የዲፕሎማሲ ልህቀት

0
84

በሰኔ 23 ቀን 1928 ዓመተ ምሕረት (እ.አ.አ. ሰኔ 30 ቀን 1936) ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጄኔቫው የዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) መድረክ ላይ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር በዓለም ዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ እና የዓለምን ሕሊና የሞገተ ታላቅ ክስተት ነው። የዚህ ንግግር መነሻ የፋሺስት ጣሊያን ጦር ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እና የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በግልጽ በመጣስ በሉዓላዊቷ የኢትዮጵያ ግዛት ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ወረራ ነበር። የጣሊያን ጦር ዘመናዊ መሣሪያዎችን እና ዓለም አቀፍ ሕግ ያገዳቸውን መርዛማ ጋዞችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ሕዝብ በጅምላ ሲጨፈጭፍ የዓለም ማኅበረሰብ ግን ጉዳዩን በቸልተኝነት ይመለከተው ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ ዲፕሎማሲያዊ ትግሉን ከአውሮፓ ምድር ሆነው ለመቀጠል እና የሀገራቸውን የጥሪ ድምፅ ለዓለም ለማሰማት ወደ ስደት ካቀኑ በኋላ የመጀመሪያው ትልቅ መድረካቸው ይህ የጄኔቫው ስብሰባ እንነበር በጄኔቫ የተደረገውን የጃንሆይን ንግግር ሙሉ ሀሳብ እና የጉባኤውን ይዘት በይፋ የያዘው ቀዳሚ የሰነድ ምንጭ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ይፋዊ መጽሔት ያስረዳል።

ንጉሡ ወደ ስብሰባው አዳራሽ በገቡበት ወቅት በአዳራሹ የነበሩ የጣሊያን ጋዜጠኞች እና የፋሺስት ደጋፊዎች በታቀደ ሁኔታ ጩኸት፣ ፉጨት እና የፌዝ ድምፅ በማሰማት ንግግሩ እንዳይሰማ እና የንጉሡ ሞራል እንዲሰበር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር። የጉባኤው ሰብሳቢ ረብሻውን ለማስቆም እና ሥርዓት ለማስያዝ ጥረት ካደረገ በኋላ የጣሊያን ተወካዮች ከአዳራሹ እንዲወጡ ተደርገዋል። በዚህ ሁሉ ማዕበል እና ውጥረት ውስጥ ንጉሠ ነገሥቱ ፍጹም በሆነ የረጋ መንፈስ፣ በንጉሣዊ ግርማ እና በጽናት ወደ መድረኩ በመውጣት ንግግራቸውን በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ ቋንቋ ሳይሆን በሀገራቸው  የአማርኛ ቋንቋ ማቅረብ ጀመሩ። ይህ ድርጊታቸው ለሀገራዊ ማንነታቸው ያላቸውን ክብር ያሳየ ከመሆኑም በላይ በወቅቱ ወረራ ደርሶባት ለነበረችው ሀገራቸው ትልቅ የሞራል የበላይነትን የሰጠ ክስተት ነበር።

የንጉሠ ነገሥቱ ንግግር ዋና ይዘት በጋራ ደኅንነት መርህ ላይ የተመሠረተውን የዓለም ሥርዓት መሠረታዊ ድክመት እና ግብዝነት በግልጽ ያጋለጠ ነበር። ጃንሆይ የፋሺስት ጣሊያን ጦር በንጹሐን ዜጎች፣ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ እንዲሁም በተፈጥሮ አካባቢ፣ በወንዞች እና በከብቶች ላይ የረጨውን አደገኛ የሰናፍጭ መርዝ ጋዝ ጭካኔ ለዓለም ማኅበረሰብ በጥልቀት እና በዝርዝር አብራርተዋል። ይህ ጥቃት በሰው ልጆች ላይ ብቻ ሳይሆን በጥቁር ሕዝቦች ላይ ያነጣጠረ ዘረኛነት የተሞላበት ወረራ መሆኑን አስገንዝበዋል። ግጭቱ በሁለት ሀገራት መካከል የተደረገ ተራ የድንበር ውዝግብ ወይም የግዛት ሽሚያ ሳይሆን የዓለም መንግሥታት ማኅበር ራሱ የቆመለትን ዓላማ እና ሕልውና የሚፈትን ትልቅ የታሪክ ማዕዘን መሆኑን በምክንያት አስረድተዋል። ንጉሡ ዓለም አቀፍ ሕግ ደካማ እና አነስተኛ ሀገራትን ከኃያላን ወራሪዎች የመጠበቅ የሞራል እና የሕግ አቅም አለው ወይስ ማኅበሩ የኃያላን ሀገራት ፍላጎት ማስፈጸሚያ ይሆናል? የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ለጉባኤው አባላት በሙሉ አቅርበዋል።

