የድል ቁልፎች

0
67

ሰኔ ወር የዓመቱ ትምህርት የሚጠናቀቅበት፣ ተማሪዎች ደግሞ ዓመቱን ሙሉ የለፉበትን ውጤት ለማግኘት ለማጠቃለያ ፈተና የሚቀመጡበት ነው፤ ከዚህ በተጨማሪም ብሔራዊ ፈተናዎችም የሚሰጡበት ወሆኑ ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ ሰኔ ለተማሪዎች የጥረት፣ የትዕግሥት እና የተስፋ ወቅት ነው። በዚህ ወር ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ ያካበቱትን ዕውቀት በፈተና ውጤት ያሳያሉ።

በኵር በግንቦት ወር ከፈተና በፊት መከናወን ስለሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶች በተከታታይ ለንባብ አብቅታለች፤ በእነዚህ ዕትሞች ከተማሪዎች፣ ከመምህራን፣ ከወላጆች እና ከሌሎች ባድርሾች ምን እንደሚጠበቅ የዘርፉን ባሙያ ሐሳብ በማካተት ነበር ያስነበበችው፡፡ በዚህ መጣጥፍ ደግሞ በፈተና ወቅት ሊኖር ስለሚገባ የሥ ልቦና ዝግጅት እናስነብባችኋለን፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ውጤት የቀለም ትምህርት (ዕውቀት) በጠንካራ ስነ ልቦናዊ ዝግጅት ሲታጀብ ነው፤ ፈተና ሲባል በባሕርይው ለፍርሃት አጋላጭ መሆኑን የሚያነሱት ባሙያዎቹ ትልቁ ውድቀት ግን ከፈተናው ይልቅ የሚፈጠረው ፍርሃት ራሱ ስለመሆኑ ነው የሚያስገነዝቡት፡፡

ታዋቂው የትምህርት ባለሙያ ዊሊያም በትለር እንደሚሉት ፈተና የፍርሃት ምንጭ ሳይሆን የዝግጅት ውጤትን የምናሳይበት ዕድል ነው፤ በመሆኑም ተማሪዎች በፈተና ወቅት ዓመቱን ሙሉ የለፉበትን እና የተዘጋጁበትን እንዲሁም ያገኙትን ዕውቀት በነጻነት መሥራት እንደሚገባ ነው ባለሙያው የሚመክሩት፡፡

ምሁሩ እንደሚሉት የፈተና ስኬት በዕውቀት ብቻ የሚወሰን አይደለም። በተለይም የፈተና ጭንቀትን መቆጣጠር፣ በራስ መተማመንን ማጎልበት እና አዎንታዊ አስተሳሰብን ማዳበር ከትምህርታዊ ዝግጅት እኩል የሚጠቀሱ የስነ ልቦና ዝግጅቶች ናቸው።

የሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የትምህርት ሥርዓቶች ውጤታማ የሚሆኑት ደረጃውን እና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በብቁ ባለሙያዎች ከመስጠት በተጨማሪ ለስነ ልቦና ዝግጅት ልዩ ትኩረት በመስጠታቸው ነው፡፡

የስነ ልቦና ዝግጁነት ተማሪዎች የፈተና ጭንቀትን እንዲቆጣጠሩ፣ በራሳቸው እንዲተማመኑ እና ያላቸውን ዕውቀት በተሻለ ሁኔታ በተግባር እንዲያሳዩ፣ በውጤትም እንዲለካ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው የጥናት ውጤቶች ያመላክታሉ።

በተለይም በፈተናዎች ወቅት የሚታየው ውጥረት እና ጫና በተማሪዎች ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል ስነ ልቦናዊ ዝግጅት የፈተና ስኬት ዋና አካል ተደርጎ ይታያል።

በዚህ ላይ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሃገራት መካከል ፊንላንድ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ  እና ደቡብ ኮሪያ ተጠቃሽ መሆናቸውን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ድርጅት መረጃ ያመላክታል፤ ተማሪዎች ለፈተና ከመቅረባቸው በፊት የጭንቀት መቆጣጠሪያ ስልጠናዎችን፣ የጊዜ አጠቃቀም ክህሎትን እና ራስን የማበረታታት ዘዴዎችን እንዲማሩ ይደረጋል።

በእነዚህ ሀገራት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የስነ ልቦና አማካሪዎች ተማሪዎችን በግልም ሆነ በቡድን በማማከር የፈተና ፍርሃትን እንዲቀንሱ ያግዛሉ። በጃፓን ለምሳሌ ተማሪዎች የፈተና ውጤትን ከሕይወታቸው አጠቃላይ ስኬት ጋር እንዳያያይዙ እና ውጤት ብቻ የሰውን ዋጋ እንደማይወስን የሚገልጹ ስነ ልቦናዊ መርሃ ግብሮች ይተገበራሉ።

