̋በሀገራችን ያለው የሥነ አዕምሮ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፤ ̋ይህን ያሉት በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ አዕምሮ ትምሕርት ክፍል መምሕር እና የተሀድሶ ክፍል ኃላፊ አቶ ጌታሰው ለጋስ ናቸው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉም ሀገራት ወጥ በሆነ መንገድ ባያከበሩትም ግንቦት ወር በስፋት የሥነ አዕምሮ ጤና ግንዛቤ መፍጠሪያ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በኵርም በሥነ አዕምሮ ጤና አጠባበቅ፣ እክል እና ሕክምናዎቹ ላይ አተኩራለች፡፡
መምህሩ እንደገለጹት አንድ ሰው ጤናማ አዕምሮ አለው የሚባለው ሰውየው የተሟላ ደኅንነት ሲኖረው እና በውስጡ ያለውን አቅም እና እውቀት አውጥቶ መጠቀም ሲችል፣ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከጎረቤት እና በአካባቢው ካሉ ሰዎች ጋር መስተጋብሩ አዎንታዊ ሲሆን፣ በሥራው፣ በኑሮው እና በትምህርቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጭንቀት መንስኤዎችን መቋቋም ሲችል፣ በሥራው ውጤታማ እና ፍሬያማ ሲሆን እንዲሁም ለቤተሰቡ እና ለማሕበረሰቡ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ከሆነ ነው፡፡ ይሁንና አንድ ሰው የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ማሟላት የማይችል ከሆነ የሥነ አዕምሮ ጤና እክል አጋጥሞታል ይባላል፡፡
የሥነ አዕምሮ ጤና እክል አጋላጭ ምክንያቶች?
“የሥነ አዕምሮ ጤና ሊጓደል የሚችልበት ዋነኛ ምክንያት አይታወቅም“ ያሉት ባለሙያው፤ ለችግሩ አጋላጭ ተብለው የተለዩት ግን ሥነ ሕይወታዊ (biological Factors)፣ ሥነ ልቦናዊ (PsychologicalFactors) እንዲሁም ማሕበራዊ (Social and Environmental Factors) ምክንያቶች ናቸው፡፡
ሥነ-ሕይወታዊ ወይም ባዮሎጅካላዊ ምክንያቶች የሚባሉት በተፈጥሮ ወይም በዘር ሊወረሱ እንደሚችሉ ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡ ይህም የሥነ አዕምሮ ችግር ካለበት ቤተሰብ የተገኙ ሰዎች ማለትም (እናት፣ አባት፣ እህት ወይም ወንድ ወንድም ) እክል አጋጥሟቸው ከነበረ እንደዚህ አይነት ታሪክ ከሌላቸው ሰዎች አንጻር ለአዕምሮ ጤና እክል የመጋለጥ አዝማሚያቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በአዕምሮ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች መዛባትም የአዕምሮ ጤናን ሊያውኩ እንደሚችሉ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በልጅነት ወይም በአዋቂነት ዕድሜ ጭንቅላት ላይ የደረሰ አደጋ፣ አደንዛዥ ዕጾችን፣ አልኮል፣ ጫት፣ ሲጋራ መጠቀም እና የምግብ እጥረት ሥነ ሕይወታዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ሥነ ልቦናዊ ምክንያቶች የሚባሉት ደግሞ በልጅነት ጊዜ ፍቅር አለማግኘት፣ ቤተሰብን በሞት ማጣት፣ ሥራ አጥ መሆን፣ በልጅነት ጊዜ ለአካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ አደጋዎች የመጋለጥ አጋጣሚዎች መኖር እንዲሁም በወሲባዊ ጥቃት የሚፈጠር የአዕምሮ እክል ነው፡፡
ሌላው ማሕበራዊ እና የአካባቢያዊ ምክንያቶች ሲሆኑ ድህነት ደግሞ ቀዳሚው ነው፡፡ ሰዎች ችግራቸውን ለኔ ለሚሉት ሰው ማካፈል ሳይችሉ ሲቀሩ፣ ችግራቸውን የሚረዳላቸው እና ሚያግዛቸው ሰው ሲያጡ፣ ራሳቸውን ከሰዎች የሚያርቁ ወይም ብቸኝነትን የሚያበዙ ከሆነ፣ ሰው ሠራሽ እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ማለትም በጦርነቶች፣ ግጭቶች፣ ድርቅ እና የጎርፍ አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ለአዕምሮ ጤና እክል የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው፡፡
የአዕምሮ ጤና እክል ምልክቶች ምንድን ናቸው?
