የ2018 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከተመሠረተ 15 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን የሊጉን ዋንጫ ለዘጠነኛ ጊዜ ማሳካት ችሏል። ክለቡ ለስድስተኛ ተከታታይ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ ክለቡ ካለው የፋይናንስ አቅም ባሻገር በውስጡ የገነባው የአሸናፊነት ስነ ልቦና ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን ለስፖርቱ ቤተሰብ አሳይቷል፡፡ በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ክለብ ዘንድሮ በ26 ጨዋታዎች 69 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነው ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው፡፡
ክለቡ ካደረጋቸው 26 መርሀግበሮች 22 ጨዋታዎችን አሸንፏል፡፡ በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል፡፡
በውድድር ዓመቱ አንድ ጨዋታ ብቻ መሸነፉ ተፎካካሪዎች ገና ብዙ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ማሳያ ሆኖ አልፏል፡፡ በሊጉ አስፈሪ የፊት መስመር የያዘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ በአጠቃላይ 73 ግቦችን ከተጋጣሚ ቡድኖች ላይ አስቆጥሯል፡፡
በቀላሉ የማይረበሸው የኋላ ክፍሉም ስምንት ግቦች ብቻ ነው የተቆጠሩበት፡፡ ይህም ክለቡ በማጥቃትም ሆነ በመከላከል በሊጉ ወደር እንደማይገኝለት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ የንግድ ባንክ የንግሥና ዘመን መቀጠል በሀገሪቱ የሴቶች እግር ኳስ ላይ አዲስ የጥራት ደረጃን ያስቀመጠ ታላቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ካለፉት ዓመታት አንጻር የዘንድሮውን የውድድር ዓመት ለየት የሚያደርገው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የሴቶች ክለብ ያሳየው እጅግ አስገራሚ መነቃቃት እና እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ለዋንጫው የነበረው ብርቱ ፉክክር ነው፡፡ ኤሌክትሪክ በ66 ነጥብ ከሻምፒዮናው ክለብ በሦስት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል፡፡ ሊጉ ከዚህ ቀደም ይታይ ከነበረው የአንድ ቡድን የበላይነት ወደ የሁለትዮሽ ፉክክር መሸጋገሩን ያበሰረ ክስተት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይህ መነቃቃት ደጋፊዎች በከፍተኛ ጉጉት ጨዋታዎችን እንዲከታተሉ በማድረግ ረገድ የራሱን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያሳየው ጥንካሬ ሌሎች ክለቦችም በስርዓት ከተገነቡ እና አስፈላጊውን ድጋፍ ከተደረገላቸው ሻምፒዮኑን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መፈታተን እንደሚችሉ ትልቅ ትምህርት የሰጠበት ዓመት ነው፡፡ ይህም ለሊጉ ዕድገት ተስፋ ሰጪ ምልክት ሆኗል፡፡
መቻልም በ56 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ተፎካካሪ ሆኖ የጨረሰ ሲሆን በሊጉ ያሳየው ወጥ አቋም ለብዙዎች አርአያ እንደሚሆን ብዙዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተውታል፡፡ ሀዋሳ ከተማ በ52 ነጥብ አራተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ሸገር ከተማ በ48 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን የ2018 የውድድር ዓመት ጉዞው በብዙ ውጣ ውረዶች የታጀበ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ዙር ሊጠናቀቅ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀሩት ክለቡን ላለፉት አምስት ዓመታት በዋና አሰልጣኝነት ስትመራ የነበረችውን አሰልጣኝ ሰርክአዲስ እውነቱን በማሰናበት እና ምክትል አሰልጣኙን ዘመኑ ታፈረን በመቅጠር ዓመቱን ጨርሷል፡፡
የግዮን ንግሥቶች በ38 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡ ይህ ውጤት ከደጋፊው ፍላጎት እና ከክለቡ ስም አንጻር ግን ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅበት ይገመታል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ትልቁ ጥንካሬ በሊጉ ውስጥ የነበረው ጽናት እና በተለይም በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ተሸንፎ ላለመውጣት ያሳየው ተጋድሎ ነበር፡፡ የቡድኑ ዋና ድክመት የሚታየው ግን በውጤት ወጥነት ሳይሆን ወሳኝ በሆኑ ጨዋታዎች ላይ ነጥቦችን በቀላሉ አሳልፎ መስጠቱ በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ ብሎ እንዳይታይ ችግር ሆኖበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የግዮን ንግሥቶች በማጥቃት ረገድ የነበራቸው ድክመት ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ በ26 ጨዋታዎች 17 ግቦችን ብቻ ነው ያስቆጠሩት፡፡ ቡድኑ በዘጠኝ ጨዋታዎች አንድም ግብ ሳያስቆጥር ከሜዳ ወጥቷል፡፡ የኋላ ክፍሉም ቢሆን በአማካኝ በየጨዋታው ከአንድ ግብ በላይ ተቆጥሮበታል፡፡ ክለቡ ከዚህ ዓመት ድክመቱ ተምሮ በቀጣይ በፋይናንስም ሆነ በተጫዋቾች ስብስብ ላይ ጠንካራ ዝግጅት ካላደረገ በቀጣይ ዓመትም ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል የዘንድሮው ዓመት አመላካች ሆኖ አልፏል፡፡
