ስለከተማ ልማት  የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን አሉ?

0
77

በኢትዮጵያ በመጭው ግንቦት ወር ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን እያስተዋወቁ ነው፤ ከሰሞኑም በከተማ ልማት ፖሊሲ አማራጮች ዙሪያ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለሕዝብ አስተዋውቀዋል:: ተሳታፊዎቹ ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኀይሎች ንቅናቄ (አዴኀን)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና ብልጽግና ፓርቲዎች ናቸው:: ቅደም ተከተሉ በዕጣ መሆኑን ልብይሏል::

አዴኀን

ፓርቲውን በመወከል የተገኙት አቶ ራስወርቅ መላኩ እና  አቶ ኤፍሬም መንገሻ ናቸው:: አቶ ራስወርቅ መላኩ  ባደረጉት ንግግር   የኢትዮጵያ የከተማ ዕድገት ካለፉት ሁለት ዐሥርት  ዓመታት ጋር ሲነፃፀር  ዕድገት አሳይቷል፤ ይሁን እንጅ ዕድገቱ በመንግሥት የሚመራና ያልተመጠነ፣ ፖለቲካ መር በመሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም::

በኢትዮጵያ የከተማ ፖሊሲ አጅግ የተማከለ መሆኑን ያነሱት አቶ ራስወርቅ፤ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በመሬት ምደባ፣ በከተማ ዕቅድ አዘገጃጀት እና  የኢንስትመንት ቅድሚያ  ቦታ አሰጣጥ ላይ  ጠንካራ  ቁጥጥር ይደረጋል ነው ያሉት:: ይህም በፖለቲካ ፍላጐት ላይ የተመሠረተ የከተማ መስፋፋት፣ ደካማ የከተማ አስተዳደር እና  የሕዝብ ተሳትፎ ማስከተሉን ጠቁመዋል::

የመሬት ባለቤትነት የመንግሥት መሆኑ ሌላው ችግር ነው ያሉት ተወካዩ ይህም ያልተረጋጋ የመሬት እጥረትን ስለማስከተሉ ተናግረዋል:: ይህ ደግሞ ክልሉ ለረጅም ጊዜ የኢንቨስትመንት ዕቅድ ላላቸው ሰዎች መዳረሻ እንዳይሆን አድርጐታል ባይ ናቸው:: “የመሬት ሊዝ ሥርዓት ግልጽ ያልሆነ እና ለሙስና የተጋለጠ በመሆኑ የመሬት እጥረትን እስከትሏል ብሎ አዴኀን ገምግሟል” ብለዋል::

አቶ ራስወርቅ አክለውም ምጣኔ ሀብቱ ከከተማ የመሬት ፖሊስ ጋር የተሳሰረ አለመሆኑን በተጨማሪ ችግርነት አንስተዋል:: ይህም ሥራ አጥነት እንዲስፋፋ ማድረጉን  ጠቁመዋል::

በከተሞች የሚታየው እንቅስቃሴ ሕገ ወጥ እና ያልተመዘገበ ኢኮኖሚ በመሆኑ የመሬት ንግድ፣ ኮንትሮባንድ፣ ግብር መሰወርና መሰል ችግሮች የከተሞችን መሠረት እያናጉ ስለመሆኑ አዴኀን መገምገሙን አስታውቀዋል::

በአሁኑ ወቅት በከተሞች ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ ያልተመጣጠነ እና በፖለቲካ ፍላጎት የሚመራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ራስወርቅ ዜጐች የመኖሪያ ቤት፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ እና የመጓጓዥ እጥረት እንደገጠማቸው ዘርዝረዋል::

“የውኃ ማማ በምትባለው ሀገራችን ውስጥ የከተማው ሕዝብ ውኃ እየተመጠነለት በስምንት ቀን አንድ ጊዜ እንዲያገኝ መሆኑ የከተማ ልማቱን ደካማነት ያሳያል:: የውኃ እጥረቱ በእያንዳንዱ የአማራ ክልል ከተሞች ከሳምንት በላይም ሊዘል ይችላል” ብለዋል:: በአማራ ክልል የትራንስፎርመር እጥረት መኖሩን በማንሳት ይህም “የከተሞች ዙሪያ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንዳይሆኑ አድርጓል” ነው ያሉት::

በዚህም በክልሉ ያሉ አምራች ኢንድስትሪዎች በትራንስፎርመር እጥረት ምክንያት አምራች ሳይሆኑ ቀርተዋል:: ከተማ አስተዳደሮችም የየራሳቸውን ገቢ ማመንጨት ስለማይችሉ የፋይናንስ ነጻነት የሌላቸው እና በቤተሰብ ትስስር የተሞላ እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጡ ደካማ እና በሙስና የተተበተበ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል::

