ሴቶች እና ሕፃናትን እንታደግ

0
73

የወደፊቱ የአንድ ሀገር/ህዝብ ህልውና የሚመሰረተው በተተኪው ትውልድ ላይ እንደመሆኑ መጠን በተሻለ እንክብካቤ ያደገ ትውልድ የተሻለ ሀገርን ለመገንባት ካለው አስተዋጽኦ አኳያ ሕጻናት ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። አንድ የፍሬ ዛፍ በችግኝ ደረጃ ባለበት ጊዜ ተገቢውን እንክብካቤ ካገኘ መልካም ፍሬ ሊያፈራ እንደሚችል ሁሉ ህጻናትም በዚሁ ሊመሰሉ ይችላሉ።

ይሁን እንጅ በተለያዩ ውስብስብ ምክንያቶች የተነሳ በአህጉራችንም ሆነ በኢትዮጵያ በርካታ ህጻናት ለደህንነታቸው አስጊ ለሆኑ አደጋዎች ተጋልጠው ይገኛሉ። እነዚህ  ህፃናትም  በተለያዩ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ተፈጥሯዊ ወይም አካላዊ ምክንያቶች የተነሳ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማግኘት ያልቻሉ እና ለደህንነት እጥረት፣ ለጥቃት፣ ለበሽታ ወይም ለስነ-ልቦና ቀውስ በቀላሉ የተጋለጡ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በርካታ ናቸዉ።

እነዚህ ህፃናት በአካል፣ በስነ-ልቦና እና በማህበራዊ ህይወታቸው ጤናማ ሆነው ለማደግ የሚያስችሏቸው እንደ ምግብ፣ መጠለያ፣ ትምህርት እና የህክምና እንክብካቤ ያሉ መብቶቻቸው ይጓደሉባቸዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕጻናት ጥበቃ እና ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ምላሽ አሰጣጥ ክላስተር ጋር ከሰሞኑ በሕፃናት ጥበቃ እና ፆታን መሰረት ባደረገ ጥቃት ዙሪያ እየሠሩ ባሉ ሥራዎች ዙሪያ ዓመታዊ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

በኢትዮጵያ ሴቶች እና ሕጻናት ማኅበራት ኅብረት የፆታዊ ጥቃት ጥበቃ እና ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ወ/ሮ ሜሮን ዓለማየሁ ኅብረቱ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ውስጥ በመሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት ላይ ጥቃት መድረሱንና አሁንም ድረስ ጥቃቱ እየደረሰ እንደሚገኝ አንስተዉ ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል እና ለጥቃቱ ሰለባዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠትም ሥራወች ተሰርተዋል በማለት  ባለሙያዋ ገልጸዋል።

የሴቶችን ጥቃት መከላከል እና የሕጻናትን ደኅንነት መጠበቅ  የጋራ ኀላፊነት በመሆኑ ሁሉም ተቀናጅቶ በመሥራት ችግሩን መቀነስ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል። ክልሉ አሁንም በግጭት ውስጥ ስላለ ችግሩ ብዙ ነው ያሉት ወ/ሮ ሜሮን የሚደርሰው ችግር ሰፊ በመሆኑ በሲቪል ማህበራት ጥረት ብቻ የሚፈታ ችግር ባለመሆኑ መንግስት፣ ማህበረሰቡ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት በጋራ መረባረብ ይገባቸዋል ፡፡

የኤስ.ኦ.ኤስ የሕጻናት መንደር በኢትዮጵያ የአማራ ክልል ኘሮግራም ዳይሬክተር አቶ መሠረት ግዛቸው ድርጅቱ ሕጻናትን በሁለንተናዊ መልኩ በመደገፍ ፣ በተለይም ወላጅ የሌላቸዉን ሕጻናትን አሳድጎ ለቁም ነገር በማብቃት እየሠራ መሆኑን ገልጸዉ ድርጅቱ ሕጻናትን ከቤተሰቦቻቸው  ሳይለዩ እንዲያድጉ የሚያበረታታው ቢሆንም በተለየ ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተለያዩትን እና ወላጆቻቸዉን በሞት ያጡትን ደግሞ አሳዳጊዎችን በመቅጠር በልጆች ማሳደጊያ ግቢ ውስጥ እንዲያድጉ እና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

ልጆች በተለያየ መንገድ ለችግር እንዳይጋለጡ ቤተሰብ እና ማህበረሰብ በልጆች አወንታዊ አስተዳደግ ዙሪያ ሊደርሱባቸው የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ መከላከል የሚችሉበትን ንቃተ ሕሊና እንዲኖራቸው በማስገንዘብ በኩል መሥራት ያስፈልጋል።

