የሴቶች እግር ኳስ ተስፋዎች እና ችግሮች

0
69

የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ በተለይም በፕሪሚየር ሊግም ሆነ በከፍተኛ ሊግ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢፈራረቁበትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ እና ትልቅ ተስፋን ያዘለ ስፖርት መሆኑ አይካድም:: የሴት እግር ኳስ ሊጎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር በተሻለ መዋቅር መመራታቸው እና አዳዲስ አሰራሮች መጀመራቸው ብሩህ ተስፋን ፈጥሯል፤ እየፈጠረም ይገኛል:: በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገራችን ኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ እያደገ እና የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ ቢመጣም ከስር መሰረቱ የተተከሉ በርካታ ችግሮች ስፖርቱን ወደሚገባው ከፍታ እንዳይደርስ ውስብስብ አድርገውታል::

እነዚህ ችሮች ከኢኮኖሚ እጦት እስከ ማህበራዊ አመለካከት፤ ከመሰረተ ልማት እጥረት እስከ ደህንነት ስጋት መሆናቸውን በሴቶች እግር ኳስ ላይ 26 ዓመታት ያገለገለው አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግሯል:: በሀገራችን “እግር ኳስ የጉልበት ጨዋታ ስለሆነ ለወንዶች ብቻ የተፈጠረ ነው” የሚል የተዛባ አመለካከት አሁንም ድረስ በስፋት ይንጸባረቃል:: አንዲት ሴት ልጅ እግር ኳስን መጫወት ስትጀምር ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት እና ከማህበረሰቡ የሚደርስባት ስነ ልቦናዊ ጫና ቀላል የሚባል አይደለም:: ኳስ ከመጫወት ይልቅ በቤት ውስጥ ሥራዎች እንድትጠመድ ወይም ለሴት ልጅ የሚመጥን ተብሎ የተፈረጀውን የህይወት መስመር እንድትከተል ትገደዳለች:: ይህ አይነቱ ማህበራዊ መገለልና ተቃውሞ በርካታ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊ ሴቶች ገና በልጅነታቸው ህልማቸውን እንዲቀጩ እና ከስፖርቱ ዓለም ርቀው እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል ተብሏል::

የሴቶች እግር ኳስ ፈተና የሚጀምረው የገንዘብ እና የደመወዝ ልዩነት መሆኑን አሰልጣኝ ብርሃኑ ያስገነዝባል:: ሴት ተጫዋቾች ልክ እንደ ወንድ አቻዎቻቸው ላባቸውን ጠብ አድርገው፣ ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን ሰውተው ቢጫወቱም የሚያገኙት ክፍያ ግን የሰማይ እና የምድር ያህል የተራራቀ ነው:: ይህ የደመወዝ ልዩነት በታዳጊ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በበለጸጉትም ሀገራት በስፋት የሚታይ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን አሰልጣኝ ብርሃኑ ይናገራል። ትልልቅ ኩባንያዎች እና ባለሀብቶች የሴቶችን ዘንግተው ሀብታቸውን በወንዶች እግር ኳስ ላይ ብቻ ለማፍሰስ ሲሽቀዳደሙ ይስተዋላል፤ ይህም ተጫዋቾቹ በሙሉ ልባቸው በስፖርቱ ላይ ብቻ ትኩረት እንዳያደርጉ ትልቅ እንቅፋት ይሆንባቸዋል::

በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ላይ ጥላውን ያጠላው እና አሁንም ድረስ አነጋጋሪ የሆነው ሌላኛው  ተግዳሮት በክለቦች ውስጥ ያለው የፋይናንስ እና የመሰረተ ልማት ችግር ነው:: አብዛኞቹ ክለቦች ውስጥ የሚታየው የወንዶች እና የሴቶች ቡድን የፋይናንስ፣ የጥቅማጥቅም ልዩነት ፍትሃዊነት የጎደለው እንደሆነ አሰልጣኝ ብርሃኑ ይናገራል:: ይህም የተጫዋቾች ደመወዝ፣ መጓጓዣ እና ስልጠና ጥራት ላይ በቀጥታ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል:: “በአንድ ክለብ ስር ያሉትን የሴቶችንም የወንዶችንም ቡድን እኩል ማየት ሲገባ አሁን ያለው አሰራር ግን አድሎአዊ አሠራር ያለበት ነው” ይላል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ::

