የግንቦት ወር በተማሪዎች

0
312

ግንቦት ወር በትምህርት ማህበረሰቡ ዘንድ ልዩ ትርጉም አለው። የትምህርት ዘመኑ ተገባዶ የዓመቱ የድካም ውጤት የሚታይበት የዓመቱ የመጨረሻ ፈተና የሚቃረብበት ወቅት ነው፡፡ በትምህርት ቤቶችም ሆነ በየቤቱ የፈተና ድባብ በጉልህ ይስተዋላል። ይህንን አስመልክቶም ተማሪዎችን፣ ወላጆችን እና መምህራንን አነጋግረናል።

ኤልሳቤት ሰለሞን የ7ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ “የክፍል ማጠቃለያ ፈተናዬ ስለደረሰ ማስታዎሻዎቼን ደጋግሜ እያነበብሁ ነው። ከጓደኞቸ ጋር በመሆንም የተማርነውን በመከለስ እና ጥያቄዎችን በመጠያየቅ ለፈተና ምን ያክል በብቃት እራሴን አዘጋጅቻለሁ? የሚለውን እየገመገምሁ ነው፡፡ የሚቀጥለው ዓመት የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ በመሆኔ የአሁኑ ጥንካሬየ ለሚቀጥለውም አጋዥ እንደሚሆነኝ ተስፋ አለኝ” በማለት ነው ቅድመ ዝግጅቷን የተናገረች፡፡

ኤልሳቤት እንደምትለው ለፈተና  በራሷ እና ከጓደኞቿ ጋር  ከምታደርገው ዝግጅት በተጨማሪ ታላላቅ እህትና ወንድሞቿ እገዛ እያደረጉላት እንደሆነ ተናግራለች፡፡

ሌላዋ ያነጋገርናት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ኤልዳና ብርሐኑ ናት፡፡  ወደ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ የተሸጋገረችበትን የመጀመሪያ ዓመት እያጠናቀቀች የምትገኘው ኤልዳና፣ “ዘንድሮ እየተከታተልናቸው ያሉ የትምህርት አይነቶች ሰፋ ያሉ በመሆናቸው የግንቦት ወርን ሙሉ በሙሉ ቡድን ፈጥረን ጥያቄዎችን በመሥራትና እርስ በርስ በመጠያየቅ እያሳለፍኩ ነው” በማለት ለፈተና ያላትን ዝግጅት አጋርታለች። ለዚህ ደግሞ የቤተሰቦቿ ድጋፍና እገዛ አቅም እንደ ፈጠራላት ተናግራለች፡፡

በተመሳሳይ ሰለሞን ወርቁ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና አንድ ዓመት ብቻ የቀረው ሰለሞን፣ አሁን ላይ እያደረገ ያለው ዝግጅት ከእለት እለት የክፍል ፈተና የዘለለ መሆኑን ገልጾልናል። “የግንቦት ወር ለእኔ የሞዴል ፈተናዎች እና የብሔራዊ ፈተና ጥያቄዎችን መለማመጃ ወቅት ነው። ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም የማጥኛ ጊዜዎችን ከፋፍዬ ነው የማጠናው” ሲልም የጥናት ስልቱን  አብራርቶልናል።

በጣና ኃይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ደረጀ ከፋለ በበኩላቸው ለበኵር  በስልክ እንደነገሩን፤ “በዚህ ወር ዋናው ሥራችን ማጠቃለያ ክለሳ ማድረግና ተማሪዎችን ከውጥረት ማውጣት ነው” ይላሉ፡፡ ምክታል ርዕሰ መምህሩ አክለውም በዚህ ወቅት ተማሪዎች ከመጠን በላይ እንዳይጨነቁ የሥነ-ልቦና ምክር መስጠት እንደሚገባና ፈተናን ተረጋግቶ የመሥራት ክህሎት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል፡፡

