በምን ያስታውሱናል?

0
380

አብርሃም ሊንከን ዲሞክራሲን ተክሎ አለፈ። ቶማስ ኤዲሰን መብራትን ሰጥቶ ሄደ። ካርል ዩንግ የተተነተነ የልቦና እውቀትን ተወልን። ስቲቭ ጆብስ አፕልን ሰጠን…። እኛስ ለልጅ፣ ለሰፈር፣ ለሀገር፣ ለትውልድ የምንተወው ምን ይሆን?

በዚህ ምድር ላይ የምናሳልፈው ጊዜ  ጎህ ሲቀድ እንደሚጠፋ ጤዛ፣ እንደ ዥረት ውሃ አላፊ ነው። ነገር ግን ሰዎች ከዚህች ዓለም ሲለዩ የሚቀሩት በቁሳዊ ሀብታቸው አይደለም።

የሰው ልጅ ዋጋ የሚለካው በኪሱ ባለው ገንዘብ ሳይሆን በምድር ላይ ባኖረው አሻራ ነው። አሻራ ማለት መሬት ላይ የምንተወው የእግር ምልክት ብቻ ሳይሆን በሰዎች ልቦና እና በታሪክ ገጽ ላይ የምንቀርጸው የማይረሳ የሕይወት ፊርማ ነው።

ሰፈር ጥቂቶችን ያስታውሳል። በነበር የሚጠራቸው ክፉም ደግም የዋሉ ሰዎች አልፈዋል። ሀገር ከሚሊዮን ሰዎች መሐል ጥቂቱን በአሻራቸው የተነሳ ይጠቅሳቸዋል። ዓለም ትንሽ በርከት የሚሉ መልካምም ሆነ መጥፎ አሻራ ያላቸው ቀደምት ሰዎችን መዝግቦ ይዟል።

መታዎሻ መኖሩ አንድ ነገር ነው። ዋናው ነጥብ ምን ለትውልድ የሚጠቅም ነገር አስቀምጠው አለፉ የሚለው ነው። ሁሉም ትውልድ፣ሁሉም ሀገር፣ ሁሉም ሕዝብ ታሪክ አለው። በውጤት ግን እኩል ክብደት የላቸውም። ክብደት ያለው ተመዝግቧል።

የእኛስ ታሪክ የሚመዘገብ ነው? ሰፈር ያውቀን ይሆን፣ ሀገር ያወራልን ይሆን፣ ዓለም በወሬው መሐል ይጠቅሰን ይሆን?

የታሪክ ምሁሩ ዊል ዱራንት “የስልጣኔ ታሪክ” በተሰኘው  መጽሐፋቸው እንደሚያስረዱት የሰው ልጅ ታላቅነት የሚለካው ለቀጣዩ ትውልድ ባስተላለፈው እውቀት እና በገነባው እሴት ነው።

ጥንታዊቷ ግብፅ ፒራሚዶቿን ስትተውልን፣ ግሪኮች ፍልስፍናቸውን ትተውልናል። እነዚህ ሰዎች የኖሩት ለራሳቸው ብቻ አልነበረም። የሥነ-ልቦናው አባት ሲግመንድ ፍሮይድ እንደሚለው የሰው ልጅ ዋና  ዓላማ  “መፍጠር” ወይም “ማበርከት” ነው። ይህ የምንተወው ነገር የሞት ፍርሃትን የምንረታበት እና ዘላለማዊነትን የምንጎናጸፍበት መሣሪያችን ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር የቅድመ አያቶቻችን አሻራ በየቦታው ይታያል። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የጅማ አባ ጅፋር ቤተ-መንግሥት፤ እነዚህ ሁሉ ዝም ብለው አልተገነቡም። “እኔ ካለፍኩ በኋላ ለሚመጣው ትውልድ የሚታይ ነገር ይኑር” የሚል የጥልቅ ትጋት እና ራዕይ ውጤቶች ናቸው።

ስቴፈን ኮቪ “የስኬታማ ሰዎች ሰባት ልማዶች” በሚል መጽሐፉ  አሻራን ማኖር የሚቻለው በስርዓት እና በራዕይ እንደሆነ ያስተምራል። ኮቪ በመጨረሻው ግብ መጀመር ሲል እያንዳንዱ ሰው ሕይወቱን እንደ ፕሮጀክት እንዲመለከተው ይመክራል። አንባቢውን እንዲህ ይጠይቃል “የቀብር ሥነ-ሥርዓትህ ላይ ሰዎች ስለ አንተ ምን እንዲሉ ትፈልጋለህ?”

ይህ ጥያቄ የአሻራችንን ጥግ ይወስናል። እውነተኛ አሻራ የምንተወው ተነሳሽነት ሲኖረን ነው። ችግሩን በሌሎች ላይ ከመጫን ይልቅ በራሳችን መፍትሔ መፍጠር ስንጀምር ነው።

እንዲሁም የአሸናፊነት አስተሳሰብ ሲኖረን ነው።  በሌሎች ውድቀት ላይ ሳይሆን በሌሎች እድገት ላይ ስንሠራ ብቻ ነው። በተጨማሪም የጋራ መደጋገፍ ሲኖር ነው። አንድ እና አንድ ሲደመሩ ሁለት ሳይሆን አስር እንዲሆኑ የሚያደርግ የጋራ ጥረት ስናደርግ ነው።

