ችግኝን መትከል የአየር ንብረት ለውጥን ከማሻሻል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው፡፡ በዘመናችን ዓለም እየተጋፈጠችው ካሉ ከፍተኛ ችግሮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። የምድር ሙቀት መጨመር፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የባሕር ውኃ በከፍተኛ መጠን መቀነስ፣ የደን ውድመት እና የአየር ብክለት በሰው ልጅ ሕይወት፣ በኢኮኖሚ እና በአካባቢ ላይ ከባድ ተፅዕኖ እያሳደሩ ናቸው። በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ችግሩን ለመቋቋም በተለያዩ መንገዶች እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ብቻ የሚፈጠር አይደለም፤ በተለይም የኢንዱስትሪ ዕድገት፣ የነዳጅ እና የከሰል አጠቃቀም፣ የደን ጭፍጨፋ እና የፋብሪካ ጭስ ልቀት ለችግሩ ዋና መንስኤዎች ሆነዋል።
በዚህ ምክንያት ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሀገራት በጋራ ለመሥራት ተገድደዋል። እ.አ.አ በ2015 የተፈረመው የፓሪሱ ስምምነት ለዚህ ትግል ታላቅ መሠረት ሆኗል። ስምምነቱ የዓለም ሙቀት ከአደገኛ ደረጃ በታች እንዲቆይ የሀገራትን የካርቦን ልቀት መቀነስን ያበረታታል። በዚህ ስምምነት ውስጥ በተለይም ታዳጊ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ድጋፍ እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቷል።
ኢትዮጵያም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ የድርሻዋን እየተወጣች ነው።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሸራ /Green Legacy Initiative/ መርሃ ግብር በ2011 ዓ.ም (2019 እ.ኤ.አ) በጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት ተጀመረ። ዋና ዓላማው የደን ጥፋትን መቀነስ፣ የአካባቢ መራቆትን መከላከል፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እና የደን ሽፋንን ማሳደግ ነው።
መርሃ ግብሩ በተጀመረበት ዓመት አራት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ከአራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን በላይ ተተክሏል። ከዚያ በኋላ በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ከኢትዮጵያ ግብርና ሚኒሥቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
በአማራ ክልልም መርሃ ግብሩ ከመጀመሪያው ዙር ጀምሮ በስፋት ሲከናወን ቆይቷል። በመርሃ ግብሩ በክልሉ ያሉ አርሶ አደሮች ንቁ ተሳታፊ ናቸው፡፡
ጉዳዩን በተመለከተም በኵር ጋዜጣ በመጭው ክረምት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅቱ እንዴት እንደሆነ አርሶ አደሮችን እና የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግራለች። በሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወረዳ የ016 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ተስፋ ምስጋኔ እንደሚሉት ችግኝ ማፍላት ለእርሳቸው ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ኑሮን የመቀየሪያ መንገድ ነው። አርሶ አደሩ ለበኵር በስልክ እንደተናገሩት በአካባቢያቸው ቀደም ሲል ተቋቁሞ በነበረ ሰፊ የችግኝ ማፍያ ተቀጥረው ሠርተዋል፡፡ በወቅቱም የችግኝ አፈላል ዘዴዎችን በተግባር መማራቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፣ ከዚያ በኋላ በጓሯቸው የተለያዩ ችግኞችን ማፍላት መጀመራቸውን ተናግረዋል። ያፈሏቸውን ችግኞችም ተስማሚ ቦታ በመምረጥ አስቀድመው ባዘጋጇቸው ጉድጓዶች እየተከሉና በእንክብካቤ እያሳደጉ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አርሶ አደር ተስፋ ገለጻ በተለይ ጌሾ፣ ባህር ዛፍ፣ ጽድ እና የመኖ ሳር በማልማት ለአካባቢው የደን ሽፋን መጨመር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። “ችግኝ ማፍላት ከጀመርኩ ረጅም ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ፤ በዚህም ኑሮዬን አሻሽያለሁ፣ ልጆቼን አስተምሬያለሁ፣ ራሳቸውንም እንዲችሉ አድርጌያለሁ” በማለትም ገልጸዋል። በተያዘው ዓመትም ከአንድ ሺህ በላይ የጌሾ ችግኝ በማፍላት ለመትከል ጉድጓድ አዘጋጅተው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ነው የጠቆሙ።
በተመሳሳይ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ማሞ ጸጋዬም ችግኝ ማፍላት በሕይወታቸው ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ለበኵር በስልክ እንደገለጹት ባሕር ዛፍ፣ ዘይቱኒ፣ ሳስፓኒያ፣ ፓፓያና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በማፍላትና በመትከል ከ10 ዓመታት በላይ ልምድ አካብተዋል። “ችግኝ መትከል ብቻ በቂ አይደለም” የሚሉት አርሶ አደር ማሞ፤ ሁሉም ሰው የተከለውን ችግኝ በቅርብ በመከታተልና በመንከባከብ እስከ ፍሬ ማድረስ እንዳለበት ያምናሉ።
