“ሙቀት” የሚለው ቃል በብዙዎች ዘንድ የተለመደ የአየር ሁኔታ መግለጫ ቢመስልም ከጥር 2018 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንታት ክስተት ግን ከመደበኛ የአየር ጠባይ በላይ የሆነ ዓለም አቀፍ ጉዳይ መሆኑን አሳይቷል፡፡ በአውሮፓ በበርካታ ሀገራት 40 ዲግሪ ሴንት ግሬድ እና ከዚያ በላይ ሙቀት ተመዝግቧል፣ የደን ቃጠሎዎች ተባብሰዋል፣ የጤና ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ በአንዳንድ ሀገራት የውጭ ሥራ ሰዓታት እንኳን ተገድበዋል ወይም ተቀይረዋል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በእስያም ከመደበኛው በላይ የሙቀት መጠን መመዝገቡን የዓለም ሜትሮሎሎጅ ድርጅት (WMO)አስታውቋል፡፡
ሰሞኑን የተከሰተው ሙቀት በአየር ጠባይ ታሪክ ውስጥ ከሚታዩ ተራ ክስተቶች አንዱ እንዳልሆነ ነው ድርጅቱ የገለጸው፡፡ ይህ ሁኔታም የአየር ንብረት ባለሙያዎች “አዲሱ መደበኛ” (New Normal) ብለው የሚጠሩት የአየር ንብረት ለውጥ የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡ በአንድ ወቅት የሚከሰቱ የሙቀት ማዕበሎች አዲስ አይደሉም፤ የተለየው ግን የመከሰቻ ድግግሞሽ፣ የሚቆዩበት ጊዜ እና የሙቀቱ ጥንካሬ እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡
በዓለም ሜትሮሎጅ ድርጅት (WMO) መረጃ መሠረት አውሮፓ በዓለም ላይ ከሁሉም አህጉራት በፍጥነት እየሞቀች ትገኛለች፡፡ ከሰሞኑ የተመዘገበው የሙቀት መጠንም በስፔን፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን፣ በግሪክ እና በፖርቹጋል 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ደርሷል፡፡ በፈረንሳይ እና በጣሊያን ቀን ላይ ከቤት ውጭ ለሚሰሩ ሰዎች ልዩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡ በግሪክ ደግሞ የደን ቃጠሎ ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡ በአጠቃላይ በደቡብ አውሮፓ በሙቀት ሳቢያ የተከሰተው የደን ቃጠሎ ከ20ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከጥቅም ውጭ አድርጓል፡፡
ከሙቀቱ ጀርባ ያለው ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ የተነሳ ሲሆን የአየር ንብረት ሳይንቲስቶች የሚሰጡት መልስ ግን የሙቀት ማዕበሎች በተፈጥሮ ሊከሰቱ ይችላሉ፤ ነገር ግን ዛሬ ያለው የካርቦን ልቀት መጨመር እነዚህን ክስተቶች የበለጠ ከባድ፣ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ እና ተደጋጋሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የከተሞች መስፋፋት፣ የደን ሽፋን መቀነስ እና በኮንክሪትና በአስፋልት የተሸፈኑ አካባቢዎች በከተሞች ሙቀቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆነዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚያስጠነቅቀው ከፍተኛ ሙቀት በዓለም ላይ ከአየር ንብረት ጋር ለተያያዙ ሞቶች ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከፍተኛ ሙቀት በተለይ በሕፃናት፣ በአረጋውያን፣ በነፍሰ ጡሮች እና ሥራቸውን ከቤት ውጭ በሚሰሩ ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ አደጋ ይፈጥራል፡፡
የዓለም የሙቀት ማዕበል የጤና ችግር ብቻ አይደለም እያስከተለ የሚገኘው፤ በዓለም ኢኮኖሚ ላይም በየዓመቱ በቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ኪሳራ እያመጣ ነው፡፡ የሥራ ምርታማነት መቀነስ፣ የግብርና ምርት መውደቅ፣ የጤና ወጪ መጨመር፣ የኃይል ፍላጎት መጨመር እና በመሠረተ ልማት ላይ የሚደርስ ጉዳት ዋና ዋና ተፅእኖዎች ናቸው፡፡ የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) እንዳስታወቀው እ.አ.አ በ2030 በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ በዓለም ዙሪያ ሁለት በመቶ የሚሆነው የሥራ ሰዓት ይባክናል፡፡ ይህም ሁለት ነጥብ አራት ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ የኢኮኖሚ ኪሳራ እንደሚያስከትል ይገመታል፡፡
በተለይ በግብርና፣ ግንባታ፣ ማዕድን እና ከቤት ውጭ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡
በዓለም ባንክ መሠረት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚጨምረው ከፍተኛ ሙቀት የምግብ ምርትን እየቀነሰ በመምጣቱ የምግብ ዋጋ እንዲጨምር እና የድህነት መጠን እንዲባባስ እያደረገ ነው፡፡ በተለይ በአፍሪካ እና በደቡብ እስያ ያሉ ሀገራት ተጽእኖው ከፍተኛ ነው፡፡