አዴኀን ታዲያ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ከተሞች የዕድገት እና የሥልጣኔ መፍለቂያ  እንዲሆኑ እንደሚሠራ አስታውቋል::

ኢዜማ

አቶ ኃይለማርያም ብርሐኑ እና አቶ ይበልጣል አድማሴ ፓርቲውን ወክለው የተገኙ አባላት ናቸው::  የፓርቲያቸውን የከተማ ልማት ፖሊሲ ያቀረቡት  አቶ ኃይለማርያም ብርሐኑ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ታይቶ በማይታወቅ የከተሞች መስፋፋት ውስጥ እንደምትገኝ ተናግረዋል፤ ይሁን እንጂ ዕቅዱ ሳይንሳዊ ያልሆነና ያልታቀደ፣ የዜጐችንም ፍትሐዊነት ያላረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል:: “ኢዜማ ታዲያ ለእነዚህ ማሕበራዊ ችግሮች ጥልቅ መፍትሔ እና አዲስ የከተማ ፖሊሲ ይዞ ቀርቧል” ብለዋል::

ኢዜማ ከተሞች  በማንነት አጥር ሳይሆን በዜግነት ክብር እና በእኩልነት እንድትመራ  እንደሚያደርግ የተናገሩት ተወካዩ፤ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ከተማ የመኖር፣ የመሥራት እና የመተባበር  ሙሉ መብቱ የተከበረ ይሆናል” በማለት አብራርተዋል::

ኢዜማ የመሬት ፖሊሲው የጥቂት ደላሎች እና ካድሬዎች መበልጸጊያ ስለመሆኑ አንስተዋል:: ኢዜማ ከተመረጠ ይህን ችግር ከመሠረቱ እንደሚፈታ በመጠቆም  “መሬትን ከመሬት ደላላ ያላቅቃል፣ የመሬት ምዝበራን በቆራጥነት  ያስቆማል እንዲሁም የመሬት  አስተዳደርን በሙሉ በግልጽ የዲጀታል ሥርዓት በመተካት ከሰው ንክኪ ነጻ ያደርጋል” ብለዋል:: በተጨማሪም “የመሬት ልማት ፖሊሲው  መንገድን፣ ውኃን፣ ኤሌትሪክን እና ማፋሰሻን በአንድ በተሳሰረ የኮሪደር ግንባታ እንዲከናወኑ ያደርጋል” ነው ያሉት::

ዲጅታል ትራንስፎርሜሽንም ሙስናን የመዋጊያ እና የማኅበራዊ ፍትሕ ዋነኛ ማስፈኛ አድርገው እንደሚተገብሩትም አስታውቀዋል:: ኢዜማ ከተመረጠ ለዜጐች ቤት መሥሪያ በዝቅተኛ ወለድ እስከ 30 ዓመት የሚቆይ ብድር የሚያገኙበትን መንገድ እንደሚያመቻችም ተናግረዋል::

ብልጽግና ፓርቲ

ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተገኙት አቶ እንድሪስ አብዱ እና ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) ናቸው:: የፓርቲውን የከተማ ልማት ፖሊሲ ያቀረቡት ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) ብልጽግና ፖርቲ ከተሞችን የመኖሪያ ቤት እሳቤ ብቻ ሳይሆን አካታች ጽኑ ራዕይ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተናግረዋል:: ፓርቲው መደመርን እንደ መንገድ በመከተል የከተሞችን ችግር ወደ ልማት ዕድል በመቀየር የልማት እምርታን ለማምጣት ስትራቴጂ ማስቀመጡንም አክለዋል::

“ዋናው ግባችን ከተሞችን የጋራ መኖሪያ ማድረግ፣ ፍትሐዊ የቤት አቅርቦትን ማረጋገጥ ነው” ያሉት ዶክተር ሞላ፤ ብልጽግና  ከተሞችን የልማት እና የዴሞክራሲ ማዕከል ለማድረግ የተመሰከረላቸውን ጅምር ሥራዎች ማከናወኑን አመላክተዋል::

በተመሳሳይ የገጠር ከተማ አሰፋፈርን በማጠናከር  ፓርቲው አቅሙን  እያሳዬ ስለመሆኑ አንስተዋል፤ “ፖለቲካውን  እና ምጣኔ ሀብቱን ለማሳደግ ከተማ ትልቅ አቅም እንደሆነ የብልጽግና ፓርቲ እምነት ነው” ብለዋል::

