የአንጐልን እድገት የሚገታዉ

0
15

ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ “ክሎሪፒሪፎስ” በመባል ለሚታወቀው ፀረ ተባይ መድሃኒት መጋለጥ ከልጅነት እስከ ጉርምስና እድሜ ዘልቆ ከዓመታት በኋላም የአንጐል እድገት ውስንነት ወይም ደካማነትን ሊያስከትል እንደሚችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሜይልማን የህዝብ ጤና ትምህርት ቤት በመረጃ ምንጭነት እንዳስነበበው “ክሎሪፒሪፎስ”ለተሰኘው ፀረ ተባይ መድሃኒት መጋለጥ ከቅድመ ወሊድ ልጅነት እና እስከ ጉርምስና እድሜ ድረስ ዘልቆ ተፅእኖ እንደሚያደርስ ማስረጃዎች ተገኝተዋል፡፡

በምርምሩ የሜይልማን የህዝብ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ሦስት ተቋማት በትብብር መስራታቸውን ያስነበበው ድረ ገጹ 270 ልጆች እና ወጣቶችን በመከታተል ውጤቱን መቀመር መቻሉን ነው ያሰፈረው – ድረ ገጹ፡፡ ከስድስት እስከ 14 ባለው እድሜ ውስጥ በሚገኙት የናሙና ተሳታፊዎች የአንጎል ምርመራ እና የባህሪ ግምገማዎችም ተካሂደዋል፡፡

ከፍ ላለ ለፀረ ተባይ መድሃኒት መጠን የተጋለጡት በቀጥታ ከአንጐል መዋቅር ጋር የተያያዙ ጉልህ ለውጦችም ተስተውሎባቸዋል፡፡

የአንጐል የማሰብ፣ የማሰላሰል እና ምላሽ መስጠትን በሚለካ ሙከራ ደካማ አፈፃፀምም  ነው የተመዘገበባቸው፡፡

ለአብነት አሜሪካ ፀረ ተባይ መድሃኒቱን ከ2001 እ.አ.አ ጀምሮ አገልግሎት ላይ እንዳይውል ብታግድም ከከተማ ራቅ ባሉ አካባቢዎች በፍራፍሬ እና ጥራጥሬ አማራቾች ዘንድ ጥቅም ላይ እየዋል መሆኑ ነው የተጠቆመው፡፡

በፀረ ተባይ መድሃኒቱ መገኛ አካባቢ በነፋስ ተሰራጭቶ ወይም የሚመረቱ ጥራጥሬ እና ፍራፍሬዎችን በመመገብ የጤና እክል እንደሚያስከትል ነው የተሰመረበት በድረገጹ፡፡ በመጨረሻም ከመርዛማ ኬሚካሎች በእርግዝና፣ በጨቅላነት እና በልጅነት እድሜ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ በማሳሰብ ነው ጽሁፉ ያደማደመው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here