የዕውቀት ቀንዲሏ

0
57

በባሕር ዳር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ተገኝተናል፡፡ የጠይማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቦታው ስንደርስ የከሰዓቱ የትምህርት ጊዜ ደርሶ ስለነበር ተማሪዎቹን የሒሳብ ትምህርት ከክፍል ወጥተው ሜዳ ላይ በቡድን በቡድን ሆነው ሲማማሩ ተመለከትን፡፡

ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄያችን ቀድመው ምላሽ የሰጡን የትምህርት ቤቱ መምህር የሆኑት መምህር በላይነሽ አበበ “ተማሪዎች ሒሳብ እየተማሩ ነው፡፡ መምህርት አስጨነቅ ስታስተምር ትምህርትን ለልጆቹ በሚገባቸው በተግባር ነው፡፡ ተማዎቹ ጠጠር ለቅመው በቡድን ተከፋፍለው እየደመሩ፣ እየቀነሱ፣ እያባዙ የምታስተምርበት ተማሪዎችንም ለመከታተል የሚያመቻት መንገድ ነው” በማለት መለሱልን፡፡

እኛም በዚህ ትምህርት ቤት የመገኘታችን ምክንያት መምህርት አስጨነቅ ሺፈራሁ በመሆናቸው ወደ ተማሪዎቹ የቡድን ውይይት ቀርበን መምህርቷን ለማነጋገር እስኪጨርሱ ጠበቅናቸው፡፡

መምህርትአስጨነቅ ላለፉት 32 ዓመታት በጠይማ ትምህርት ቤት በመምህርነት ያገለገሉ ስኬታማ የሒሳብ መምህርት ናቸው፤ ትውልድ እና ዕድገታቸው በባሕር ዳር ከተማ ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ አንድ ወንድም እና ሰባት እህት አላቸው፡፡

አንደኛ ደረጃ  ትምህርታቸውን ፋሲሎ አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በጣና ሀይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶቸ ተምረዋል፡፡ ከዚያም በሀገር አቀፍ ፈተና ወደ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሚያስባ ውጤት አመጡ፡፡

ይሁን እንጂ በወቅቱ አካላቸው ትንሽ በመሆኑ ለማስተማርም ሆነ ጎንደር ድረስ ሄዶ ለመማር እንዲሁም ሩቅ ቦታ በመሄድ ለማስተማር ትቸገራለች በሚል ቤተሰብ ከለከላቸው፤ በመሆኑም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ ግቢ (በወቅቱ ፔዳ ለብቻው መሆኑን ልብ ይሏል) በሴሚስተር 56 ብር እየተከፈለላቸው መማር ጀመሩ፡፡

መምህርት አስጨነቅ እንደነገሩን በፔዳ በ1977 ዓ.ም የሕብረተሰብ (ጂግራፊ) ትምህርትን መማር እንደጀመሩ ወላጅ አባታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፤ ክፍያውን የሚፈጽም ጠፋ፡፡ የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸው የቤተሰብ አባላትን ለማሳደግ ከእናታቸው ጋር ኃላፊነት ተጣለባቸው፡፡ በመሆኑም ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ጎንደር መምህራን ኮሌጅ በ1978 ዓ.ም ለመሄድ ተገደዱ፡፡

በዓመቱ ተመርቀው በ230 ብር ደመወዝ በመቀጠር ፓዊ መንደር ሲመሠረት ወደዚያ አካባቢ ሄደው እንዲያስተምሩ ተመደቡ፡፡ በቦታው ለሁለት ዓመት አስተማሩ፤ ከዚያም በ1981 ዓ.ም ትዳር መሠረቱ፡፡ በትዳር ምክንያትም ዝውውር አግኝተው ወደ ቅንባባ አካባቢ በመዘዋወር በዚያው አካባቢ ለአምስት ዓመታት አስተማሩ፡፡

