በባሌ ዞን ምስራቃዊ ቀጣና፣ ዳዌ ቃጨና ወረዳ ነው የሚገኘው -ሶፍ ኡመር ዋሻ፡፡ ዋሻው ከባሌ ዞን ዋና ከተማ ሮቤ 110 ኪሎ ሜትር፣ በቅርብ ከምትገኘው የጐሮ ከተማ ደግሞ 40 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡
የሶፍ ኡመር ዋሻ በ11ኛው ክፍለ ዘን የእስልምና ሀይማኖት ወደ ቀጣናው ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ስሙ ገኖ እውቅና አግኝቷል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው በዚያን ጊዜ ወደ ቦታው ባቀኑ ሺህ ሶፍ ኡመር አህመድ በተባሉ የእስልምና ሃይመኖት አባት የእምነት ቦታ በመሆኑ ነበር፡፡
በሌላ መረጃ የስያሜው መነሻ “sof’’ ቀዝቃዛ “omar’’ ወተት ከሚል የአረብኛ ቃል ጋር የተያያዘ ነው የሚሉ ወገኖችም አለ፡፡ ያም ሆነ ይህ የወይብ ወንዝ ከባሌ ከፍተኛ ቦታዎች ተነስቶ ቁልቁል አንድ ሺህ ሜር ወርዶ አግድም 15 ኪሎ ሜትር ወስጥ ለውስጥ የቦረቦረው ዋሻ መሆኑ ሁሉንም ያሰማማ ሀቅ ነው፡፡
የወይብ ወንዝ በዋሻው ውስጥ ግራ እና ቀኝ የኖራ ድንጋዩን እየጠረበ አስገራሚ ቋሚ ምሰሶዎች እና ግድግዳዎችን አኑሯል፡፡ዋሻው አንዳንድ ቦታ ሲጠብ በሌላው እስከ ስድስት ሜትር ስፋት ተለክቷል፡፡
በዋሻው ውስጥ የሌሊት ወፍ፣ ዓሳ፣ መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ ዋሻው ውስጥ ዘልቆ ለመጐብኘት ቅዝቃዜውን እና ወንዙን ታሳቢ ያደረገ አለባበስ ይሻል፡፡ በወጉ ለመመልከትም የእጅ ባትሪ መያዝ ግድ ይላል ፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ኦሮሚያ ቱሪዝም፣ ባሌ ኤቨርላስቲንግ ቱር እንዲሁም ዩኔስኮ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