ይህ በጠንካራ አመክንዮ እና በማስረጃ የተደገፈ ንግግር የዓለምን ሕዝብ አስተያየት ሙሉ በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያደላ ያደረገ ሲሆን የማኅበሩን ፍጹም አቅም ቢስነትም ለዓለም ሕዝብ ይፋ አድርጓል። ኃያላን ሀገራት በተለይም እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የራሳቸውን ሰላም እና ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ በጣሊያን ላይ ጠንካራ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የኢኮኖሚና የጦር መሣሪያ ማዕቀቦችን ለመጣል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ይህ መድረክ አጋልጧል። ይህ ዓይነቱ የፍርሃት እና የጥቅም ስሌት የተሞላበት አካሄድ የማኅበሩን መፈራረስ ያፋጠነ እና ዓለም አቀፍ የሕግ የበላይነትን የናደ ታሪካዊ ስህተት ሆኖ ተመዝግቧል።

ጃንሆይ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ ለዓለም መሪዎች ያስተላለፉት ማስጠንቀቂያ “ዛሬ በእኛ ላይ የደረሰው ወረራ እና ግፍ ነገ በእናንተ ላይ መድረሱ አይቀሬ ነው” የሚል ነበር። ይህ ንግግር በወቅቱ እንደ ተራ የቁጭት መግለጫ ተወስዶ የነበረ ቢሆንም ከሦስት ዓመታት በኋላ 1939 እ.አ.አ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ እና አውሮፓ በናዚ ጀርመን እና በጣሊያን እሳት ስትታመስ በተግባር የታየ እውነተኛ ትንቢት ሆኗል።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጄኔቫው የዓለም መንግሥታት ማኅበር መድረክ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ሙግት በሚያደርጉበት ወቅት፣ በሀገር ውስጥ የነበሩት ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደሉ መራራ የነፃነት ተጋድሎ ያደርጉ ነበር። የጣሊያን ጦር ዋና ዋና ከተሞችን እና የትራንስፖርት መስመሮችን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ እንደገዛ ለዓለም ቢያውጅም፣ በየገጠሩ የነበረው የአርበኞች የውስጥ ተጋድሎ ግን ወራሪው ኃይል ለአፍታ እንኳ ሰላም እንዳያገኝ አድርጎታል። ይህ የሀገር ውስጥ ተጋድሎ የፋሺስትን አስተዳደር መዋቅር በማዳከም እና ለኢትዮጵያ ነፃነት መመለስ ወሳኝ ሚና የተጫወተ የታሪካችን ወርቃማ ምዕራፍ ነው።

የውስጥ አርበኝነቱ ተጋድሎ በዋናነት የተመሠረተው በሰደፍ ውጊያ (Guerrilla Warfare) ስልት ላይ ነበር። አርበኞቹ የሀገሪቱን አስቸጋሪ መልክዓ ምድር ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው በጣሊያን የጦር ሠራዊት ስምሪት እና የማከማቻ መጋዘኖች ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር ከፍተኛ ኪሳራ ያደርሱ ነበር። የፋሺስት ጦር ዘመናዊ ታንኮች፣ አውሮፕላኖች እና የመርዝ ጋዞች ቢኖሩትም በየጫካው እና በየተራራው ለሚሸሸጉት አርበኞች ምቹ አልነበረም። አርበኞቹ የጠላትን የስልክ መስመሮች በመበጠስ፣ ድልድዮችን በማፍረስ እና ስንቅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችን በመቅማት የጣሊያንን የጦር እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ሽባ ያደርጉት ነበር ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልጸዋል።

በዚህ የውስጥ ተጋድሎ ውስጥ የሴቶች ሚና እጅግ ከፍተኛ እና ታሪካዊ ነበር። እንደ እቴጌ መነን አስፋው፣ ልዕልት ፀሐይ ኃይለስላሴ እና አርበኛ እሸቴ ደምሴ ያሉ ታዋቂ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ እናቶች እና እህቶች ለአርበኛው የጀርባ አጥንት ነበሩ። ሴቶቹ ለአርበኞች ስንቅ በማዘጋጀት፣ ቁስለኞችን በማከም፣ የጠላትን መረጃ በምስጢር በማቀበል እና አስፈላጊ ሲሆንም ጠመንጃ አንስተው ግንባር ድረስ በመዋጋት አቻ የሌለው መስዋዕትነት ከፍለዋል። በተለይም “የውስጥ አርበኞች” በመባል የሚታወቁት በከተሞች ውስጥ በጣሊያን መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ዜጎች የጠላትን የጦር ዕቅድ አስቀድመው ለጫካ አርበኞች በማድረስ ረገድ ትልቅ ሥራ ሰርተዋል።

የኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ መሪዎች ስም ዛሬም ድረስ በክብር ይነሳል። እንደ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዝማች ኃይለ ማርያም ማሞ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ እና በላይ ዘለቀ ያሉ ጀግኖች የወራሪውን ጦር እንቅልፍ የነሱ ስመ ጥር አርበኞች ነበሩ። በተለይም በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓመተ ምሕረት አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም በታሪካዊው ጨካኝ የጣሊያን እንደራሴ ማርሻል ግራዚያኒ ላይ የሰነዘሩት የግድያ ሙከራ የፋሺስትን የውስጥ መዋቅር ያናወጠ እና ሕዝቡ ለተጨማሪ ተጋድሎ እንዲነሳሳ ያደረገ ትልቅ ክስተት ነበር። ምንም እንኳን ጣሊያን በዚሁ ምክንያት በከተማው ሕዝብ ላይ አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ ቢያካሂድም የአርበኞቹን የልብ ትርታ ግን ሊያቆም አልቻለም።

ለአምስት ዓመታት የተካሄደው ይህ መራራ የውስጥ ተጋድሎ ጣሊያን ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ረግቶ እንዳይገዛ እና የሀገሪቱን ሀብት እንዳይበዘብዝ አድርጎታል። ይህ የሀገር ውስጥ ጽናት ከውጭው የዲፕሎማሲ ትግል ጋር ተዳምሮ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ድጋፍ እንድትሰጥ በር ከፍቷል።

የጃንሆይ የጄኔቫ ንግግር የኢትዮጵያን ሕዝብ የነፃነት ተጋድሎ ለዓለም ከማስተዋወቁም በላይ የዓለም መንግሥታት ማኅበር እንዲፈርስ ያደረገ ታሪካዊ ሰነድ ነው። ንግግሩ ዛሬም ድረስ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በዲፕሎማሲ ትምህርት ውስጥ የጋራ ደኅንነት መርህ ውድቀትን ለማሳየት እንደ ዋነኛ መማረሪያ እና ምሳሌ ሆኖ ይጠቀሳል። ኢትዮጵያውያን በጦር ሜዳ የከፈሉትን መስዋዕትነት በዲፕሎማሲው መድረክም የታገሉበት እና የጥቁር ሕዝቦችን ኩራት እና ክብር በዓለም ፊት ያስመሰከሩበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ሳምንቱ በታሪክ

 

የንጉሥ ላሊበላ እረፍት

የዛግዌ ሥርወ-መንግሥት ታዋቂው ንጉሥ ጻድቁ ቅዱስ ላሊበላ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየበት (ያረፈበት) ዕለት ሰኔ 12 ቀን መሆኑ በኢትዮጵያ ስንክሳር እና የታሪክ ድርሳናት ተመዝግቧል። ይህ ዕለት በየዓመቱ በቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ይዘከራል።

ንጉሥ ላሊበላ ዕድሜው በገፋ ጊዜ ሥልጣኑን ለወንድሙ ልጅ ለአንኳ ረዓብ (ነአኩቶ ለአብ) በገዛ ፈቃዱ አስረክቧል። ከዚያም ቀሪ ዘመኑን በጸሎት እና በብሕትውና ካሳለፈ በኋላ በሰኔ 12 ቀን አርፏል። ሥጋውም እርሱው ራሱ ካሳነጻቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በሆነው በቤተ ጎልጎታ (በተለይ ሥላሴ ተብሎ በሚታወቀው ምሥጢራዊ ክፍል) ውስጥ በክብር ማረፉ እና እስከ ዛሬም ድረስ መቃብሩ እዚያ እንደሚገኝ ይታመናል።

ፈረንሳይ እጅ ሰጠች

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ሰኔ 15 ቀን 1932 ዓ.ም የፈረንሳይ መንግሥት በናዚ ጀርመን ፊት ይፋዊ የእጅ መስጠት ስምምነት የፈረመበት ነው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደንጋጭ እና ትልቅ የኃይል ሚዛን መዛባትን የፈጠረ ጥቁር የታሪክ ዕለት ነው።

አዶልፍ ሂትለር የፈረንሳይን የሽንፈት ስምምነት ለማስፈረም የመረጠው ቦታ ፍጹም የበቀል ስሜት የተሞላበት ነበር። ስምምነቱ የተፈረመው በፈረንሳይ ኮምፒዬኝ (Compiègne) ጫካ ውስጥ በሚገኝ አንድ ታሪካዊ የባቡር ፉርጎ ውስጥ ነበር ይላል ብሪታኒካ።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሰኔ 8  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here