ሰማኒያ ሺህ ሰዎችን እንድትይዝ ታስባ በ1990ዎቹ ንድፏ የተሰራ ግዙፍ ሀገር አቋራጭ መጓጓዣ መርከብን ከ30 ዓመታት በኋላ ለመገንባት ክሩዝ ላይን ኢንተርናሽናል የተሰኘ ኩባንያ እቅድ ማቅረቡን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በአሜሪካዊው መሀንዲስ ኖርማን ኒክሰን የተሰራን “ፍሪደም” የተሰኘ ግዙፍ የመርከብ ንድፍ ባለፉት ዓመታት ለመስራት ሳይቻል ቀርቷል -እነሆ ከ30 ዓመታት በኋላም የግዙፏን መርከብ ግንባታ ለማስጀመር 16 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገንቢው ኩባንያም ወጪዋን አስልቶ አስቀምጧል፤ በሰው ኃይልም 12 የተካኑ የኘሮጀክት አስተዳደሪ ባለሙያዎችን… ቀጥሯል፡፡
ግዙፏ መርከብ 240 ሜትር ስፋት፣ ባለ30 ወለል ወይም ፎቅ ከፍታ እንዲሁም የጐን ርዝመቷ 1600 ሜትር ነው የተለካው – ኖርማን ኒክሰን በሰራው ንድፍ፡፡
መርከቧ ተሰርታ ስትጠናቀቅ 50 ሺህ ተጓዦች፣ 10 ሺህ ጐብኚዎችን እና 20 ሺህ የራሷን ሰራተኞች ተሸክማ በባህር ላይ ትጐማለላለች፡፡
በጥቅሉ ግዙፏ “ፍሪደም” መርከብ ተሰርታ ስትጠናቀቅ አሁን ካሉት ትልቅ ወይም ግዙፍ ከሚባሉት መርከቦች ስምንት እጥፍ እንደምትበልጥ እና ሆስፒታል፣ ት/ቤት፣ ባንክ፣ ሱቆች፣ ፌስቶራንት እንደሚኖራትም ነው በንድፉ የተካተተው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


