የተመድ ጉዞ

0
226

ከ50ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሞቱበት በሚገመተው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ዓለም አቀፍ ሰላምን ለማስፈን አዲስ መዋቅር እንዲፈጠር የሚጠይቅ ግፊት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህም በ1945 በሳን ፍራንሲስኮ የተፈረመውን የተመድ ቻርተር እና በጥቅምት 24 ቀን 1945(እ.አ.አ) በይፋ የተመሠረተውን ድርጅት ወለደ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ80 ዓመታት በፊት 51 ሀገራት በጋራ ሲያቋቋሙት የራሱ ቻርተር ያለው፣ አባል ሀገራቱ በየዓመቱ በሚያዋጡት መዋጮ የሚተዳደርና የነዚህን ሉዓላዊ ሀገራት ፍላጎት እና የጋራ ዓላማ በተግባር ለመተርጎም የተቋቋመ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡

 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የተመሠረተበት ዋና አላማም የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅ እና የዓለም አቀፍ ሕግን ለማስከበር ነው፡፡ ሌላ ተመሳሳይ የዓለም ጦርነት እንዳይከሰት ለመከላከል፣ በዓለም ዙሪያ ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር እንዲሁም ለመላው የዓለም ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቃሚ ጉዳዮችን መከወን የሚሉ እቅዶችን አንግቧል፡፡

የተመድ አወቃቀር

ዛሬ ላይ 193 አባል ሀገራት ያሉት የተባበሩት መንግሥታት በድርጅቱ ቻርተር መሠረት ሁሉም የድርጅቱ አባል እኩል ሲሆኑ አምስቱ ግን ከሌሎች የተለየ (በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል በመሆናቸው)ድምጽን በድምጽ የመሻር የቬቶ ሥልጣን አላቸው፡፡ እንዲሁም ድርጅቱ ከ30 በላይ በዋና ዋና ተቋማት የተዋቀረ ነው፡፡

 

የዓለም ጤና ድርጅት፣ የትምህርት፣ የዓለም የሳይንስና የባህል ማእከል (ዩኔስኮ)፣ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት(FAO)፣ የዓለም ባንክ(IMF)፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ፕሮግራም፣ ዩኤን ውሜን… ይገኙበታል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስድስት ዋና አካላት ያሉት ሲሆን እነሱም ጠቅላላ ጉባኤ (General Assembly)፣ የጸጥታው ምክር ቤት (Security Council)፣ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ምክር ቤት (ECOSOC)፣ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (International Court of Justice)፣ የተመድ ጽሕፈት ቤት (Secretariat) እና የአደራ ምክር ቤት (Trusteeship Council)ናቸው፡፡

የድርጅቱ ስኬቶች

በተባበሩት መንግሥታ ድርጅት መመስረት ምክንያት በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ሰላም እና ፀጥታ ላይ ያስመዘገበው ውጤት ነው፡፡ ድርጅቱ በዓለም ዙሪያ ተደጋግመው ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችንና ጦርነቶችን በመቆጣጠር፣ የሰላም አስከባሪዎችን (Peacekeepers) በማሰማራት አብዛኛውን የዓለም ሀገራት ከከፍተኛ ጦርነት እና ግጭቶች  ታድጓል፡፡ በናሚቢያ፣ በሴራሊዮን፣ በአንጎላ፣ በሞዛምቢክ፣ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲ፣ በካምቦዲያ፣ በኤልሳልቫዶር፣ በጓቲማላ፣ በምሥራቅ ቲሞር እና በሌሎች ሀገራት የእርስ በርስ ግጭቶችን በማስቆም የብዙዎችን ሕይወት ማዳን ችሏል፡፡ እንዲሁም በታላላቅ ሀገራት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ  እንዲፈቱ የውይይት መድረክ ፈጥሯል፡፡

