የእዕምሮ ስፖርት

0
114

አንድን ማኀበረሰብ ወደ አስተሳሰብ ልዕልና ለማምጣት እና ከዕቅድ አልባ የህይወት ውዝግብ ውስጥ ለማውጣት ረቂቅ የሆኑ የአዕምሮ መሣሪያዎችን መጠቀም ያስፈልጋል ይላል የቼዝ ዶት ኮም መረጃ፡፡ ለዚህ  ሁነኛ መፍትሄ ደግሞ  የቼዝ  ስፖርት መሆኑን መረጃው ያስረዳል፡፡ ታዲያ ያደጉ ሀገራት ይህን ስፖርት እንደ አንድ የልማት እና የስትራቴጂ መቅረጫ አድርገው ተጠቅመውበታል፤ እየተጠቀሙበትም ነው፡፡

በኢትዮጵያ ግን የቼዝ ስፖርት ገና ምንም ያልተሠራበት እና ትኩረት የተነፈገው የስፖርት ዘርፍ መሆኑን ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ  የማስተዋል ቼዝ አካዳሚ መስራች አቶ ፈለቀ ጌታቸው ይናገራሉ፡፡

ቼዝ  የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ወይም መዝናኛ ብቻ አይደለም፤ ከስልሳ አራቱ ነጭ እና ጥቁር ካሬዎች በላይ የሰፋ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ህይወታችንን ውሳኔዎች በጥንቃቄ እንድንመረምር የሚያስገድድ ረቂቅ ጥበብ እንጂ። አርቆ አሳቢ፣ ችግር ፈቺ እና በምክንያት የሚመራ ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችል  ስፖርት  ጭምር ነው- ቼዝ።

ይህ የስፖርት ዘርፍ ከስህተት መማርን፣ ትዕግስትን እና የሌላውን ሰው (የተጋጣሚን) የአስተሳሰብ አቅጣጫ መረዳትን ያስተምራል፡፡ በቼዝ ጨዋታ ወቅት እያንዳንዱ ተጫዋች የሚወስደው እርምጃ በግብ እና በውጤት የተሰላ ነው፡፡ አንዲትን ፒስ (ጠጠር) ያለ በቂ ምክንያት እና ግብ ማንቀሳቀስ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል። ይህ ሕግ  በሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥም በትክክል የሚሰራ መሆኑን የቼዝ ስፖርት አሰልጣኙ አቶ ፈለቀ ጌታቸው ይናገራሉ፡፡

“በቼዝ ዓለም ውስጥ ስኬታማ እና አሸናፊ የሚያደርገን ብቸኛው መንገድ ተፎካካሪን በመመልከት ብቻ ሳይሆን ቀድመን ያወጣነው እና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነው” እናም ቼዝ እውነተኛውን የችግር አፈታት ክህሎት ለማዳበር እና አዕምሮን  በተግባር ለማለማመድ የሚያስችል ነው ብለዋል ባለሙያው።

ዘመኑ ያመጣው የቴክኖሎጂ እድገት ለቼዝ ስፖርት መስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ምንም እንኳን በሀገራችን በአካል የሚደረጉ ውድድሮች እና የቼዝ ማዕከላት ውስን ቢሆኑም የወቅቱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እድገት ለኢትዮጵያውያን የቼዝ ተጫዋቾች አዲስ እና ሰፊ የዕድል በር ከፍቷል፡፡ የኦንላይን መተግበሪያዎች (እንደ Chess.com እና Lichess ያሉት) ስፖርቱ በሰፊው ማኀበረሰቡ ዘንድ በቀላሉ እንዲደርስ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፤  የቦታ እና የጊዜ ገደብንም አስቀርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ የዲጂታል መተግበሪያዎች ብቻቸውን ግን ዘላቂውን ሀገራዊ ለውጥ እንደማያመጡ የቼዝ ስፖርት አሰልጣኙ አቶ ፈለቀ ተናግረዋል፡፡ እናም ይህን በበይነ መረብ የተፈጠረ መልካም ጅማሮ ወደ መሬት በማውረድ በተደራጀ እና ተቋማዊ በሆነ  መንገድ በመምራት በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ባይ ናቸው የዘርፉ አሰልጣኝ፡፡

ስፖርቱን ለማሳደግ መንግሥት ትልቅ ትኩረት፣ የእውቅና እና የፖሊሲ ድጋፍ ሊያደርግለትም ይገባል፤ በየክልሉ ያሉ የቼዝ ፌዴሬሽኖች በንቃት መንቀሳቀስ እና ለስፖርተኞች ተገቢውን ድጋፍ ክትትል ማደረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቼዝ እንደ ተራ ጨዋታ ሳይሆን በአስተሳሰብ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ የህይወት መቀየሪያ መንገድ ተደርጎ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል- የቼዝ አሰልጣኙ ፈለቀ ጌታቸው አስተያየት ነው።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቼዝ በታዳጊዎች የትምህርት አቀባበል ላይ ቀጥተኛ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ ስፖርቱ ህጻናት ችግሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲመረምሩ፣ አማራጭ የፈጠራ መፍትሔዎችን እንዲያመነጩ እና የሂሳብ ስሌቶችን በአዕምሯቸው በፍጥነት እንዲያሰሉ ያግዛቸዋል። በአጠቃላይ ቼዝ ታዳጊዎች የችግር አፈታት ክህሎቱንም በተግባር እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

ቼዝ  የኢትዮጵያ አዲስ የአስተሳሰብ አብዮት እንዲሆን ከተፈለገ ስፖርቱ ለግለሰብ እድገት ብቻ ሳይሆን ለማኀበረሰብ እና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚጠቅም መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋልም ነው የተባለው፡፡ ጥራት ያላቸው እና ተደራሽ የሆኑ የቼዝ ማሰልጠኛ ማዕከላትን ማስፋፋት፣ በየክፍለ ከተማው፣ በየፓርኮች እና በባህል ማዕከላት ሕዝባዊ የቼዝ ውድድሮችን እና ፌስቲቫሎችን ማዘጋጀት፣ በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ እና በማህበራዊ ሚዲያዎች ስለ ቼዝ ጥቅም ተከታታይ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋልም ተብሏል።

የቼዝ መጫወቻ ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነፃ (Duty Free) ወደ ሀገር የሚገቡበትን አሰራር ማመቻቸት፣ ለቼዝ ፌዴሬሽኖች በቂ በጀት እና የስፖርት መዝወተሪያ ስፍራ ማዘጋጀት፣ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንደ አእምሮ ማበልጸጊያ ተደርጎ እንዲካተት መፍቀድ ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚያግዝ የማስተዋል ቼዝ አካዳሚ መስራች አቶ ፈለቀ ጌታቸው ጠቁመዋል።

ወላጆችም ልጆቻቸው ከስልክ ጌሞች ይልቅ የቼዝ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ ማበረታታት እና መደገፍ ለነገ የማይተው ተግባር መሆኑን አቶ ፈለቀ ጌታቸው ያስረዳሉ። ውስብስብ የሆኑትን የቼዝ ሕጎች እና ስልቶች ማህበረሰቡ በቀላሉ በሚረዳው መንገድ በአማርኛ እና በሀገር በቀል ቋንቋዎች ማዘጋጀትም ለስፖርቱ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጭምር የዘርፉ ባለሙያ አቶ ፈለቀ ያስረዳሉ።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 8  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here