የማሕፀን መውጣት  ምንነት እና ሕክምናዎቹ

0
108

“በእኛ ማሕበረሰብ በተለይም በገጠሩ አካባቢ ስለመራቢያ አካላት ማውራት ወይም መረጃ መለዋወጥ እንደ ነውር ስለሚታሰብ አብዛኛዎቹ እናቶች ችግር ሲያጋጥማቸው እንኳን ለሐኪም ለሚቀርቡት የቤተሰብ አባል አያሳውቁም:: ከዛ ይልቅ ‘በኃጢአቴ የመጣ ነው፣ ይሄ በእኔ ብቻ የተከሰተ ነው’ ብሎ የማመን ሁኔታ አለ::” በማለት አስተያየታቸውን ለበኵር ጋዜጣ የሰጡት በደብረ ታቦር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የማሕፀን እና የፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም  ዶ/ር ሹምዬ አድማሱ ናቸው::

የሕክምና ባለሙያው የማሕፀን መውጣት ወይም መንሸራተት ምን ማለት ነው? ሕክምናዎቹስ ምንድን ናቸው?… በሚሉት ዙሪያ ምላሽ ሰጥተውናል:: ዶ/ር ሹምዬ አድማሱ እንዳብራሩት በተለምዶ ማሕፀን ሲባል የሽል ቤት ወይም ልጅ የሚያድግበት ቦታ ማለት ነው::  ታዲያ ማሕፀንን  ባለበት እንዲቆይ ወይም  በሚገባው ቦታ እንዲቀመጥ የሚያስችሉ አቅፈው የሚይዙ ጡንቻዎች እና ጠንካራ ጅማቶች አሉ:: ይሁንና እነዚህ ጅማቶች በተፈጥሮ ወይም በአደጋ እና በሌሎች አጋላጭ ምክንያቶች የተነሳ ጉዳት ሲደርስባቸው ይዝላሉ ወይም ይላሉ:: በፊት የነበራቸውን ጥንካሬም ያጣሉ:: በዚህ ጊዜ ማሕፀን የነበረበትን ቦታ ለቀቅቆ ወደ ታች ይንሸራራተታል ወይም  ወደ በብልት በኩል ወደ ውጭ ይወጣል::

እንደ ዶ/ር ሹምዬ ገለጻ ለማሕፀን መንሸራተት አጋላጭ ምክንያቶች  90 በመቶው   ከወሊድ ጋር የተያያዘ ነው:: አንድ እናት ስታረግዝ የሆድ ዕቃዋን እና ሆዷን ወይም ፔልቪክ (Pelvic) የሚባለውን  አቅፎ የሚይዘው አካል ይለጠጣል:: በመሆኑም ማርገዝ በራሱ አንድ አጋላጭ ምክንያት ነው::

የተራዘመ ምጥ (Prolonged labor)፣ በሐኪም ያልታገዘ ወሊድ፣ በልጅነት ልጅ መውለድ(ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች ሲወልዱ)፣ ከአምስት እና ከዛ በላይ ልጅ መውለድ ለማሕፀን መንሸራተት አጋላጭ ናቸው:: ይሁንና  በቀዶ ጥገና  አንድ ወይም ሁለት ልጆች  የወለደች እናትም የማሕፀን መንሸራተት ሊገጥማት እንደሚችል ልብ ሊባል ይገባል:: ሌላው ከባድ እቃ የሚያነሱ፣ በመውደቅ ምክንያት ዳሌያቸው አካባቢ ስብራት ወይም ጉዳት ያጋጠማቸው፣  የወር አበባ ማየት ያቆሙ(ያረጡ) እናቶች ከሚያጋጥማቸው የሰውነት የሆርሞን ለውጦች ጋር ተያይዞ የመራቢያ አካላቸው እና በአካባቢው ያሉት የሰውነት መዋቅሮች (ጅማቶች) ይኮማተራሉ፤ መጠናቸውም ይቀንሳል:: በዚህ ጊዜም አቃፊ አካላትም  የመሳሳት ወይም ደግሞ የአቅም ማነስ ይገጥማቸዋል:: በተለይ ከሀምሳዎች እና ከዛ በላይ እድሜያቸው  ያለፈ ሴቶች  ተጋላጭ ናቸው::

የሆድ እቃ ላይ ጫና የሚፈጥሩ (ረጅም ሰዓት የቆየ የሆድ ድርቀት፣ ያልታከመ ሳል፣ ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት፣ እና የሆድ እጢ) ወደ ታች የመግፋት አቅም ስለሚኖራቸው  የማሕፀን መንሸራተቱን እንደሚያባብሱ ባለሙያው ተናግረዋል::

የማሕፀን መንሸራተት ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

ባለሙያው እንዳሉት  የማሕፀን መንሸራትት በአንድ ጊዜ የሚመጣ ሳይሆን ቀስ በቀስ በዓመታት ሂደት የሚከሰት ነው:: አንዲት ሴት  ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት ሕክምና ሳታገኝ ከችግሩ ጋር ልትቆይ ትችላለች:: ምልክቶቹም  ቶሎ ቶሎ ሽንት መምጣት፣  ለመሽናት መቸገር፣ ፊኛ ላይ የመክበድ ስሜት፣ ማሕፀንን ወደ ታች የሚጎትት ስሜት መኖር እንዲሁም የጀርባ ሕመም በአብዛኛው በሽታው በተከሰተባቸው እናቶች ላይ ይኖራል:: ሲባባስ ደግሞ ማሕፀን በአጠቃላይ ወደ ውጭ በመውጣት ለንፋስ ይጋለጣል፤ ሲጓዙ ደግሞ በጭናቸው መካከል በመፋተግ መላጥ እና መድማት ይከሰታል::