መምሕር ጌታሰው ለጋስ እንዳስረዱት ዋና ዋና የሚባሉት የአዕምሮ ጤና ሲታወክ የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡ እነዚህም ከዚህ በፊት ያልተለመደ ባሕሪ ማሳየት፣ የስሜት መለዋወጥ ለአብነትም ከመጠን ያለፈ ደስታ ወይም ደግሞ ጥልቅ የሆነ ሀዘን ውስጥ መግባት፣ የስሜት መቀዝቀዝ፣ የእንቅልፍ መዛባት (በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ወይም ከሚገባው በላይ እንቅልፋም መሆን)፣የአመጋገብ መዛባት ይህም ማለት ከተለመደው በላይ መመገብ ወይም አለመመገብ ሲኖር፣ ከመጠን ያለፈ ፍርሐት ወይም ጭንቀት፣ የዕለት ተዕለት ተግባርን ማከናወን አለመቻል፣ በሥራ ውጤታማ አለመሆን፣ ብቸኝነትን መምረጥ፣ ሰዎችን መጠራጠር፣ ጠብ አጫሪነት፣ ራስን ወይም ሰዎችን ለመጉዳት ማሰብ እና መሞከር አዘውትረው ከሚታዩ የስነ አዕምሮ በሽታዎች መካከል የሚታዩ ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው፡፡
ሰዎች የሥነ አዕምሮ ጤናቸውን እንዴት ይጠብቁ?
መምሕር ጌታሰው እንዳስረዱት አደንዛዥ ዕጾችን አለመጠቀም፤ ሲጋራ አለማጨስ፣ ጫት አለመቃም እንዲሁም አልኮል አለመጠጣት የአዕምሮ ጤናን ይጠብቃል፡፡ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ማለትም ከሰባት እስከ ስምንት ሰዓት የሚደርስ በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፣ አመጋገብን ማስተካከልም ተገቢ ነው፡፡
ውጥረትን እና ጭንቀትን መቆጣጠር ሌላው የአዕምሮ ጤናን መጠበቂያ መንገድ ሲሆን ጭንቀት እና ውጥረት ሲያጋጥም በቂ ረፍት መውሰድ፣ የሰዎችን እገዛ መጠየቅ፣ ለሚቀርቡት ሰው ችግርን ማካፈል እና መፍትሔ ማምጣት፣ ማሕበራዊ ግንኙነትን ማጠናከር፣ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት እና ከማሕበረሰቡ ጋር አዎንታዊ ግንኙነት መፈጠር መቻል የሚያጋጥምን የሥነ አዕምሮ ችግር ለመከላከል እና የአዕምሮ ጤናን ለመጠበቅ ቁልፍ መንገዶች ናቸው፡፡
ሕክምናዎቹ ምንድን ናቸው?
እንደሌላው የጤና እክሎች ሁሉ የሥነ አዕምሮ ሕመም የራሱ ሕክምናዎች እንዳሉት የገለጹት መምህር ጌታሰው፤ የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎትም ሕመሙ ያለበት ደረጃ እንደሚወስነው አስረድተዋል፡፡ ብዙ ጊዜም የሥነ ልቦና ሕክምና እና በመድኃኒት የታገዘ ሕክምና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ በጤና ተቋማት ተኝቶ በመታከም እና በተመላላሽ ሕክምና ሊሰጥ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
የሥነ አዕምሮ ጤና እክል በማንኛውም የዕድሜ ደረጃ እንደሚከሰት የጠቆሙት መምህሩ ይሁንና ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የሥነ አዕምሮ ጤና ሕመሞች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ እድሜ ሲጨምርም እየቀነሱ የሚመጡ የሥነ አዕምሮ ችግሮች መኖራቸውን አስገንዝበዋል፡፡
በተያያዘም በሀገራችን ያለው የሥነ አዕምሮ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ የተናገሩት ባለሙያው፤ አሁን ያለው የኑሮ ውድነት፣ ግጭት፣ ሥራ ማጣት እና ለፍቺ መጋለጥ ሁኔታውን እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡ የአዕምሮ ጤና መታወክ የታመሙ ሰዎች ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሁሉም ሰው የዕለት ተዕለት ሕይወት፣ ደስታ፣ ምርታማነት እና ግንኙነት መሠረት መሆኑንም በመጠቆም አዕምሮን መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
ጤና አዳም
* በዓለም ላይ ከሰባት ሰዎች መካከል አንዱ የአዕምሮ ጤና መታወክ ያጋጥመዋል፡፡
* አብዛኛዎቹ የሥነ አዕምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ውጤታማ እንክብካቤ አያገኙም፡፡ ብዙ ሰዎች መገለል፣ አድልዎ እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ይደርስባቸዋል፡፡
* እ.አ.አ በ2021 72 ሚሊዮን ሕፃናትንና ጎረምሶችን ጨምሮ 359 ሚሊዮን ሰዎች በጭንቀት አዕምሯቸው ታውኮ ነበር፡፡
ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


