የወንጪ ሐይቅ በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ በስተምእራብ 155 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በቅርብ ከሚገኙት ከወሊሶ ከተማ 38፤ ከአምቦ ደግሞ 28 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡
የሐይቁ መገኛ ከባህር ወለል በላይ 3380 ሜትር ከፍታ ባለው የጠፋ እሳተ ገሞራ በፈጠረው ጐድጓዳ ቀጣና ነው፡፡ ጠቅላላ ስፋቱ አራት በአራት ነጠብ ስምንት ወይም 19 ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡ በሐይቁ መሀልም የቂርቆስ ገዳም የተገደመባት አነስተኛ ደሴት ትገኛለች፡፡
በቀጣናው 66 የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎች ይገኛሉ፤ ከነዚህም መካከል የደጋ አጥቢ እንስሳት እና አእዋፍትን ይዟል፡፡ከአጥቢ እንስሳት ዝንጀሮ እንዲሁም በየቁጥቋጦዎች የተለያዩ የዓይጥ ዝርያዎች መኖሪያ ሆኖም ያገለግላል፡፡ የሀይቁ ዙሪያ ቀጣና ከዓዕዋፍት ጥቁር ዝይ፣ ባለ ሰማያዊ ክንፍ ዝይ የአፍሪካ ዳክዬ እንዲሁም በአካል ግዝፈት የሌላቸው ዓዕዋፍ መገኛ ነው፡፡
በኃይቁ ዳር አራት ሺህ ኗሪዎችን የያዘው የወንጪ መንደር ይገኛል፡፡ ኗሪዎቹ የኦሮሞ፣ የአማራ እና የጉራጌ ብሄር ሲሆኑ 99 በመቶ የሚሆኑት የክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች ናቸው፡፡ መተዳደሪያቸውም ከጐብኚዎች የሚያገኙት ገቢ፣ እርሻ፣ የከብት እርባታ፣ ንብ ማናባት ዋነኞቹ መሆናቸውን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡
በሐይቁ ዙሪያ በሚገኙ ኗሪዎች እንሰት፣ ገብስ፣ ስንዴ እና ድንችን በብዛት ያመርታሉ፡፡
ለጐብኚዎች ማረፊያም የተለያዩ ሎጂዎች ለመስተንግዶ ተዘጋጅተዋል፡፡ ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ማይ ኢትዮጵያ ቱር፣ ቪዚት ኢትዮጵያን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


