ሄይቲ (አይቲ)

0
231

ሄይቲ በካሪቢያን ባሕር ውስጥ በሂስፓኒዮላ ደሴት ላይ ትገኛለች፡፡ ምንም እንኳ በተለያዩ ወቅቶች በተከሰቱ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ብትፈተንም እጅግ የበለጸገ የተፈጥሮ ሀብት ጸጋ እና ማራኪ የከተማ የታሪክና የባህል ውበት ያላት ልዩ የካሪቢያን ሀገር ናት።

የሀገሪቱ ስም “አይቲ” (Ayiti) ከጥንታውያኑ የታይኖ ተወላጆች ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም “የተራራዎች ምድር” ማለት ነው። ይህ ተራራማ መልክዓ-ምድር ለሀገሪቱ ልዩ የተፈጥሮ መዋቅር እና የማዕድን ሀብት ሰጥቷታል። በሄይቲ ምድር ውስጥ እንደ ቦክሳይት፣ መዳብ፣ ካልሲየም ካርቦኔት፣ እብነበረድ እና በሰሜናዊው ክፍል በስፋት የሚገኘው ያልተቆፈረ የወርቅ ክምችት ዋና ዋናዎቹ የተፈጥሮ ማዕድናት ናቸው። በግብርናው ዘርፍ የሄይቲ ምድር እጅግ ለም በመሆኑ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ልዩ ጣዕም ያለው ቡና፣ ታዋቂው የ”ፍራንሲክ” ማንጎ ዝርያ እና ከፍተኛ የአገዳ ምርት ይገኝበታል። በተለይም በዓለም የሽቶ ኢንዱስትሪ ውስጥ እጅግ ውድ እና ተፈላጊ የሆነው ለመሬት ጥበቃም ጭምር የሚያገለግለው የ”ቬቲቨር” (Vetiver) እፅዋት ዘይት ቀዳሚ አምራች ሄይቲ ናት።

የታይኖ ሕዝቦች አሳሹ ክርስቶፎር ኮሎምበስ ከመምጣቱ በፊት በካሪቢያን ደሴቶች በተለይም በሄይቲ ይኖሩ የነበሩ ጥንታውያን እና ሰላማዊ የሀገሬው ተወላጆች ናቸው። የታይኖ ማኅበረሰብ ካሲኬ በሚባሉ ነገሥታት የሚመራ ሲሆን የሥልጣን ሽግግሩ የሚከናወነው በሴት ወገን በእናት መስመር በኩል ነበር። በዚህ ሥርዓት ምክንያት እንደ ንግሥት አናካዎና ያሉ ሴቶች ትልቅ የፖለቲካ መሪ መሆን ይችሉ ነበር። የአኗኗር ዘይቤያቸው ሙሉ በሙሉ በግብርና ላይ የተመሠረተ ስለነበር ካሳቫ፣ ስኳር ድንች እና በቆሎ በስፋት ያመርቱ ነበር። ከካሳቫ እፅዋት የሚሠሩት እና ካሳቢ የሚባለው ጠፍጣፋ ዳቦ ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ስለሚቆይ የዘወትር ዋና ምግባቸው ነበር።

ታይኖዎች ባቴይ የተሰኘ በድንጋይ በተከበበ ሰፊ ሜዳ ላይ የሚጫወቱት ታዋቂ የኳስ ጨዋታ ነበራቸው። ይህ ጨዋታ ለሰላማዊ ውድድር ብቻ ሳይሆን በጎሳዎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት እንደ ፍርድ ቤትም ያገለግል ነበር። ምንም እንኳ የአውሮፓውያን ወረራ ሕዝቡን ቢያጠፋውም የታይኖ ባህል ግን በዓለም ቋንቋዎች ውስጥ ዛሬም ሕያው ነው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ የምንጠቀምባቸው እንደ ሃሞክ (የመረብ አልጋ)፣ ካኑ (ታንኳ)፣ ባርቤኪው (ጥብስ) እና ሀሪኬን (ማዕበል) ያሉ ቃላት በሙሉ ቀጥታ ከታይኖ ሕዝቦች ቋንቋ የተወሰዱ ናቸው።