የሕፃናት ጉዳይ የአንድ ድርጅት ወይም የተወሰኑ ቦታዎች ሚና ሊሆን ስለማይገባው የማህበረሰቡን አቅም በመጨመር በኩል የሃይማት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ማህበረሰቡ በትብብር ችግሩን ለመከላከል በጋራ መሥራት ተጋላጭነትን መቀነስ ያስፈልጋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው በበኩላቸዉ ከሰሜኑ ጦርነት ማግስት የሕጻናትን መብት ለማስጠበቅ እና የሴቶችን ጥቃት በመከላከል ዙሪያ የተከናወኑትን ተግባራት በርካታ እንደነበሩ ነው ያነሱት፡፡

ቢሮዉ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀትም በጦርነት እና ግጭቶች ምክንያት የተጎዱ ሕጻናትን ጥበቃ በማድረግ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ የፆታ፣ የሥነ-ልቦና እና ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት በጋራ ሢሠራ መቆየቱን አውስተዉ ከግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ባለፈ በጊዜያዊ እና በቋሚነት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

በክልሉ ከ1 ሚሊዮን በላይ የብዙዎችን ምላሽ የሚሹ ሕጻናት መኖራቸውን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የሲቪክ ማኅረሰብ ድርጅቶች ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሕፃናት እና የፆታዊ ጥቃት ጉዳይ በአንድ ተቋም የሚሠሩ ሥራዎች ባለመሆናቸው በጉዳዩ ዙሪያ ሲሰሩ የነበሩ አካላት በቀጣይም  ሥራቸዉን በማጠናከር መሥራት እንዳለባቸዉ  የችግሩ ሰፊነት ያሳያልና  አስካሁን የተሠራው ሥራ ብቻ በቂ ባለመሆናቸዉ ሌሎች ረጂ ድርጅቶች፣ ሲቪል ተቋማት እና የመንግስት ተቋማት መዋቅርን በመጠቀም ገብተው እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል።

በቀጣይም ጥራት ያለው የጤና እና ሥነ ልቦና አገልግሎት በመሥጠት፣ ጥቃት አድራሽ አካላት ላይ ደግሞ አስተማሪ የሆነ የሕግ እና የተቀላጠፈ እርምጃ መውሰድ፣ማህበረሰቡን ደግሞ በጥቃት ወቅት መረጃ እና ማስረጃ ሆኖ እንዲቀርብ በደንብ በማስተማር በኩል በደንብ እንዲሠራ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል፡፡

የሕግ አንቀፅ

ጾታዊ ጥቃት በኢትዮጵያ እና ዓለምአቀፍ ሕግጋት

 

የወንጀል ጉዳዮችን በተመለከተ በሥራ ላይ ያሉት ዋና ዋና ሕጎች በ1954 ዓ.ም. የታወጀው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዐት እና በ1997 ዓ.ም. የታወጀው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ- አዋጅ ቁ 414/1996 ናቸው::

  • በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃትን የሚመለከቱት የሕግ ድንጋጌዎች በተሻሻለዉ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ ከበፊቱ በተሻሻለ መልኩ ለሴቶች ጥበቃ እንደሚያደርግ አብዛኞቹ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ ሕጉ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካኝነት በህይወት፣ በአካል እና በጤና ላይ ጉዳት በማድረስ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በአንቀጽ (561-570)፣
  • በትዳር ጓደኛ ወይም ከጋብቻ ውጭ በሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት በሚኖር ሰዉ ላይ ጥቃት ማድረስ (564)፣
  • ጠለፋ (587- 589፣
  • አስገድዶ መድፈር (620)፣
  • በንጽኅና ክብር ላይ የሚፈጸም የሃይል ድርጊት 622፣
  • አንድ ሴት ያለባትን ከፍ ያለ ችግር ወይም ጥገኝነቷን ምክንያት በማድረግ የሚፈጠር ድርጊት (655)፣
  • ሴቶች እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ለዝሙት አዳሪነት በማቅረብ መነገድ (695) የሚሉ ዝርዝር አንቀጾችን ያስቀምጣል፡፡
  • በተጨማሪም በሰዉ የመነገድ እና ሰዉን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 እና የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 ጾታዊ ጥቶችን ወንጀል የሚያደርጉ ድንጋጌዎችን ያካተትታሉ፡፡
  • ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በጁን 11 ቀን 1993 ዓ.ም. ያጸደቀችው ዓለምአቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት በተለይ በአንቀጽ 3፣ 14፣ እና 26 ላይ ስለወንዶች እና ሴቶች እኩል የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ተጠቃሚነት፣ በሕግ ፊት እኩልነት፣ ከመገለል ነጻ መሆን፣ እና በጾታ መሰረት ማግለል ሳይፈጻም ሊደረግ ስለሚገባ ስለሕጻናት ልዩ ጥበቃ ይደነግጋል።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here