በአሜሪካ እና በእንግሊዝ ያሉ ትምህርት ቤቶችም የአዕምሮ መረጋጋት (Mindfulness) ልምምዶችን ለተማሪዎች ያስተምራሉ፤ ተሞክሮዎችንም ያስፋፋሉ።

እነዚህ ልምምዶች ተማሪዎች ትኩረታቸውን እንዲያጠናክሩ፣ ከስጋት እና ከፍርሃት እንዲርቁ እንዲሁም በፈተና ወቅት የሚያጋጥማቸውን ጫና በተሻለ ሁኔታ እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል።

ባለሙያዎች እንደሚገልጹት አዎንታዊ አስተሳሰብ እና በራስ መተማመን በፈተና ውጤት ላይ እጅግ ከፍተኛ ሚና አላቸው። በኢትዮጵያም በፈተናዎች ወቅት ተማሪዎች ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደሚገቡ ይታወቃል።

ተማሪዎች በቂ ዕውቀት ቢኖራቸውም በፍርሃት እና በጭንቀት ምክንያት ያላቸውን አቅም ማሳየት አይችሉም። በመሆኑም ከትምህርት ዝግጅት ጎን ለጎን የስነ ልቦና ድጋፍ ለተማሪዎች መሰጠት እንዳለበት የትምህርት ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ተማሪዎች በፈተና ወቅት ሊኖራቸው የሚገቡ የስነ ልቦና ዝግቶች በራስ መተማመንን፣ አዎንታዊ አስተሳሰብን፣ የጊዜ አጠቃቀም ችሎታን እና የጭንቀት መቆጣጠር ክህሎትን ያካትታል። ተማሪዎች “አልችልም” ከሚል አስተሳሰብ ይልቅ “የተማርኩትን እችላለሁ” የሚል አዎንታዊ እምነት ሊያዳብሩ እንደሚገባም ይመክራሉ።

በተመሳሳይ ወላጆች እና መምህራን የሚያበረክቱት ድጋፍ በተማሪዎች ስነ ልቦና ዝግጁነት ላይ ወሳኝ ነው። ወላጆች ከመጠን ያለፈ ጫና ከማሳደር ይልቅ ልጆቻቸውን በማበረታታት እና በመደገፍ ለስኬታቸው የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል። መምህራንም ተማሪዎችን በተስፋ የሚሞሉ ምክሮችን በመስጠት የፈተና ወቅት ፍርሃትን እንዲቀንሱ ሚናቸው ከፍተኛ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ እና መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ የአዕምሮ ጤናን ለማጠናከር አስፈላጊ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት የአዕምሮ ጤና፣ ጭንቀት አያያዝ እና የወጣቶች ስነ ልቦና ጤና መረጃ ያስገነዝባል። ይህ ሲሆን ታዲያ ተማሪዎች በነጻነት ፈተናቸውን እንዲፈተኑ ያስችላል፤ ውጤታማም ያደርጋቸዋል፡፡

በአጠቃላይ የፈተና ስኬት የሚወሰነው ዕውቀት በጠንካራ የስነ ልቦና ዝግጁነት ሲታጀብ መሆኑን ነው የስኬታማ ተማሪዎች ተሞክሮ የሚያሳየው።

ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥም በትምህርት ቤቶች የስነ ልቦና ድጋፍ ፕሮግራሞችን ማጠናከር፣ ተማሪዎችን በጭንቀት አያያዝ ማሰልጠን እና ወላጆችን በጉዳዩ ላይ ማስተዋወቅ የፈተና ውጤትን ከማሻሻል ባለፈ ጤናማ እና በራሳቸው የሚተማመኑ ተማሪዎችን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ ፈተና የፍርሃት ሳይሆን የዕድል በር መሆኑን በመረዳት ፈተናን መፈተን ተረጋግቶ ይገባል።

ይህ ሲሆን ደግሞ የትምህርት ጥራትን ከፍ በማድረግ ለሀገር ልማት የሚያስፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ያስችላል።

 

መረጃ

ስለ ፈተና ስኬት የሚያበረታቱ አባባሎች፦

 

“ስኬትበአጋጣሚ አይመጣም፤ በዝግጅት፣ በጥረት እና በጽናት ይገኛል።” – ኮሊን ፓውል

“ትልቅ ስኬት የሚጀምረው ከትናንሽ ጥረቶች ድምር ነው።” – ሮበርት ኮሊየር

“ስኬት ወደ አንተ አይመጣም፤ አንተ ወደ እሱ ትሄዳለህ።” – ማርቫ ኮሊንስ

“ፈተና የዕውቀት መለኪያ እንጂ የሕልም መጨረሻ አይደለም። ራስን ማመን ደግሞ የስኬት ጉዞ ግማሽ መንገድ ነው።” – ቲዮዶር ሩዝቬልት

“ትምህርት ዓለምን ለመቀየር ልትጠቀምበት የምትችለው እጅግ ኃይለኛ መሣሪያ ነው።” – ኔልሰን ማንዴላ

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሰኔ 8  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here