በከፍተኛ ሊጉም ሆነ በፕሪሚየር ሊጉ የሚወዳደሩ የሴቶች ክለቦች ጥራት ያላቸው የልምምድ ሜዳዎች እና ዘመናዊ የመለማመጃ መሳሪያዎች እጥረት አለባቸው:: “ብዙ ጊዜ የሴት ቡድኖች በክለቦቻቸው የሚሰጣቸው የልምምድ ሰዓት እና የሜዳ ጥራት ከወንዶቹ ያነሰ ነው:: ይህ የተጫዋቾችን የክህሎት እድገት እና አጠቃላይ የሊጉን የውድድር ጥራት በእጅጉ ይቀንሳል” ብሏል አሰልጣኝ ብርሃኑ:: አንዲት ሴት ተጫዋች ሙሉ ጊዜዋን ለክለቧ ስትሰጥ አነስተኛው የሚጠበቀው ነገር የጤና እና የሥራ ዋስትና ነው:: ሆኖም በሁለቱም ሊጎች የሚጫወቱ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ተገቢ የጤና እንክብካቤ፣ የህክምና ኢንሹራንስ እና አስተማማኝ የውል ስምምነት ዋስትና አይደረግላቸውም:: በዚህ ምክንያት ጉዳት በሚያጋጥማቸው እና ጡረታ በሚወጡበት ጊዜ በእግር ኳስ ህይወታቸው እና በግል ህይወታቸው  አደጋ ይገጥማቸዋል::

የፕሪሚየር ሊግ እና የከፍተኛ ሊግ ክለቦችን ወደ ኋላ ከሚጎትቱት ሌላኛው ችግር ከሜዳ ውጪ ያሉ ተጽዕኖዎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ:: የሴቶች ሊግ ውድድሮች በመገናኛ ብዙኃን ያላቸው ሽፋን እጅግ ዝቅተኛ ነው:: “ ዜና ሲያጡ የዜና ሽፋን ለመሸፈን ነው እንጂ ሥራዬ ነው ብለው የሊጉን ጨዋታዎች የሚከታተሉ ጥቂት ናቸው” በማለት የሴቶች ሊግ ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን እያገኙ አለመሆኑን ይጠቅሳል:: የመፍትሄው አካል መሆን የነበረባቸውና የሊጉን ክለቦች በዋናነት የሚመሩት አንዳድ አሰልጣኞች በሴቶች እግር ኳስ ውስጥ የፈጠሩት የስነ ምግባር ክፍተት እጅግ አሳሳቢ እንደሆነም አሰልጣኝ ብርሃኑ አልሸሸገም::

አሰልጣኞች ለሴት ተጫዋቾች አርአያ መሆን ሲገባቸው በተቃራኒው የሚጓዙ አሉ:: “ከተጫዋቾቹ ጋር ቁማር የሚጫወት፣ ከነሱ ጋር ገንዘብ የሚበደር፣ እንደገና እንደ ደላላ ሆኖ ደግሞ እነሱን የሚያጠቃ መሆን የለበትም” በማለት ሙያዊ ክብር የጎደላቸው ተግባራት በሴት ተጫዋቾች ላይ ምን ያህል የስነ ልቦናና የሞራል ስብራት እየፈጠሩ መሆኑን በአጽንኦት ያስረዳል:: ተጫዋቾችን ለግል ጥቅም ማዋል የክለቦችንም ሆነ የሊጉን እድገት የሚያቀጭጭ ትልቅ ነቀርሳ መሆኑንም አሰልጣኝ ብርሃኑ ተናግሯል::

በኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶች ከፖሊሲና አስተዳደር (የሊግ ፎርማት ጥራት፣ የክለቦች አስተዳደር ድክመት) አንስቶ እስከ ማህበራዊ አመለካከት ድረስ የተንሰራፉ ናቸው:: ነገር ግን እነዚህን ውስብስብና ስር የሰደዱ ችግሮች ተሻግሮ የሴቶችን የክለብ ውድድር ወደተሻለ የከፍታ ደረጃ ለማድረስ ቁልፉ በእጃቸው እንደሆነ አሰልጣኝ ብርሃኑ ጠቁሟል:: ትልቁ መፍትሄም በክለቦች አስተዳደር ውስጥ የአመለካከት ለውጥ) ማምጣት መሆኑን አንጋፋው አሰልጣኝ ያስገነዝባል:: ለሴቶች ቡድን የሚሰጠው ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን አለበት:: ክለቦች ሴት ተጫዋቾችን ማግለል፣ ትኩረት አለመስጠት እና አድልዎ መፍጠርን ከስፖርቱ መድረክ ሊያስወግዱ ይገባል ነው ያለው አሰልጣኙ:: የሴቶች እግር ኳስን ከዚህ አዘቅት ውስጥ አውጥቶ ብሩህ ወደሆነው መድረክ ለማሸጋገር የመንግሥት የስፖርት ተቋማት፣ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የክለብ አመራሮች፣ የሊግ ካምፓኒው ሚዲያው እና የግሉ ዘርፍ በአንድነት መስራት አለባቸው::

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here