ግን ትኩረት እየተሰጠው ነው፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የምርምርና ትምህርት ዘርፍ ሆኖ በመካተት እየተሠራ መሆኑ ደግሞ ማሳያ ነው። የዚህ አብነት የሆነው የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የማዕከሉ አስተባባሪ ማርሸት ግርማይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች መካከል ባሕላዊ ሕክምና፣ የግብርና ሥራ ስልቶች፣ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች፣ እደ ጥበብ፣ ባሕላዊ አስተዳደር፣ የዘመን አቆጣጠር ስልቶች እና ሌሎችም ይገኙበታል።
እነዚህ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለሀገር ዕድገትና ግንባታ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ታዲያ በምርምር እና በጥናት አስደግፎ መሥራት ግድ ይላል፤ በጎንደር ዩኒቨርቲ የተቋቋመው የሀገር በቀል ዕውቀት ጥናት ማዕከልም ይህን መሠረት አድርጎ ነው እየሠራ የሚገኘው፡፡
ዘመናዊ ሕክምና ባልተስፋፋባቸው ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሆነ ዘመናዊ ሕክምና በተስፋፋበት በአሁኑ ወቅት የማሕበረሰባችን ባሕላዊ ሕክምና እና መድኃኒቶችን የመጠቀም ዝንባሌው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ባሕላዊ ሕክምና እና መድኃኒቶች በአቅራቢያ ስለሚገኙ፣ የገንዘብ አቅምን የማይፈትኑ እንዲሁም በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታመንባቸውና በተግባርም ፈዋሾች መሆናቸው ነው፡፡
ተክሎችን በቤት ውስጥ የአትክልት ቦታ የመትከል ዝንባሌ አለው፡፡ የእንዶድ ቅጠል ለቢላሃርዝያ በሽታ መዳኃኒት መሆኑ በዶ/ር አክልሉ ለማ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከመተዋወቁ በፊት ብዙ የማሕበረሰባችን ክፍል ባሕላዊ በሆነ መንገድ ሲጠቀምበት መቆየቱ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለሳይንሳዊ ስራዎች መሠረት ለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ማርሸት ማብራሪያ ከሰው ሕክምና በተጨማሪ ዘመናዊ የእንስሳት ሕክምና ተደራሽ ባልሆነበት ዘመን አብዛኛው የእንስሳት ባለቤት ባሕላዊ ሐኪሞችና ቀማሚዎች ከሚሰጡት አገልግሎት ተጠቃሚ ሲሆን ቆይቷል፤ አሁንም በስፋት ይጠቀማል፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ ሀገር በቀልና ባሕላዊ ዕውቀቶችን የያዙ ብዙ መቶ ዓመታትን ያስቆጠሩ መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ሀገር በቀል መድኃኒትን በመጠቀም ህክምና የሚያገኘው ነዋሪ ቁጥር ከፍተኛ ነው፤ ፈዋሽነታቸው ተረጋግጦም ፈቃድ በመውሰድ በዘርፉ የተሰማሩ በርካቶች ናቸው፡፡ አስተባባሪው ያነሱት ሌላው አብት ትምህርትን ነው፤ አብዛኛው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ በአብዛኛው በሀገር በቀል ዕውቀት የተገነቡ ናቸው፡፡
በተለይ ከአክሱም ዘመነ-መንግሥት ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የታዩት የተለያዩ ሀውልቶች፣ ውቅር አብያተ – ክርስትያናት፣ ቤተ – መንግሥቶች፣ የግንብ ሥራዎች እንዲሁም ሌሎች የስነ- ሕንፃ ሥራዎች በማህብረሰቡ ውስጥ ታምቆ የነበረውን የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችሎታ አመላካች መሆናቸውን ዶክተር ማርሸት አብራርተዋል፡፡
ዘርፉን ለማሳደግ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን መነቃቃት መልካም ጅምር መሆኑን ያነሱት ዶክተር ማርሸት፣ “ይህ የሀገር በቀል ዕውቀት ቀጣይነት እንዲኖረው፣ የዕውቀቱ ባለቤቶች ዕውቀቱን መጠቀማቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታት፤ ለንግድ እና ሌሎች ዘርፎች ለሚውሉ የሀገር በቀል ዕውቀቶች እና ምርቶች ከለላ መስጠት፤ እንዲሁም የሀገር በቀል ዕውቀቶችን መሠረት አድርገው የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎችን ማበረታታትና ማስተዋወቅ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
እንደ አስተባባሪው ማብራሪያ መንግሥትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሀገር በቀል ዕውቀት ባለቤቶችና አዋቂዎች እንዲሁም በተመራማሪዎች መካከል የጋራ ጥቅም የሚያስገኝ ትስስር እንዲፈጠር ማድረግ፣ ትስስሩንም መደገፍ አለባቸው፡፡ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በቴክኖሎጂ ደግፎ ለመጠበቅና ለመጠቀም፣ ከለላ ለመስጠት፣ ለመመዝገብና ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲሁም የዕውቀቱን ባለቤቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ መቅረፅ፣ ግንዛቤ መፍጠር፣ በዕውቀቱና በቴክኖሎጂው ባለቤቶች እና ማሕበረሰቡ መካከል የልምድ ልውውጥ ማመቻቸት ይገባል፤ ከዚህ ባለፈም የንግድ ትስስር እንዲኖር ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል።
ኮረጆ
ሀገር በቀል እውቀቶች ምን ምን ናቸው?
ሀገር በቀል እውቀቶች (Indigenous Knowledge) የሚባሉት በሚከተሉት ዋና ዋና ዘርፎች ይጠቃለላሉ፦
- ባሕላዊ ሕክምና እና ጤና አጠባበቅ
ይህ ዘርፍ በኢትዮጵያ በስፋት የሚታወቅና ለብዙ ዘመናት ሕዝቡን ሲያገለግል የቆየ ነው። የዕፅዋት ቅመማን መሠረት በማድረግ የሚሰጥ ሕክምና ነው።
- ግብርና እና አካባቢ ጥበቃ
አርሶ አደሩ ከአየር ንብረቱና ከመሬቱ ጋር ተስማምቶ እንዲኖር ያስቻሉት እውቀቶች ናቸው።
የመሬት አጠቃቀም፣ የሰብል ጥበቃ እና የእንስሳት እርባታ ይጠቃለላሉ።
- የምግብ ዝግጅት እና አያያዝ
የተመጣጠነ እና ለረጅም ጊዜ የማይበላሽ ምግብ የማዘጋጀት ጥበብን ያካትታል።
የማብላላት (Fermentation) ሂደት እና ምግብን የማቆየት ዘዴዎችን ያጠቃልላል።
- የግጭት አፈታት እና ማሕበራዊ አስተዳደር፡- የተለያዩ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ያካትታል፡፡
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