እርሳቸው ይህን መንገድ በመከተላቸው በምግብ ራስን ከመቻል አልፈው ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ኑሯቸው መሻሻሉን አስረድተዋል። አርሶ አደሩ በተያዘው ዓመትም ከ400 በላይ የባሕር ዛፍ ችግኝ በማፍላት ለመትከል ቦታ በመለየት ጉድጓድ እያዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ አስፋው ታፈረ በበኩላቸው በ2018 ዓ.ም አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የደን፣ የፍራፍሬና የመኖ ችግኞች ለማፍላትና ለመትከል እቅድ መያዙን ገልጸዋል። እስካሁንም ከአራት ሚሊዮን በላይ ችግኝ ማፍላት መቻሉን እና ከ50 በላይ በሚሆኑ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ሥራው በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ አቶ አስፋው ገለጻ 895 ሺህ የሚጠጉ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ተዘጋጅተዋል፤ አራት ሺህ 124 የሚሆኑ የተከላ ቦታዎችም ተለይተዋል። ከእነዚህም ሁለት ሺህ 767 ሄክታር መሬት ለተከላ ተዘጋጅቷል፤ አንድ ሺህ 687 ያህሉ ካርታ የተሰራለት መሆኑን ተናግረዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የደን ባለሙያ አቶ ጋሻው ዓለሙ ለበኵር ክፍል በስልክ እንዳነጋገሩን ዞኑ ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለተከላ በመለየት የማጽዳት፣ ጉድጓድ የመቆፈርና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ ነጭ እና ቀይ ባሕር ዛፍ፣ ግራር፣ ግራቪሊያ፣ ጌሾ እና ሌሎች ከ130 በላይ የችግኝ ዓይነቶችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
ባለሙያው እንዳሉት 169 ሚሊዮን ችግኞች ለማፍላት ታቅዶ እስካሁን 167 ሚሊዮን ችግኞች መፈላቱን አረጋግጠዋል። ለዚህም 41 ሚሊዮን የመትከያ ጉድጓዶች ተዘጋጅተዋል፡፡ ቀሪዎቹን በቀጣይ ቀናት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ ለመጭው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ያለው የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ነው። የዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ጌታነህ ተክለማርያም እንደተናገሩት ዞኑ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ ነው። የተራቆተው መሬት እንዲያገግም በማድረግ፣ የደን ውጤቶችን ምርታማነት በማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠንካራ የአረንጓዴ ልማት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
የግብርናውን ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ብሎም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል የአረንጓዴ ሽፋንን ለማሳደግ በታቀደ እና በተቀናጀ መንገድ የልማት ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚተገበሩም አስረድተዋል፡፡ የዞኑ የደን ሽፋን አሁን ላይ 17 ነጥብ ሦስት የደረሰ ሲሆን በቀጣይ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 18 ነጥብ ሦስት ለማድረስ ታቅዷል። ዕቅዱን ለማሳካት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውንም ነው ያስታወቁት።
በዞኑ በ14 ሺህ 141 ችግኝ ጣቢያዎች 295 ሺህ ችግኝ ተዘጋጅተዋል። አሁን ላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ እየተዘጋጀ ሲሆን ከመተከሉ በፊት አንድ ወር ቀድመው መዘጋጀት እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል። ከ14 ሺህ 900 ሄክታር በላይ የካርታ ልየታም ተሠርቷል።
በዞኑ ከግንቦት 30/2018 ዓ.ም በፊት የችግኝ ጉድጓድ ተዘጋጅቶ እንዲጠናቀቅ የጋራ ስምምነትም ተደርጓል። ከመትከል ባለፈ ማህበረሰቡ “የኔ ነው!” ብሎ በባለቤትነት ተንከባክቦ የማሳደግ ልምዱ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም የፅድቀት መጠኑ እንዲጨምር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ቡድን መሪው አሳሰበዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በመጭው የክረምት ወራት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡ የሚተከሉ ችግኞችም ለጥምር ደን፣ ለደን ልማት፣ ለምግብነት የሚያገለግሉ ፍራፍሬዎች እና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ ናቸው።
ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ዝግባ፣ ዋንዛ፣ ፅድ፣ ግራር፣ ግራቪሊያ፣ ዲከረስ (ከሰል ለማምረት የሚጠቅም ዛፍ) እና መሰል ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉንም አስታውቋል። በተጨማሪም እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ እና ፓፓያን ጨምሮ የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ትኩረት ተሰጥቷል።
ባለፉት ዓመታት የደን ሽፋንን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱንም የክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምሕረት ለበኵር ጋዜጣ ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የችግኝ ተከላ ስኬት ከ79 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 82 በመቶ አድጓል። የክልሉ የደን ሽፋንም ከ13 ነጥብ 9 ወደ 18 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ከፍ ብሏል። የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት ምጣኔ በአንደኛው ዙር በተደረገው ጥናት 86 በመቶ ደርሷል። የፅድቀት መጠናቸውን ለመጨመርም ችግኞችን ዓመቱን ሙሉ በባለቤትነት የመንከባከብ እና የመጠበቅ ሥራ በዋናነት ተከናውኗል።
በቀጣይ የክረምት ወራት (ለ2018 ዓ.ም) የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለማከናወን በተለያዩ አካባቢዎች ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ ባለሙያዎች እና አመራሮች ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ ናቸው። ችግኝ ጣቢያ ማዘጋጀት፣ ችግኝ ማፍላት፣ የተከላ ቦታ እና ችግኙ የሚስማማውን የአፈር ፀባይ መለየት፣ ግብዓት በተለይም ኮምፖስት እና ደረጃውን የጠበቀ ጉድጓድ ማዘጋጀት፣ ከአየር ንብረቱ ጋር የሚስማማ ችግኝ መምረጥ እና መሰል ተግባራት በቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ናቸው።
የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ በማድረግ በተራቆቱ እና በደጋማ አካባቢዎች የአየር ንብረቱን ተቋቁመው ሊያድጉ የሚችሉ የዛፍ ዝርያዎች ተለይተው እየተዘጋጁ ነው።
አቶ እስመለዓለም እንደገለጹት በክልሉ ከ76 ሺህ በላይ የችግኝ ጣቢያዎች አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኝ ለማፍላት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፤ እስካሁንም አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኝ ተፈልቶ ዝግጁ ሆኗል። ከችግኝ ማፍላት ጎን ለጎን የመትከያ ቦታ የመለየት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት። በዚህም ከ261 ሺህ ሄክታር በላይ የመትከያ ቦታ ተለይቶ ዝግጁ መደረጉን አክለዋል። ከሁለት መቶ ሚሊዮን በላይ የመትከያ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩ፡፡ በቀሪዎቹ በቀጣይ ቀናቶች እንደሚዘጋጁም አክለዋል፡፡ የችግኝ ማፍላት ሥራው በግለሰቦች፣ በማሕበራት፣ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በተቋማት እየተከናወነ ነው።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የችግኞችን የፅድቀት ምጣኔ ለማሳደግ ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ ችግኞች በችግኝ ጣቢያ እንዳሉ ውኃ ማጠጣትን መቀነስ፣ ሥራቸውን መገረዝ፣ ዳሱን በማንሳት ፀሐይ እንዲያገኙ ማድረግ እና በአጠቃላይ ችግርን የማላመድ ሥራ ይከናወናል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ክልሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑ መነቃቃት ፈጥሯል ነው ያሉት። በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የተከናወኑት ተግባራት በአካባቢ ሥነ ምሕዳር ላይ አወንታዊ ለውጥ ማምጣት እንደቻሉም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት በሕዝብ ተሳትፎ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሸራ መርሃ ግብር ከተራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ በላይ ትልቅ ሀገራዊ ዓላማን የተሸከመ ፕሮግራም መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ መርሃ ግብሩ የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የአፈርና የውሃ ሀብትን ለመጠበቅ እንዲሁም ለዜጎች ዘላቂ የኑሮ መሠረት ለመፍጠር ያለመ ነው።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


