በጃፓን የኦሳካ ዩኒቪርሲቲ ተመራማሪዎች በሰው ሰራሽ “ፎቶ ሲንተሲስ” ወይም የፀሀይ ብርሃንን በመጠቀም ከውኃ እና ከካርቦንዳይኦክሳይድ (co2) ለነዳጅነት የሚውል “ፎርሚክ አሲድ ”ን ማመንጨት መቻላቸውን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
“ፎርሚክ አሲድ” ወይም “ Hcooh ” ወይም ካርቦሲክሊክአሲድን በቀጥታ በኃይል ምንጭነት ማዋል የሚያስችል አነስተኛው ውህድ ነው፡፡ ሂደቱ ከፀሀይ የተረጋጋ፣ ወጪ እና ውስብስብነትን የሚቀንስ የነዳጅ ምርትን ማግኘት ያስችላል ነው የተባለው- በድረ ገጹ፡፡
የነዳጅ ወይም የኃይል ምንጭ የማምረት ሂደቱ በባትሪ ላይ የተመሰረተ የቁጥጥር መሣሪያዎች አስፈላጊነትን ያስወገደ ነው፡፡ ሰውሰራሽ የፀሀይ ብርሃን መቀበያ ንጣፉ የሚይዛቸውን የፀሀይ ብርሃን ከውኃ እና ካርቦንዳይኦክሳይድ ጋር አዋህዶ ነዳጅ (ፎርሚክ አሲድ)ን በማመንጨት ራሱን በራሱ ኃይል ማመጣጠንን በራሱ እንዲከውን ነው ያደረጉት- ተመራማሪዎቹ፡፡ ይህም ተጨማሪ ባትሪ ወይም የኃይል ቋት ፍላጐትን ማስቀረት አስችሏል፡፡
በተለመደው መልኩ ለነዳጅ ምርት ባትሪ መገልገል የፀሀይ ብርሃን ሲቀንስ ተጨማሪ ኃይል ለመስጠት ቢሆንም ሂደቱ በራሱ የፀሀይ ብርሃን ሲጨምር የኤሌክትሪክ ኃይል ፍሰቱ እንዲቀንስ እና በተመጠነ መልኩ እንዲደርስ በማስቻል መሰራቱ መፍትሄ መሆኑን ነው ያብራሩት- ተመራማሪዎቹ፡፡
በመሆኑም ራሱን በራሱ በማስተካከል ወይም የፀሃይ ብርሃንን በማመጣጠን ያለ ባትሪ እና ተጨማሪ ጥገኝነት ያለማቆራረጥ “ፎርሚክ አሲድ”ን ማመንጨት እንደሚቻል ነው በማደማደሚያነት የድረ ገጹ ጽሁፍ ያሰፈረው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