ባለቤታቸው ረጅም ዓመት በጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የሠሩ በመሆኑ በባቤታቸው የሥራ ልምድ ከ32 ዓመታት በፊት ወደ ጠይማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዘዋወሩ፡፡ በዚሁ ት/ቤት አሁንም ድረስ በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡

መምህርት አስጨነቅ የማስተማር ሥራን ከልባቸው ወደው የሚሠሩት ተግባር እንደሆነ ያነሳሉ፤ የሚያስተምሯቸው ልጆች ደግሞ ህፃናት በመሆናቸው ትምህርቱን በአግባቡ እንዲረዱ አስፈላጊውን ተግባራዊ ልምምድ ሁሉ እንደሚያቀርቡ ነው የሚገልፁት፡፡

የተማሪ ቁጥር በክፍል ውስጥ አንደዛሬ ሳይበዛ ተማሪዎችን በመረዳት በአግባቡ መከታተል ይቻል እንደነበር ያነሱት መምህርቷ በአሁኑ ወቅት የተማሪ ቁጥር በክፍል ውስጥ ስለበዛ ለመከታተል እና በተግባር ለማስተማር ወደ ግቢ በማስወጣት ሙቀት ሳይሰማቸው በተግባር ጠጠሮችን ለቅመው ያስተምሯቸዋል፤ በዚህም በተለይ የሒሳብ ስሌቶችን (መቀነስ፣ መደመር፣ ማባዛት እና ማካፈል) ቀላል ተግባር መሆኑን መረዳት እንደሚችሉ ይገልፃሉ፡፡

መምህርት አስጨነቅ በትዳራቸው ሁለት ልጆችን አፍርተው ለቁም ነገር አብቅተዋል፤ ከሁለቱ ልጆቻቸው ደግሞ አምስት የልጅ ልጆችን በማግኘት አያት ሆነዋል፡፡

“ወላጅ እናታችን ጠንካራ እና ጥሩ ማሕበራዊ ሕይወት ያላቸው እንዲሁም ልጆቻቸውን በሥነ ምግባር አሳድጋለች፤ ይህን ጥንካሬዋን ወስጀዋለሁ” ይላሉ፡፡

ማንም ሰው ያለፈ ችግርን በማንሳት ሰበብ ሲያስቀምጥ አልቀበልም የሚሉት መምህርት አስጨነቅ “ሰው ያጣውን ወደ ኋላ ካሰበ ወደፊት መራመድ ስለማይችል ያለፈውን ማሰብ የለበትም፤ ይህን ተሞክሮም ለተማሪዎቼ እመክራለሁ፡፡ የተማሪ ወላጅን በማስመጣትም እመክራለሁ” ብዋል፡፡

በዘጠናዎቹ አጋማሽ ባለቤታቸውን በሞት ያጡት መምህርት አስጨነቅ፣ የራሳቸውን ሁለት ልጆች፣ ሰባት እህት እና ወንድማቸውን አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡

ልጆቻቸውን እና እህትና ወንድማቸውን አስተምረው ለቁምነገር ካደረሱ በኋላ ደግሞ በ50 ዓመታቸው እንጅባራ ዩንቨርሲቲ በክረምት መርሃ ግብር ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡

በሐምሌ ወር 2018 ዓ.ም በጡረታ የሚሰናበቱት መምህርት አስጨነቅ፣ በምስጉን ሠራተኝነት 32 ሰርተፍኬት እና ሦስት ሜዳሊያ በሽልማት አግኝተዋል፡፡ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የመማሪያ መጽሐፍ ሲዘጋጅ ደግሞ በኮሚቴነት ተሳትፈዋል፡፡

ወጣት መምህራን አለቃን ፈርተው፣ ደመወዝን አስበው በሰበብ አስባቡ ሲቀሩ እንደሚገስፁ የገለፁልን መምህርቷ “መምህርነት ለተማሪው አስቦ በጥሩ ስነ ምግባር መሥራትን እና አርዓያ መሆንን የሚጠይቅ ሥራ ነው” ብለዋል፡፡