ሀገሪቱን ከበው የሚገኙት የካሪቢያን ባሕር ወሽመጦች ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብቷ ናቸው። እንደ ላባዲ፣ ፖርት-ሳሉ እና ኢል-አ-ቫሽ (Île-à-Vache) ያሉ ደሴቶች እና ነጭ አሸዋማ የባሕር ዳርቻዎች በደማቅ ሰማያዊ ውኃቸው፣ በኮራል ሪፎቻቸው (“የባሕር ውስጥ ዓለቶቻቸው) እና በባሕር ውስጥ ሕይወት ብዝሃነት የታወቁ ናቸው። በየብስ ላይ ደግሞ እንደ ፒክ ማካያ እና ፎሬት ደ ፒን (Forêt des Pins) ያሉ ብሔራዊ ፓርኮች በደመና የተሸፈኑ ጥቅጥቅ ያሉ የተራራ ደኖችን የያዙ ሲሆን በዓለም ላይ በሌላ በማንኛውም ቦታ የማይገኙ ብርቅዬ የዕፅዋት፣ የነፍሳት፣ የዓሳ እና የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች መገኛ መጠለያዎች ናቸው።

የሄይቲ ከተሞች ከባሕር ዳርቻ ተነስተው ወደ ተራራማው ጫፍ የሚዘልቁ በመሆናቸው እጅግ አስደናቂ የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ውበት ጥምረት አላቸው። ዋና ከተማዋ ፖርት-ኦ-ፕሪንስ በተራራ ሰንሰለቶች እና በባሕር መካከል የተዘረጋች በመሆኗ ከኮረብታዎቿ ላይ ሆኖ ወደ ታች ሲመለከቱ ልዩ እይታን ትሰጣለች። በከተማዋ እምብርት የሚገኘው ታሪካዊው የብረት ገበያ (Marché de Fer) በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ከፓሪስ ተሠርቶ የመጣ ሲሆን እስላማዊ የስነ-ሕንጻ ጥበብ ቅርፅ ያላቸው አራት ታወሮች ያሉት ደማቅና ሕያው የንግድ ማዕከል ነው። ከተማዋ “የጅንጅብል ቤቶች” (Gingerbread houses) በሚባሉ በፈረንሳይ እና በአሜሪካ የሕንጻ ጥበብ ተፅዕኖ በተሠሩ ውስብስብ የእንጨት ቅርጻቅርጾች፣ ሰፊ በረንዳዎች እና ረዣዥም መስኮቶች ባሏቸው ውብ እና በቀለማት ያሸበረቁ መኖሪያ ቤቶቿ ትታወቃለች።

በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኘው የካፕ-ሄይቲየን ከተማ ደግሞ የሄይቲ የጥንት ስልጣኔ እና የሀብት ማሳያ ናት። ከተማዋ በፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ዘመን የተሠሩ የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች፣ ባለቀለም ግድግዳዎች እና የብረት በረንዳ ያላቸው ሕንፃዎች ያሉባት በመሆኗ ሙሉ ከተማዋ እንደ አንድ ክፍት ሙዚየም ትቆጠራለች። ከዚህች ከተማ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ ተራራ ላይ “ሲታዴል ላፌሪየር” የተሰኘው እና በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ግዙፍ ምሽግ እና የሳን-ሱሲ ቤተ-መንግሥት ፍርስራሽ ይገኛል። ይህ ምሽግ ጥቁር ሕዝቦች ነፃነታቸውን ካወጁ በኋላ ሀገራቸውን ለመከላከል የገነቡት ሲሆን የሄይቲን የምህንድስና ጥበብ እና ታላቅ ታሪክ የሚያሳይ ድንቅ የሕንጻ ጥበብ ነው። በደቡብ የምትገኘው የጃክሜል ከተማ ደግሞ የሄይቲ የጥበብ እና የባህል መናገሻ ስትሆን በየመንገዶቹ ላይ በሚታዩ የሞዛይክ ስዕሎች፣ በወረቀት በተሠሩ ጭምብሎች እና በደማቅ የቪክቶሪያን ዘመን ሕንጻዎቿ የጎብኚዎችን አይን ትማርካለች።

የሄይቲ የቱሪዝም ዘርፍ እጅግ ግዙፍ የሆነ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ እምቅ አቅም ያለው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በጸጥታ እና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት ከፍተኛ ፈተና ውስጥ የሚገኝ እና የተደናቀፈ ኢንዱስትሪ ነው። ሀገሪቱ በካሪቢያን ምድር ሁለተኛውን ረዥም የባሕር ዳርቻ የያዘች በመሆኗ ለባሕር ዳርቻ እና ለሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ በርካታ መዳረሻዎች አሏት። በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው እና በነጭ አሸዋማ የባሕር ዳርቻው የሚታወቀው ላባዲ እና በደቡብ የምትገኘው ንፁህ ደሴት ኢል-አ-ቫሽ ዋነኞቹ የባሕር ዳርቻ ቱሪዝም መዳረሻዎች ናቸው። በጃክሜል ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው እና በደማቅ ሰማያዊ ውኃው የሚታወቀው ባሲን ብሉ የተፈጥሮ መዋኛ ስፍራ እና ሳውት ማቱሪን የተባለው ግዙፍ ፏፏቴ የሀገሪቱ የተፈጥሮ ጌጦች ናቸው። ምንም እንኳ እነዚህ ሁሉ መስህቦች ቢኖሩም የሀገሪቱ የውስጥ ደኅንነት ሁኔታ በቱሪዝሙ ላይ ከባድ ተፅዕኖ አሳድሯል። በሀገሪቱ ባለው የቡድን ግጭት እና የጸጥታ አለመረጋጋት ምክንያት እንደ ሮያል ካሪቢያን ያሉ ታላላቅ የዓለም አቀፍ የቱሪስት መርከብ ኩባንያዎች ወደ ላባዲ የባሕር ዳርቻ የሚያደርጉትን ጉዞ እስከ 2026 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ሙሉ በሙሉ አቁመዋል። እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራትም ዜጎቻቸው በእገታ እና በወንጀል ስጋቶች ምክንያት ወደ ሄይቲ እንዳይጓዙ የ”ደረጃ 4 – አትጓዙ” የደኅንነት ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።

