ማረስ ነው እንጂ እርፍ እስኪለመጥ፣
ያሳፍር የለ መሶብ ሲገለጥ፡፡
የሚለው ኢትዮጵያዊ ብሂል አርሶ አደሩ ለመኸር ምርት ቀድሞ ማሳውን አለስልሶ፣ አርሶ፣ ዘርቶ፣ አርሞ፣ አጭዶ እና ወቅቶ ተገቢውን ምርት ካላገኘ ቤተሰቡ ጠግቦ ማደር እንደማይችል እና እንግዳ ሲመጣም በበቂ ማስተናገድ እንደማይችል ሸንቆጥ የሚያደርግ ነው፡፡ ለዚህ መፍትሔው ደግሞ ስንፍን ታግሎ በወቅቱ የእርሻ ሥራን ማከናወን ተገቢ መሆኑ ታምኖበት መንግሥት እና አርሶ አደሩ ለመጭው የመኸር ምርት ውሏቸውን ከማሳቸው አድርገዋል::
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በተለይም ግንባር ቀደም(ሞዴል) አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችላቸውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ በማጠናቀቅ ላይ ናቸው። በክልሉ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ጥሩ ሰላም ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር የሺዋስ ዓላምር ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት አካባቢው ላይ እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ ተጠቅመው ማሳቸውን በተደጋጋሚ በማረስ ለመኸር እርሻ አዘጋጅተውታል። “ካላረሱ አይጎርሱ!” የሚሉት አርሶ አደር የሺዋስ በመጭው የመኸር ወቅት በዋናነት ጤፍ፣ በቆሎ እና በርበሬ ያመርታሉ፡፡ እንደ ጓያ እና ሽምብራ ያሉ ጥራጥሬዎችንም በተጨማሪ ያመርታሉ።
ለምርት ዘመኑ በቂ የሆነ አቅርቦት እንዳለም አርሶ አደሩ ለበኵር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የማዳበሪያ ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱን ጠቁመዋል። እሳቸውም ለሚያለሙት ሰፊ ማሳ ከ12 እስከ 13 ኩንታል ማዳበሪያ (ዩሪያ እና ዳፕ) እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል። ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያው ጎን ለጎንም የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) በማዘጋጀት በማሳቸው ላይ በስፋት እንደሚጠቀሙ አክለዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ የዘር ምርጫ ወሳኝ መሆኑን የሚረዱት እኚሁ ሞዴል አርሶ አደር፤ ለበቆሎ እርሻቸው ‘ሊሙ’ እና ‘ቢኤች 661’ (BH 661) የተሰኙትን ምርጥ ዘሮች እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል። አሁን ላይም የ661 ዝርያን የገዙ ሲሆን የሊሙን ዝርያ ደግሞ በቀጣይ ሳምንታት ለመግዛት ዝግጅት እያደረጉ ነው። ለጤፍ ማሳቸው ደግሞ በምርታማነቱ የታወቀውን ‘ቁንጮ’ ጤፍ በስፋት እንደሚዘሩ ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል።
ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው የምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ቁጭ አካባቢ የሚኖሩት አርሶ አደር ጋሻየ ጌታሰው ለመጭው የመኸር የሰብል ልማት በዝግጅት ላይ ናቸው። ማሳቸውን ማፅዳት፣ ደጋግሞ ማረስ እንዲሁም ግብዓት በመግዛት እና በማጓጓዝ ሥራ ላይ ናቸው። አርሶ አደሩ በስፋት የሚያመርቱትን በቆሎ በአራት ሔክታር መሬት ለመዝራት ተዘጋጅተዋል። ለዚህም ፈጥነው ለሚዘሩ ሰብሎች ቀድሞ እየተሰራጫ ካለው የአፈር ማዳበሪያ ስድስት ኩንታል አውጥተዋል።
አርሶ አደሩ እንዳሉት በቀጣይም ለሌሎች ሰብሎች የሚያገለግል ግብዓት ለማውጣት ተዘጋጅተዋል። በቂ ምርጥ ዘርም አግኝተዋል። የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦቱ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ መምጣቱን የተናገሩት አርሶ አደር ጋሻየ የአፈር ማዳበሪያን እንደ በፊቱ አቅራቢያቸው ድረስ ስለማይገባ ለማድረስ ግን ረጅም ርቀት እንደሚጓዙ ነግረውናል። ይህም ላልተገባ ወጪ እና እንግልት ዳርጓቸዋል። በተጨማሪም የአፈር ማዳበሪያ ግዥው ከባንክ ጋር የተያያዘ በመሆኑ መጉላላት መኖሩን ነው ያስረዱት።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ ለበኵር እንደተናገሩት በ2018/2019 የምርት ዘመን 669 ሺህ 645 ሔክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ነው። እስካሁንም 350 ሺህ 123 ሔክታር መሬት በአንደኛ ዙር የእርሻ ሥራ መከናወን መቻሉን ነው ያብራሩት።