የፈተና ዝግጅት በትምህርት ቤት ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑን የጠቆሙት  ምክትል ርዕሰ መምህሩ፤ ወላጆች በቤት ውስጥ የሚያደርጉት ክትትል የጎላ ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የሁለት ተማሪዎች እናት  ወይዘሮ ዓለምፀሐይ መሸሻ በበኩላቸው፤ “በግንቦት ወር የልጆቻችንን የቤት ውስጥ ሥራዎች በመቀነስ የጥናት ጊዜ እንዲያገኙ እናመቻቻለን። ከምግብ አቅርቦት ጀምሮ አእምሯቸው ሳይወጠር በተረጋጋ ስሜት እንዲያጠኑ የቅርብ ክትትልና ማበረታቻ እያደረግንላቸው ነው” ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የሥነ ልቦና አሰልጣኝ አቶ እሱባለው ይርጋ በበኩላቸው ተማሪዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል በራስ አለመተማመን፣ ፈተናን አግዝፎ ማየት እና ራስን ዝቅ አድርጎ መገምገም ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።“ብዙ ተማሪዎች ጠንክረው ቢያነቡም ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት ከተበላሸ የሚፈልጉትን ውጤት ማምጣት አይችሉም” ያሉት ባለሙያው፤ የሥነ ልቦና ዝግጅት ለተማሪዎች ስኬት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል።

ባለሙያው አክለውም ጠንካራ ትውልድ ለመፍጠር በተማሪዎች ላይ መሥራት የሁሉም ማህበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው፣ ተማሪዎች ጠንክረው ከማንበብ ባለፈ በራስ መተማመናቸውን እንዲያጎለብቱ እና ውጤታማ እንዲሆኑ የሥነ ልቦና ሥልጠናዎች ከፈተና ጊዜ ቀደም ብሎ በስፋት መሰጠት ይኖርበታል፡፡ ይህም በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ  የፈተና ዝግጅት ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ተማሪዎች ከማንበብ ባለፈ ጊዜያቸውን በአግባቡ መቆጣጠር፣ በየቀኑ የጥናት መርሃ ግብር ማዘጋጀት፣ የቀድሞ ፈተናዎችን መለማመድ እና በራሳቸው መተማመንን ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል። ከጓደኞቻቸው ጋር በቡድን በማጥናት እርስ በርስ መደጋገፍና የማይገባቸውን  ርእሰ ጉዳዮች መጠያየቅም የፈተና ዝግጅታቸውን ይበልጥ ያጠናክራል። በተጨማሪም በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ ጤናማ ምግብ መመገብና ከከፍተኛ ጭንቀት ራሳቸውን መጠበቅ ለውጤታማነታቸው ወሳኝ መሆኑን አቶ እሱባለው አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል ወላጆች ለልጆቻቸው የተረጋጋ የጥናት አካባቢ በመፍጠር፣ ከመጠን በላይ ጫና ሳያሳድሩ ማበረታቻ በመስጠት እና የጥናት ጊዜያቸውን በቅርብ በመከታተል ትልቅ ድርሻ ሊኖራቸው እንደ ሚገባ አስገንዝበዋል። መምህራንም የተማሯቸውን መከለስ፣ የሞዴል ፈተናዎችን ማዘጋጀት እና ከፈተና ፍርሃት እንዲወጡ የሥነ-ልቦና ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። ስለሆነም የፈተና ውጤታማነት የአንድ አካል ጥረት ብቻ ሳይሆን የተማሪ፣ የወላጅ እና የመምህር የተቀናጀ ትብብር በመሆኑ  የግንቦት ወር የጭንቀት ጊዜ ሳይሆን የትጋትን ፍሬ በስኬት የሚያስጨብጥ ወቅት እንዲሆን ሁሉም አካላት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ግእዝ በአማርኛ

ከሠተ—- ገለጠ

ነበበ —- ተናገረ

ዘመረ — አመሰገነ

ኀሠሠ — ፈለገ

በርሀ —– በራ

እክል —– እህል

ሄላ  —–  የወይን ዘለላ

ከርካዕ —- ሎሚ

(ሰናይት በየነ)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here