የአውሮኘላን በረራ አድናቂ እና ጥልቅ ስሜት ያደረበት የ14 ዓመቱ ታዳጊ ቼ ጂንጋንግ በንባብ ራሱን በራሱ በማስተማር በእጁ የጄት ሞተር ሰርቶ ለመሞከር መዘጋጀቱን ዩፒ አይ ድረ ገጽ አስነብቧል::
ታዳጊው የመለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው:: ገና በለጋ እድሜው ለአውሮኘላን በረራ ትምህርት ጥልቅ ፍላጐት ያለው በመሆኑ በወረቀት በዓየር ላይ ተንሳፋፊ ቅርፅ በመስራት ያበር ነበር::በወረቀት ኳስ እንዲሁም የአውሮኘላን ቅርፅ ሰርቶ በመወርወር ልዩነቶችን መገንዘቡን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው::
በዚህም መኖሪያ ክፍሉን ቤተሙከራ እንዳስመሰለው ነው የተጠቆመው::እንደወላጆቹ ገለፃ ጂንጋንግ በቀን ለሦስት ሰዓታት ስለዓየር በረራ የተፃፉ የሳይንስ መፃህፍትን ያነብ ነበር:: ሦስተኛ ክፍል ላይ ሳለም “ካልኩለስ” ወይም የቁጥር ስሌት፣ በወረቀት ላይ የታተሙ ስለአውሮኘላን በረራ እና እንቅስቃሴ የሚያወሳ የኮምፒዩተር ኘሮግራሞች እና በ(‘ሲኤዲ’) ኮምፒዩተር ኤይድድ ዲዛይን እየታገዘ ንድፍ መስራት ችሏል::ታዳጊው በአንድ ወቅት በ”ኦንላይን” ያገኘውን ስልጠና መሰረት አድርጐ በተግባር ሊታይ የሚችል ውጤት ለመስራት እና ለማሳየት ይወስናል:: በዚሀ ውሳኔው የሌሎችን ንድፍ ከመገልበጥ ይልቅ መማር እንደሚችል በመወሰን የራሱን መንደፍን ይያያዘዋል:: ከምንም በላይ በራሱ ጥረት በእጁ ወረቀት ላይ ከዚያም ቀስ በቀስ በኮምፒዩተር ለመስራት ጥረት አድርጓል:: የዓየር ግፊቱን፣ የሞተሩን እንቅስቃሴ በምስለ ሙከራ በቻይናው የቲክቶክ ማህበራዊ ገፅ “ዶዩን”የደረሰበትን ደረጃ ለብዙዎችም አጋርቷል::
ስራውን የተመለከቱ መሰሎቹ የሰጡትን አስተያየትም በግብአትነት ተቀብሏል፤ የሚበጅት አካቷል:: ከስድስት ወራት በኋላም የተሻሻለ የስራ ውጠቱን አጠናቆ ለመሞከር በዝግጅት ላይ መሆኑን በማጠቃለያነት ድረ ገጹ አስነብቧል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዚያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