ሌላው ያስገኘው መልካም ውጤት በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዙሪያ ሲሆን እ.አ.አ በ1948 የወጣው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) ለሰው ልጆች ሁሉ እኩልነትና ክብር ዓለም አቀፍ እውቅናን አጎናጽፏል፡፡ እንደ ፈንጣጣ (Smallpox) ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የሚዳርጉ  በሽታዎችን በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በኩል ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ችሏል፡፡ በዚህም የሕዝብ ጤና እንዲሻሻል አድርጓል፡፡

በየዓመቱም ሚሊዮኖችን የሚገድሉ በሽታዎችን ለመቀነስ የክትባት መርሃ ግብሮችን፣ የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ፕሮግራሞችን እና የተላላፊ በሽታዎች የቁጥጥር ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ በሌላ በኩል በሕጻናት ፈንድ (UNICEF)በኩል ለትምህርት፣ ለንጹህ ውኃ እና ለምግብ ዋስትና የሚደረጉ መርሐ ግብሮችን(ፕሮግራሞችን) አጠናክሯል፡፡

 

በተጨማሪም በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር (UNHCR) እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) አማካይነት በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ሚሊዮኖች የዕለት ደራሽ እና የረጅም ጊዜ ድጋፎች ተደርገዋል፡፡ እንዲሁም ዘላቂ የልማት ግቦችን ማለትም (SDGs) ድህነትን ለመቅረፍ፣ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ አጀንዳ 2030 የመሳሰሉ ዕቅዶችን በመንደፍ የጋራ የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ አድርጓል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለምን ይተቻል?

ድርጅቱ በ80 ዓመታት ውስጥ ከ70 በላይ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮዎችን አካሂዷል፡፡ ይሁንና ሁሉም ተልዕኮዎች ስኬታማ አልነበሩም፡፡ እ.አ.አ በ1994 በሩዋንዳ የተፈፀመው አሳዛኝ የዘር ማጥፋት እና እ.አ.አ በ1995 በቦስኒያ የተፈፀመውን ተመሳሳይ እልቂት የፖለቲካ ተቺዎች እንደ ድክመት ያነሳሉ፡፡ ድርጅቱ  እነዚህ እልቂቶች ከመከሰታቸው በፊት የሁኔታውን አሳሳቢነት በመረዳት በቂ ወታደራዊ ኀይል ባለማሰማራቱ ይወቀሳል፡፡

በሩዋንዳ የጅምላ ጭፍጨፋ ወቅት በ100 ቀናት ውስጥ በግምት ስምንት መቶ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ በኋላ ላይ የተመድ ባለሥልጣናት ጭፍጨፋውን በፍጥነት ባለማስቆማቸው የድርጅቱ ከባድ ውድቀት እንደ ነበረ አምነዋል፡፡ በዚህ ምክንያት “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዛሬም ለጅምላ ግድያዎች ምን ያህል ፈጣን ምላሽ መስጠት ይችላል?” በሚለው ጥያቄ ይፈተናል፡፡

በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት የተመድ ትልቁ ድክመት የጸጥታ ምክር ቤቱ አወቃቀር ነው፡፡ የምክር ቤቱ አምስቱ ቋሚ አባላት እና የቪቶ መብት ያላቸው ሀገራት ብዙ ጊዜ ውሳኔዎች እንዳይተላለፉ ያደርጋሉ፡፡   በዚህም ዓለም አቀፍ ግጭቶች ሲከሰቱ የተመድ አቋም ከሕግ ይልቅ በኃያላን ሀገራት የፖለቲካ ፍላጎት ይወሰናል የሚል ትችት ይቀርብበታል፡፡ ለአብነትም ይህ ሁኔታ በዩክሬን ጦርነት፣ በጋዛ ቀውስ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ድርጅቱ ፈጣንና ውጤታማ ውሳኔ እንዳይወስድ አድርጎታል በሚል ትችት ይሰነዘርበታል፡፡ እንዲሁም “ኃያላን ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች በሌሎች ሀገራት ላይ ያደረጉትን ወረራ እና የሀገራትን የእርስ በርስ ጦርነት እና ውድመት ለማስቆም አቅም ያንሰዋል“ የሚለው ድርጅቱ ሌላው ትልቁ የሚወቀስበት ጉዳይ ነው፡፡