ዘንድሮ የሊጉ ፉክክር ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩ፣ አዳዲስ ኮከብ ተጫዋቾች ብቅ ማለታቸው እና የጨዋታ መርሃግብሮች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቃቸው ለሊጉ አስተዳደር ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሊጉ አሁንም ድረስ ሊላቀቃቸው ያልቻላቸው በርካታ ስር የሰደዱ ችግሮች እንዳሉበት የሚካድ አይደለም፡፡
በዚህ ዓመት ጎልቶ የታየው ችግር በሊጉ ክለቦች መካከል ያለው ሰፊ የገንዘብ አቅም ልዩነት ነው፡፡ በንግድ ድርጅቶች እና በከተማ አስተዳደሮች የሚደገፉ ክለቦች መካከል ያለው የኢኮኖሚ አቅም አለመመጣጠን ሜዳ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሲያሳድር ተስተውሏል፡፡ ይህም በሊጉ አናት እና ግርጌ ባሉ ቡድኖች መካከል ሰፊ የጥራት እና የብቃት ልዩነት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ የስታዲየም እና የሚዲያ ሽፋን እጥረት አሁንም ሊጉን ወደ ላቀ ደረጃ እንዳይሸጋገር አንቆ የያዘው ሌላኛው ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በዚህ ዓመት አዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን መውረዳቸው የዘንድሮው ሊግ አሳዛኝ ገጽታ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ አዳማ ከተማ እና ይርጋጨፌ ቡና ለጥቂት ከመውረድ ተርፈዋል፤ በቀጣይ ዓመት ራሳቸውን ካላደራጁ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ይጠብቃቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ በ26 ጨዋታዎች አራት ድሎችን ብቻ ማስመዝገቡን የአወዳዳሪው አካል መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህም የክለቡን አስተዳደራዊ እና ቴክኒካዊ ድክመት ያሳያል፡፡ አርባምንጭ ከተማ በዐስር ነጥብ ብቻ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ወርዷል፡፡ የእነዚህ ክለቦች ወደ ታችኛው የሊግ እርከን መውረድ ለሌሎች የከተማ አስተዳደር ክለቦች ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ በወረዱት ክለቦች ምትክም የጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ እና የሰበታ ከነማ ሴቶች ቡድን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አድገዋል፡፡
የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ወደ ሊጉ ማደግ በርካታ ወጣት እና ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ሊጉ ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡ ይህ ደግሞ የሊጉን የጥራት ደረጃ እና ፉክክር ይጨምረዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ሰበታ ከነማም ቢሆን በደጋፊው ታጅቦ ወደ ሊጉ መመለሱ ለሊጉ ድምቀት ይሆናል ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡
በዚህ የውድድር ዓመት ካየናቸው አስገራሚ ሁነቶች መካከል የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን ያስመዘገበችው ስኬት በቀዳሚነት ይነሳል፡፡ ዳግማዊት 24 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆና አጠናቃለች፡፡ ይህም ከንግድ ባንክ አጥቂዎች የበላይነት ወጥቶ አዲስ ኮከብ በሊጉ መፈጠሩን ያበሰረ ታላቅ ክስተት ነው፡፡ የዳግማዊት በተከታታይ ግብ የማስቆጠር ብቃት ለኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) የፊት መስመር ላይ ትልቅ አቅም እና የወደፊት ተስፋ የሚሰጥ ነው። የንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኝ በ21 ግቦች ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ ሌላኛዋ የንግድ ባንክ ተጫዋች እሙሽ ዳንኤል በ13 ግቦች ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡ እነዚህ የግል ብቃቶች እያደጉ መምጣታቸው የሊጉን ማራኪነት ከመጨመሩም በላይ ክለቦች በተጫዋቾች የግል ክህሎት ላይ እንዲሰሩ በር ከፋች ሆኖ አልፏል፡፡
የ2018 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ በክህሎት እያደገ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ዕድገቱ በፋይናንስ እና በመዋቅር ካልታገዘ አሁንም የጥቂት ክለቦች ብቻ የበላይነት እንዳይሆን ስጋትን ይፈጥራል፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ላቀ ከፍታ ለመሸጋገር መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልገዋል- የብዙዎች አስተያየት ነው፡፡
የንግድ ባንክ ሻምፒዮናነት መደበኛ ክስተት መሆኑ ቀርቶ ሌሎች ቢያንስ አምስት ክለቦች ለዋንጫ የሚፎካከሩበት ሊግ መፈጠር እንዳለበትም የእግር ኳስ ፍቃሪዎች ያምናሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ የሊጉን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ ከግል ኩባንያዎች ጋር ጠንካራ ስምምነት ማድረግ ይጠበቅበታል፤ አሰልጣኞች የሴቶች እግር ኳስን በማጥቃት ላይ ብቻ ሳይሆን በመከላከል ስልት (Tactical discipline) ላይ አተኩረው ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