በጡረታ ምክንያት ከመምህርነት ሥራ ቢርቁም ሌሎች አሁንም በትርፍ ጊዜ የሚሠሯቸውን ሥራዎችን ከመሥራት እንደማይቦዝኑ ነው የገለፁት፡፡

መምህርት ብርሃን ሳለሁ ከመምህር አስጨነቅ ጋር ለዓመታት አብረው ያስተማሩ ጓደኛ ናቸው፤  መምህርት አስጨነቅ ጥሩ ሠራተኛ እና ለመምህራንም አርዓያ እንደሆኑ ያነሳሉ፣ ሁል ጊዜ እንደ አዲስ መምህር  ተነሳሽነት ኖሯቸው ሥራቸውን በፍቅር እንደሚሠሩ የገለፁልን መምህርት ብርሃን “መሠልቸት የማታውቅ፣ ሥራውን በፍቅር ወዳው የምትሠራ እና ለወጣት መምህራንም አርዓያ ናት” በማለት ነው ምስክርነታቸውን የሰጡን፡፡

ታናሽ እህቷ ነጻነት አድማሴ በበኩሏ ገና 4ተኛ ክፍል ተማሪ ሆና እናታቸው መሞቷን ገልፃልን አስጨነቅ ክፍተታቸውን ሁሉ እየሞላች ሙሉ አድርጋ እንዳሳደገቻው ተናግራለች፤ ከሥራ ውጭ ባለው ህይወታቸውም ማረፍን የማይወዱ ጠንካራ ሠራተኛ መሆናቸውን ነው የተናረችው፡፡

ማናት

ሳናኤ ታካኢቺ

ሳናኤ ታካኢቺ በጃፓን የመጀመሪያዋ የሀገሪቱ ሴት ጠቅላይ ሚኒሥትር በመሆን ታሪክ የሠሩ ሴት ናቸው።  ጠቅላይ ሚኒሥትሯ  በጃፓን ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ነበራቸው፣ “የጃፓን ብረቷ እመቤት” የሚል ቅጽልንም አትርፈዋል። ጠቅላይ ሚኒሥትሯ በሰው እጅ የተገደሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒሥትር ሺንዞ አቤ ተከታይ ከመሆናቸው በተጨማሪ በጠንካራ ወግ አጥባቂ አቋማቸው ይታወቃሉ።

እስካሁን ባላው የጃፓን የመሪነት መንበር ላይ ወንዶች ሰፊ የበላይነት ይዘው የቆዩ ቢሆንም  ሳናኤ ታካኢቺ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒሥትር ሆነው መምጣታቸው ታላቅ እምርታ መሆኑ እየተነገረ ነው። በርካቶች እንደሚሉትም ይህ የጠቅላይ ሚኒሥትሯ ሹመት በጃፓን ፖለቲካ ውስጥ ቀስ በቀስ እየተቀየረ ላላው የሴቶች ተሳትፎ ውክልና ታሪካዊ ርምጃ ነው።

ጠቅላይ ሚኒሥትር ሳናኤ ታካኢቺ መረጋጋት በሌለው የጃፓን ፖለቲካ በአምስት ዓመት ውስጥ ወደ ሥልጣን የመጡ አራተኛዋ ጠቅላይ ሚኒሥትር ናቸው። የታካኢቺ ድል የመጣው ፓርቲያቸው ሊብራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲካዊ ቅሌት በገጠመው እና የሕዝብ ተቀባይነቱ ዝቅ ባለበት ጊዜ ነው።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያለውን አብዛኛውን ጊዜ ጃፓንን የመራው ፓርቲው ሴት ጠቅላይ ሚኒሥትሩን ለማስሾም ከቀኝ ክንፉ የጃፓን ኢኖቬቲቭ ፓርቲ ጋር ጥምረት ለመመሥረት ከተስማማ በኋላ ነው። ጠቅላይ ሚኒሥትሯ የተቀዛቀዘውን የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለማነቃቃት መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ማዋዕለ ነዋይ እንዲያፈስ የሚያደርግ ርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር በኲር የሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here