ምርታማነቱንም በሔክታር ከ38 ኩንታል ወደ 40 ኩንታል ለማሳደግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት እና አዳዲስ አሠራሮች እየተከናወኑ ናቸው። ለዚህም በምርት ዘመኑ አንድ ሚሊዮን 468 ሺህ 728 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ (ዩሪያ እና ዳፕ) ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 403 ሺህ 76 ኩንታል ወደ ወረዳዎች ደርሶ ለአርሶ አደሩ እየተሠራጨ ነው። በተመሳሳይ ምርታማነትን ለማሳደግ ሌላው ግብዓት ምርጥ ዘር ሲሆን 23 ሺህ 162 ኩንታል ለማቅረብ ታቅዶ 18 ሺህ 838 ኩንታል ምርጥ ዘር ወደ ዞኑ ገብቷል። 10 ሺህ 608 ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል።
ምርት እና ምርታማነትን የሚጨምሩ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም የታቀደውን ምርት ለማሳካት በትጋት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። “የዞኑን ምርታማነት ለማሳደግ የተሻሻሉ አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው” ያሉት አቶ ጥላሁን” በዚህም 78 ሺህ 250 ሔክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ታቅዶ ሁለት ሺህ 960 ሔክታር መሬት በትራክተር ታርሷል” ብለዋል። በዞኑ በ2018/2019 የመኸር ምርት ዘመን በዘር ከሚሸፈነው መሬት 26 ሚሊዮን 885 ሺህ 988 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ በ2018/19 የምርት ዘመን 332 ሺህ 32 ሔክታር መሬት በማልማት 17 ሚሊዮን 929 ሺህ 674 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። መምሪያው በተለይም ለውጭ ገበያ (ኤክስፖርት) እና ለአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓት በሚሆኑ ሰብሎች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጓል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ አለኸኝ ለበኵር ጋዜጣ እንደገለጹት ዘንድሮ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው አጠቃላይ ማሳ ውስጥ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ግንቦት 6/2018 ዓ.ም 314 ሺህ 887 ሔክታር መሬት ታርሷል። አያይዘውም በዘመናዊ እርሻ ዘርፍ ትልቅ መሻሻል መታየቱን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው በዞኑ 68 ሺህ 350 ሔክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ታቅዶ እስካሁን 28 ሺህ 487 ሔክታር መሬት በ19 ትራክተሮች መታረሱን አብራርተዋል። ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግም እርሻን ደጋግሞ ከማረስ ባሻገር የግብዓት አቅርቦት አንዱ ነው።
ስለሆነም ወሳኝ የሆነውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በተመለከተም አንድ ሚሊዮን 220 ሺህ ኩንታል (ዳፕ እና ዩሪያ) ለማቅረብ ታቅዷል። እስካሁንም 486 ሺህ 932 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ የገባ ሲሆን 65 ሺህ 495 ኩንታሉ በኩፖን ሥርዓት ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸዋል። የአፈር ማዳበሪያዉ ከማዕከል ወደ ወረዳዎች፣ ከወረዳዎች ደግሞ ቀጥታ ወደ አርሶ አደሩ በፍጥነት እንዲሰራጭ እየተደረገ ይገኛል።
በሌላ በኩል ከ50 ሺህ 700 ኩንታል በላይ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 31 ሺህ ኩንታል ወደ ዞኑ ገብቷል። ዘጠኝ ሺህ 566 ኩንታል ደግሞ ለአርሶ አደሩ መሠራጨቱን ነው የገለጹት። ይሁንና እንደ ሊሙ፣ (661 እና 546) ያሉ የበቆሎ ምርጥ ዘሮች ላይ እጥረት በመኖሩ ከወዲሁ የተለየ ትኩረት እንደሚሻ ተጠቁሟል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕገ-ወጥ እና ጥራታቸውን ያልጠበቁ ዘሮች ወደ አርሶ አደሩ እንዳይገቡ የኳራንታይን እና የጥራት ቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ኃላፊው አክለዋል።
በግብዓት አቅርቦት ሂደት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ አቶ መልካሙ ሲያብራሩ፤ ዋነኛው ችግር ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የተያያዘ መሆኑን አንስተዋል። አርሶ አደሩ ግብዓት ለመግዛት በንግድ ባንክ እና በፀዳይ ባንክ በኩል ክፍያ ሲፈጽም የገንዘብ ዝውውር ገደቦች እና የሲስተም መጨናነቆች መጉላላትን እየፈጠሩ ይገኛሉ። ይህንን ችግር ለመፍታትም በየደረጃው የግብዓት አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከባንክ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። “በዚህ ዓመት ለግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት በልዩ ትኩረት መሥራት አለብን” ነው ያሉት።