በቅርቡ የጸጥታ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ከሚደረጉ ጥረቶች ጎን ለጎን የቱሪዝም እና የትራንስፖርት ዘርፉን ለማነቃቃት አዳዲስ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። ሄይቲ እና ጎረቤቷ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ ላለፉት ሁለት ዓመታት ዘግተውት የነበረውን የጋራ የአየር ክልላቸውን በ2018 ዓ.ም መልሰው ለመክፈት ተስማምተዋል። ይህ ስምምነት በተለይ ሰላማዊ በሆነው በሰሜናዊው የሄይቲ ክፍል በኩል የንግድ እና የቱሪስት በረራዎች እንዲጀመሩ በር ከፋች ሆኗል። የፖርት-ኦ-ፕሪንስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የጸጥታ መሻሻሎችን ተከትሎ የሀገር ውስጥ እና የክልላዊ አየር መንገዶች (እንደ ሳንራይዝ ኤርዌይስ ያሉ) በረራዎችን በጥንቃቄ መጀመራቸውን አሳውቀዋል።

ሄይቲ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ውስጥ ብትገኝም ያሏት የተፈጥሮ ስጦታዎች፣ ብርቅዬ ብዝሃ-ሕይወት እና የሕዝቦቿ የጥበብ፣ የታሪክ እና የሕንጻ ውበት ሀገሪቱን በካሪቢያን ምድር እጅግ ማራኪና ድንቅ ያደርጋታል።

ምንጭ፡- የዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች ማዕከል፣ የሄይቲ ኤምባሲ እና የሮያል ካሪቢያን ኩባንያ

 

አጫጭር እውነታዎች

ሄይቲ

  • ሄይቲ በካሪቢያን ባሕር ውስጥ በሂስፓኒዮላ ደሴት ላይ ትገኛለች፡፡
  • የሀገሪቱ ስም “አይቲ” (Ayiti) ከጥንታውያኑ የታይኖ ተወላጆች ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም “የተራራዎች ምድር” ማለት ነው።
  • በሄይቲ ምድር ውስጥ እንደ ቦክሳይት፣ መዳብ፣ ካልሲየም ካርቦኔት፣ እብነበረድ እና በሰሜናዊው ክፍል በስፋት የሚገኘው ያልተቆፈረ የወርቅ ክምችት ዋና ዋናዎቹ የተፈጥሮ ማዕድናት ናቸው።
  • የታይኖ ሕዝቦች አሳሹ ክርስቶፎር ኮሎምበስ ከመምጣቱ በፊት በካሪቢያን ደሴቶች በተለይም በሄይቲ ይኖሩ የነበሩ ጥንታውያን እና ሰላማዊ የሀገሬው ተወላጆች ናቸው።
  • በዓለም ዙሪያ የምንጠቀምባቸው እንደ ሃሞክ (የመረብ አልጋ)፣ ካኑ (ታንኳ)፣ ባርቤኪው (ጥብስ) እና ሀሪኬን (ማዕበል) ያሉ ቃላት በሙሉ ቀጥታ ከታይኖ ሕዝቦች ቋንቋ የተወሰዱ ናቸው።
  • ሀገሪቱን ከበው የሚገኙት የካሪቢያን ባሕር ወሽመጦች ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብቷ ናቸው።
  • የሄይቲ ከተሞች ከባሕር ዳርቻ ተነስተው ወደ ተራራማው ጫፍ የሚዘልቁ በመሆናቸው እጅግ አስደናቂ የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ውበት ጥምረት አላቸው።
  • በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኘው የካፕ-ሄይቲየን ከተማ የሄይቲ የጥንት ስልጣኔ እና የሀብት ማሳያ ናት።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here