ዶክተር ሞላ መልካሙ እንዳሉት የከተማ የኢኮኖሚ ምንጮች ዘርፈ ብዙ ናቸው::  ባለፉት የለውጥ ዓመታት የከተማ ልማት ሥራዎች በጽናት እና በፈጠራ ተፈጽመዋል፤ የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ጀምሮ ወደ ትላልቅ ከተሞች ስለመስፋፋቱ ተናግረዋል::

እንደ ዶክተር ሞላ ገለጻ በአማራ ክልል ሪጂኦ ሜትሮፖሊታንት ከተሞችን ጨምሮ 333 የመንገድ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የመዝናኛ ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ለበርካታ ዜጐች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል:: የባሕር ዳር የጣና ዳር፣ የጎንደር ቅርስ፣ የደሴና የኮምበልቻ ከተሞች የመንገድ እና የተጎሳቀሉ አካባቢዎችን ማልማትም ምሳሌዎች ሆነዋል::

እነዚህ ኘሮጀክቶች የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የሕዝብን አጋርነት በማረጋገጥ ከተሞች ለነዋሪው እና ለቱሪዝም እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ እና የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ ዓላማቸው መሆኑን ተናግረዋል:: “የኮሪደር ልማት ከተሞችን ለማልማት ብቻ ሳይሆን የቀጣይ የልማት አቅጣጫዎችን የቀረፀ ምርጥ ስትራቴጅ ነው” ያሉት የፓርቲው ተወካይ “በእነዚህ ታሪካዊ እጥፋቶች ብልጽግና ፖርቲ ሁለንተናዊ የለውጥ አቅሙን በተግባር በማሳየት የከተማ ልማትን ትክክለኛ  አቅጣጫ አመላክቷል” ነው ያሉት::

በታሪክ አጋጣሚ ዘመናዊ የከተማ ገጽታ ያልነበራቸው የተጎሳቆሉ የከተማ ማዕከላት የነበሩ አካባቢዎችን ፓርቲያችን እምቅ ሀብታቸውን በመጠቀም በዕቅድ እና በይዘት ቀይሯቸዋል:: ነዋሪውን ከልማቱ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ እና አካታች የመልሶ ግንባታ  ልማትን በማካሄድ የኑሮ ውድነቱን የሚያሻሻል ፓርቲ መሆኑንም ገልጸዋል::

ዶክተር ሞላ እንደተናገሩት ብልጽግና ፓርቲ ከለውጡ በፊት የነበረውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ባለፉት አምስት ዓመታት 210 ሺህ ቤቶች በመንግሥት፣ በሕብረት ሥራ ማሕበራት እና በግሉ ዘርፍ እንዲገነቡ አድርጓል:: ለግሉ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት በቀጣይ አምስት ዓመታት ግማሽ ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ይዟል::

ብልጽግና ፓርቲ የከተሞችን አገልግሎት የሚያስፋፋ ዘመናዊ አሠራሮችን በ80 ማዘጋጃ ቤቶች እየተገበረ ሲሆን የአሠራር ቅልጥፍናም እየተረጋገጠ ይገኛል:: ከዚህ ጎን ለጎን ከተሞች ዘመኑን የዋጀ አሠራር እንዲኖራቸው በ85 ከተማ አስተዳደሮች እና በ643 የቀበሌ አስተዳደሮች ዘመናዊነትን የሚያሳድግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ዘርዝረዋል::

በተጨማሪም “ብልጽግና ፓርቲ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዲጅታል ስትራቴጂ መር ማዕቀፍ አድርጎ በመተግበር ላይ ይገኛል:: እንዲሁም በክልሉ በዘጠኝ ከተሞች የዲጅታል ሥርዓቱን ለማሳደግም እየተሠራ ነው:: የአገልግሎት አሰጣጡን እና የሲቪል ሥርዓቱን ለማሳደግም ፓርቲው በትኩረት እየሠራ ነው” ብለዋል::

ፓርቲያችን በአረንጓዴ ልማት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በሽዎች የሚቆጠሩ ሄክታር መሬት ማልማት ችሏል:: በከተማ ግብርናም በአማራ ክልል ብቻ ሩብ ሚሊዮን ዜጐች ተጠቃሚ ሆነዋል:: ባለፉት ዓመታት ለሀገራዊ ዕድገት ብሔራዊ ምርጫ ድርሻው 55 በመቶ በመሆኑ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል::

እንደ ዶክተር ሞላ ማብራሪያ ብልጽግና ፓርቲ የዜጐችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሳካት፣ በኮሪደር እና አረንጓዴ ልማት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው:: ሰው ተኮር አቀራረቦች ላይ ይበልጥ በማተኮር ከተሞችን ሳቢ(ስማርት0 እና አረንጓዴ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረትም አንስተዋል::

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here