በግብዓት ስርጭት ዙሪያ አርሶ አደሩ እንደ ቀደሙ በአቅራቢያው አለማግኘቱ ለእንግልት እና ላላስፈላጊ ወጪ መዳረጉ ተነስቷል፡፡ ይሁን እንጅ የነዳጅ እጥረት ያስከተለው ችግር በመሆኑ ችግሩ እስኪፈታ አርሶ አደሩ የዘር ወቅት ሳያልፍ እየገዛ ጥቅም ላይ እንዲያዉል ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡
ባለፈው የ2017/18 የምርት ዘመን በዞኑ 321 ሺህ 531 ሔክታር መሬት ለምቶ 16 ሚሊዮን 571 ሺህ 108 ኩንታል ምርት መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን የዘንድሮው እቅድ መሬትን ከ10 ሺህ ሔክታር በላይ ምርትን ደግሞ ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማሳደግ ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል። ይህንን እቅድ ለማሳካትም የባንክ አገልግሎት እንግልትን በመፍታት አርሶ አደሩ ሙሉ ጊዜውን ወደ ማሳው እንዲያዞር በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
በአማራ ክልል በ2018/2019 የመኸር ምርት ዘመን አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። በዘንድሮው የመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው መሬት ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለበኩር ተናግረዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት 18 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። በሰብል ለመሸፈን ከታቀደው መሬት ውስጥ እስካሁን አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በአንደኛ ዙር እርሻ ታርሷል ብለዋል። ዳይሬክተሩ እንደገለጹት የግብርና ሥርዓቱን ማዘመን እና ከልማዳዊ አሠራር ማውጣት ይጠበቃል።
አርሶ አደሩን ከበሬ ጫንቃ ለማላቀቅ፣ ጊዜ እና ጉልበቱን ለመቆጠብ እና ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ሜካናይዜሽን አሠራር በትኩረት እየተተገበረ ነው። ለዚህም በክልሉ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል። በምርት ዘመኑ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የታለመውን ዕቅድ ለማሳካት የኩታ ገጠም እርሻ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት። ለአማራ ክልል በ2018/19 የምርት ዘመን ከስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ (ዳኘ እና ዩሪያ) እንደሚያስፈልገው ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ከ46 በመቶ በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እንደገባ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
መረጃ
የግብርና ግብዓቶች ዋና ዋና ጠቀሜታዎች፦
- ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ፡-
እንደ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያን በመጠቀም ከፍተኛ ምርት ማግኘት ይቻላል።
- የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፡-
የግብርና ግብዓቶችን መጠቀም በቂ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር እና የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
- የሰብል እና የእንስሳትን ደህንነት መጠበቅ፡-
የፀረ-ተባይ፣ የፀረ-አረም እና የፀረ-ፈንገስ ኬሚካሎች ሰብልን ከተለያዩ በሽታዎች እና አጥፊ ተባዮች ይታደጋል።
- ጊዜን እና ጉልበትን መቆጠብ፡-
እንደ ትራክተር፣ መዝሪያ እና መሰብሰቢያ ማሽኖች (ኮምባይነር) እንዲሁም የውኃ ሞተር ፓምፖች የአርሶ አደሩን ከፍተኛ የጉልበት እና ድካም ይቀንሳሉ።
- የምርት ጥራትን ማሻሻል፡-
ተገቢውን የግብርና ግብዓት መጠቀም የምርትን መጠን ብቻ ሳይሆን ጥራቱንም ይጨምራል።
- የአርሶ አደሩን ገቢ እና የሀገር ኢኮኖሚ ማሳደግ፡-
አርሶ አደሩ ግብዓቶችን ተጠቅሞ ብዙ እና ጥራት ያለው ምርት ሲያመርት ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚያቀርበው ምርት ይኖረዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የግንባት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