የማሕፀን መንሸራተት ሕክምናው

አብዛኛውን ጊዜ እናቶች የማሕፀን መውጣት ወይም መንሸራተት የሚታከም እንደማይመስላቸው  ባለሙያው ተናግረዋል:: ሕመሙ እንደ ጀመራቸውም በፍጥነት ወደ ሕክምና ቦታ ስለማይመጡ  ጤናቸው ይታወካል:: በዚህ የተነሳም ከትዳር አጋራቸው ጋር የተለያዩ በርካታዎች እንደሆኑ ዶ/ር ሹምዬ አስገንዝበዋል::

ዶ/ር ሹምየ እንዳብራሩት  ሕክምናው የሚጀምረውም ለማሕፀን መንሸራተት አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶችን በማከም  ነው:: ለአብነትም የሆድ ድርቀትን በቂ ውኃ በመጠጣት እና አትክልት እና ፍራፍሬ በማዘውተር ማስወገድ፣ ተመጣጣኝ የሰውነት ክብደት እንዲኖር ማድረግ፣ ለረጅም ጌዜ የቆየን ሳልም በማከም ማዳን ይቻላል:: ከወሊድ በኋላም ሰውነትን ከእርግዝና በፊት ወደ ነበረበት (Pre-pregnancy state) እንዲመለስ በአራስነት ጊዜያቸው  በአግባቡ መመገብ ተገቢ ነው::

ሕክምናዎቹም  ሕመሙ እንዳለበት ደረጃ ስለሚወሰን አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የማሕፀን መንሸራተት ያለባቸው  እናቶች ማሕፀናቸው ወደ ቦታው እንዲመለስ ወይም ደረጃው እንዳይባባስ የማሕፀን ጡንቻ እንቅስቃሴ መሥራት ይኖርባቸዋል:: በተለይም ኬግል (kegel Exercise)  የሚባለው የስፖርት እንቅስቃሴ ፍቱን እንደሆነ ነው ያብራሩት:: ኬግል የሚባለው እንቅስቃሴ  ሽንት ሲመጣ እንዳያመልጠን የምንይዝበት ሂደት ማለት ነው፤ ይህንን ተግባር  ደጋግመው በቀን እስከ ሃያ ጊዜ መሥራት ይመከራል:: ከአንደኛ እና ከሁለተኛ ደረጃ አልፎ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ የደረሰ የማሕፀን መንሸራተት ወይም መውጣት ግን  የቀዶ ጥገና ሕክምና ማድረግ አማራጭ ይሆናል ማለት ነው::

ሌላው በአነስተኛ መጠን እና በተለያዩ ቅርጾች የተሠሩ የፕላስቲክ ድጋፎችን (Pessaries) በብልት ውስጥ በማስገባት ማስተካከል ይቻላል:: ይህ የሕክምና ዓይነት የቀዶ ሕክምና ለማይፈልጉ እና ለዚህ ዓይነት ሕክምና ለማድረግ የጤናቸው ሁኔታ ላልፈቀደላቸው ሴቶች አንደ አማራጭ ሆኖ ያገለግላል:: አንዲት እናት መውለድ ይበቃኛል ካለች  ግን ሕክምናው የሽል ቤቱን አጠቃላይ ማውጣትንም እንደ ሚጨምር ባለሙያው ጠቁመዋል::

መከላከያዎቹ ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ሹምዬ እንዳሉት  አንዲት ሴት መውለድ እስካላቆመች ወይም እስከ ወለደች ድረስ የማሕፀን መንሸራተት ሊያጋጥማት ይችላል:: ይሁንና ችግሩ ሳይከፋ መታከም ይቻላል:: በመሆኑም ከዚህ ሕመም ለመጠበቅ እናቶች የወሊድ ሂደታቸውን በሕክምና ተቋማት በባለሙያ የታገዘ ማድረግ ይኖርባቸዋል:: በባለሙያ ሲታገዙ ረጅም ሰዓት እንዳያምጡ፣ ማማጥ ከሌለባቸው ደግሞ በሌላ መንገድ (በቀዶ ጥገና) እንዲወልዱ የሚደረግበት መንገድ ይኖራል::

ልጅን በእቅድ አራርቆ እና መጥኖ መውለድም ሌላው የመከላከያ መንገድ ነው::  ችግሩ በሚፈጠርበት ጊዜም እንዲህ አይነት ሕመም በሐጢያት ምክንያት እንዳልመጣ እና ማኝኛዋንም ወላድ ሴት ሊያጋጥማት እንደሚችል ማወቅ እና የጤና ባለሙያዎችን ማማከር መፍትሔ  መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ እንደሆነ መክረዋል::

መረጃ

 

በዓለም አቀፍ ደረጃ የማሕፀን መውጣት (Uterine Prolapse) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን የሚያጠቃ የጤና ችግር ነው፡፡ የችግሩ ስርጭት እንደ ሀገራቱ የኢኮኖሚ እድገትና እንደ ምርመራው ዓይነት ይለያያል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሁለት እስከ 20 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በማሕፀን መውጣት  ችግር እንደሚጠቁ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

እ.አ.አ በ2021 በተደረገ ጥናት በዓለም ዙሪያ 140 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች የማሕጸንና የሌሎች የዳሌ ውስጥ አካላት መውጣት (Pelvic Organ Prolapse) ችግር እንዳለባቸው ተመዝግቧል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ  በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የተጋላጮች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን፣ ይህም እስከ 20 በመቶ እና ከዚያ በላይ ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል፡፡

 

ምንጭ፡- National Institutes of Health (NIH)፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here