ከነዚህም መካከል በኢራቅ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ፍልስጤም እና በሌሎች ሀገራት በኃያላን መንግሥታት በተደረገ ጥቃት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰወች ለሞት እና ለአካል ጉዳተኝነት ተዳርገዋል፡፡ ሀገራቱ ፈራርሰው ለእርስ በርስ ግጭት ተዳርገዋል፤ ይህም ለሚሊዮኖች ስደት እና ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡

በ80ኛ ዓመት አከባበሩ ላይ በጣም ተደጋግሞ የተነሳው ጉዳይ የአፍሪካ ውክልና ነበር፡፡

አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሕዝብ ያላት አፍሪካ በጸጥታው  ምክር ቤት ቋሚ ወንበር የላትም፡፡ የአፍሪካ ሕብረት (African Union) በተደጋጋሚ ቢያንስ ሁለት ቋሚ ወንበሮች ለአፍሪካ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡ ብዙ አፍሪካዊ ዲፕሎማቶች የ1945 የኀይል ሚዛን በ2026 የዓለም እውነታን አይወክልም ይላሉ፡፡

በ80ኛው ዓመት መድረክ ላይ የተመድ ዋና ጸሐፊ የአንቶኒዮ ጉተሬዝ የዓለም ተቋማት ከዘመኑ ጋር መራመድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡“የ1945 ተቋማት የ2025 እና የ2026 ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት አይበቁም” የሚለው ሃሳብ በተደጋጋሚ በእርሳቸው ንግግሮች ውስጥ ተደምጧል፡፡

ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት

ኢትዮጵያ በወቅቱ( እ.አ.አ በ1945) የሀገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር በነበሩት  አክሊሉ ሃብተወልድ መሪነት የድርጅቱን ቻርተር ያረቀቀች እና በ1945 ድርጅቱ ሲቋቋም ከነበሩት 51 መስራች አባል ሀገራት አንዷ ናት፡፡  ከዛን ጊዜ ጀምሮም የተመድ አባል ሆና ቀጥላለች፡፡

የሀገሪቱ ዋና መዲና አዲስ አበባም የአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያቤት መቀመጫ በመሆኗ በርካታ  የተመድ ተቋማት እና ቢሮዎችም በከተማዋ ይገኛሉ፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በምግብ ዋስትና፣ በስደተኞች እና በድርቅ አደጋ ምላሽ ላይ ይሠራል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ 28 የተመድ ኤጀንሲዎችና ፕሮግራሞች መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡ በቅርቡም የድርጅቱን 80ኛውን ዓመት አስመልክቶ በአዲስ አባባ ሲከበር የኢትዮጵያ መንግሥት የተመድን ጉዞ የሚዘክር የተለያዩ ቴምብሮችን አሰባስቦ ነበር፡፡

ድርጅቱ ከ80 ዓመታት በፊት ሲመሰረት የሰው ልጅ ከጦርነት ያገኘውን ትምህርት ወደ ተቋማዊ መፍትሔ ለመቀየር ነበር፡፡ ዛሬ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሳይበር ጥቃት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በስደተኞች ቀውስ እና በኃያላን ሀገራት ፉክክር አዲስ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚገጥመው ትልቁ ፈተና ሕልውናውን ማስጠበቅ ሳይሆን ራሱን ማሻሻል ነው፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮችን ለመፍታት የ1945 መዋቅር በቂ ነውን? የሚለው ጥያቄ ዛሬም ክፍት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ መረጃዎቹን ያጋራናችሁ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ)፣ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከካውንስል ኦፍ ፎሬን ሪሌሽን ድረ ገጾች ነው፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሰኔ 22   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here