እነዚህ ልማዶች እኛን ከራስ ወዳድነት አውጥተው ለአንድ ትልቅ ዓላማ እንድንኖር ያደርጉናል። አሻራ የሚጀምረው በግል ድል ሲሆን የሚያበቃው ደግሞ በህዝባዊ ትብብር  ነው።

የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች እንደሚሉት የሰው ልጅ አሻራን የመተው ፍላጎት  የደስታ እና የጤናማነት መሰረት ነው። በኤሪክ ኤሪክሰን የሳይኮ-ማህበራዊ እድገት ቲዮሪ መሠረት አንድ ሰው በጉልምስና ዕድሜው ካልተሳካለት የሚገጥመው “መደንዘዝ” ነው። ሰዎች ለራሳቸው ብቻ ሲኖሩ ከስሜት መረበሽ እና ከመሰላቸት ጋር ይታገላሉ። ነገር ግን አሻራቸውን ለሌሎች ሲያሳርፉ የህይወት ትርጉም ይፈጠርላቸዋል።

በዚህ ዘመን የተደረጉ ማህበራዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ታላላቅ አሻራ የጣሉ ሰዎች የተዋሐዱባቸው ዋና ዋና መርሆዎች አሉ። እነርሱም ርህራሄ፣ ታማኝነት፣ እና ቀጣይነት ያለው ትምህርት  ናቸው።

አሻራ ሁሌም ዓለምን የሚያናውጥ መሆን የለበትም። የ”አቶሚክ ሀቢትስ”  ደራሲ ጄምስ ክሌር እንደሚለው ትንንሽ ለውጦች (1%) በጊዜ ሂደት ትልቅ ውጤት ይኖራቸዋል።

ዛሬ የምትናገረው ደግ ቃል፣ በስራ ቦታ የምትሰጠው ታማኝ ውሳኔ፣ ለልጅህ የምታስተምረው የስራ ፍቅር፤ እነዚህ ሁሉ በአንተ የህይወት መጽሐፍ ላይ የሚቀረጹ የማይጠፉ አሻራዎች ናቸው ይላል።

ስቲቭ ጆብስ “ዓለምን መቀየር የሚፈልጉ ሰዎች ብቻ ናቸው የሚቀይሯት” ብሏል። ዓለምን መቀየር ማለት ግን ሰማይና ምድርን ማናወጥ አይደለም። ዓለም ማለት አንተ በምትኖርበት ቤት፣ በምታገለግለው ሰፈር፣ በምትሠራበት ድርጅት ውስጥ ያለችው አነስተኛ ዓለም ናት። አንተ ያንን ክፍል ስታሻሽል የመላው ዓለም አሻራ ቀያሪ ትሆናለህ።

ዓለምን የቀየሩ መልካም ተግባራት፣ የፈጠራ ሥራዎች፣ የነጻነት ተጋድሎዎች የተጀመሩት በአንድ ሰው፣ ትንሽ ቤት ወይም መንደር ውስጥ ነበር።

የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ የኢትዮጵያውያን መታወቂያ እንዲሆን ያደረገው የአበበ ቢቂላ ጀብዱ የጀመረው በጃቶ መንደር ነው። ምንም አይነት የቅንጦት ትጥቅ ሳይኖረው በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ ባዳበረው ጽናት በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ የዓለምን ትኩረት ሰረቀ። የእርሱ ያቺ ትንሽ መንደር ውስጥ የጀመረች ልምምድ ዛሬ ኢትዮጵያን በረጅም ርቀት ሩጫ የዓለም ቁንጮ እንድትሆን አድርጓታል።

ከዓመታት በፊት ባንግላዲሽ በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ ሙሐመድ የኑስ የተባሉ ሰው ለደሀ ሴቶች ከኪሳቸው 27 ዶላር ብቻ በማውጣት ብድር ሰጡ። ይህ ድርጊታቸው “ማይክሮ ፋይናንስ” የተባለውን የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጽንሰ-ሀሳብ ወለደ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ከድህነት ያወጣው ይህ እንቅስቃሴ ዛሬ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ተጠቃሚ አድርጓል። አንዲት መንደር ውስጥ የተጀመረች ትንሽ የርህራሄ ተግባር ዓለም አቀፍ የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ሆነች።

አንባቢያን ሆይ! ቆም ብለን አናስብ። እኛ ከሞትን በኋላ በሰፈራችን ማን ያስታውሰናል? ለልጆቻችን ምን አይነት የእሴት አሻራ ትተንላቸው ነው የምንሄደው? ሀገራችንን በምን አይነት አስተሳሰብ ነው የምንቀርጻት?

አሻራ ማለት በድንጋይ ላይ የሚቀረጽ ስም ብቻ አይደለም። አሻራ ማለት በሰው ልብ ውስጥ የሚቀረጽ ፍቅር፣ በሀገር ህንጻ ውስጥ የሚቀመጥ ታማኝነት እና በትውልድ አእምሮ ውስጥ የሚቀመጥ አርአያነት ነው።

ጊዜው የኛ ነው። የዛሬው ጥረታችን የነገው ታሪካችን ነው። አብርሃም ሊንከን፣ ቶማስ ኤዲሰን፣ ካርል  ዩንግ፣ ስቴፈን ኮቪ እና  ስቲቭ ጆብስ የየራሳቸውን ታሪክ ጽፈዋል። እኛስ?

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር በኲር የሰኔ 22  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here