የዓለም የሜትሮሎጂ ድርጅት (WMO) እንደሚያስጠነቅቀው የሙቀት ማዕበሎች በየዓመቱ እየተደጋገሙና እየተባባሱ በመምጣታቸው የመንግሥታትን የጤና በጀት፣ የአደጋ ምላሽ ወጪ እና የመሠረተ ልማት ጥገና ወጪ ይጨምራሉ፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ደግሞ ዛሬ ለሙቀት መከላከል የሚወጣ ወጪ ወደፊት የሚደርሰውን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ለመቀነስ እጅግ ጠቃሚ መዋዕለ ንዋይ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የሰሞኑ የሙቀት ዜና በአውሮፓ ላይ ብዙ ትኩረት ቢሰጠውም በአፍሪካ ያለው ሁኔታ በጥልቀት ሲታይ የበለጠ ውስብስብ ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ሙቀት ብቻ ሳይሆን፣ ሙቀቱ ከድርቅ፣ ከውኃ እጥረት፣ ከግብርና ምርታማነት መቀነስ፣ ከረሃብ እና ከሕዝብ መፈናቀል ጋር በመጣመሩ ነው፡፡ የአፍሪካ የአየር ንብረት ሪፖርቶች እንደሚገልጹት አህጉሪቱ በተደጋጋሚ በድርቅ፣ በከባድ ጎርፍ እና የሙቀት ጫናዎች እየተፈተነች ነው፡፡ በተለይ በሳህል ክልል፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በደቡባዊ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ሁኔታው መዛባት ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን የዓለም የሜትሮሎጅ ድርጅት በአፍሪካ የአየር ንብረት ሁኔታ ላይ ያዘጋጃቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡
አፍሪካ ለዓለም የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት (የካርቦን ልቀት) አራት በመቶ ድርሻ ቢኖራትም የሚደርስባት ጉዳት ግን ትልቅ ዋጋ እያስከፈላት ነው፡፡ በአየር ንብረት ጉዳይ ላይ የሚታየው ትልቁ ተቃርኖ ይህ ነው፤ አፍሪካ በአየር ንብረት ቀውስ በጣም ከሚጎዱ አካባቢዎች መካከል ትገኛለች፡፡ ለዚህም ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ በዝናብ ጥገኛ በሆነ ግብርና ላይ መመርኮዙ፤ የውኃ አስተዳደርና የመሠረተ ልማት አቅም ውስን መሆን፤ የጤና እና የአደጋ ምላሽ ሥርዓቶች በአንዳንድ ሀገራት ደካማ መሆን እንዲሁም ድህነት ሰዎችን ለአደጋው የበለጠ እንዲጋለጡ ማድረጉን የአየር ንብረት ለውጥ ኢንተር-መንግሥታዊ ፓነል (IPCC) ያለፈው የስድስት ወራት ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ ለአብነትም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በግልጽ ከሚታይባቸው ሀገራት አንዷ ናት፡፡
በሀገሪቱ በተለያዩ ዓመታት የተከሰቱ ድርቆች፣ የዝናብ መዛባት፣ የጎርፍ አደጋዎች እና የግብርና ጫናዎች የአየር ንብረት ጉዳይ ከአካባቢ ችግር በላይ የልማትና የሰብዓዊ ደኅንነት ጉዳይ መሆኑን አሳይተዋል፡፡
ለአየር ንብረት ቀውስ መፍትሄ ሚሆነው ሙቀትን ብቻ መቀነስ አይደለም፡፡ የሰሞኑ የሙቀት ማዕበል ዓለምን ያስተማረው ትልቁ ትምህርት የአየር ንብረት ጉዳይ የወደፊት ችግር ሳይሆን የዛሬ እውነታ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም መፍትሄው ሁለት አቅጣጫዎችን ይይዛል፦ አንደኛው የአየር ንብረት ለውጥን መቀነስ ወይም (Mitigation) ሲሆን ይህም የሙቀት አማቂ ጋዞችን መቀነስ፣ ንጹህ ኃይልን ማስፋፋት፣ ደኖችን መጠበቅ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መላመድ (Adaptation)ነው፡፡ ይህም የሚከሰቱ የሙቀት፣ የድርቅ፣ የጎርፍ እና የውኃ እጥረት ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም ሕብረተሰቡን ማዘጋጀት ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥትታ ድርጅት የአየር ንብረት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ዓለም እየወሰደች ያለችው እርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት የሙቀት መጨመርን ከ አንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴንቲግሬድ እስከ ሁለት ዲግሪ ሴንትግሬድ እንዳይበልጥ ለመገደብ የተስማሙበትን መተግበር ነው፡፡ ነገር ግን ባለሙያዎች የአሁኑ የልቀት አዝማሚያ ከቀጠለ የተስማሙትን ግቦች ማሳካት እንደሚያስቸግር ያስጠነቅቃሉ፡፡ የታዳሽ ኃይል፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ የደን ጥበቃ እና የካርቦን ቅነሳ ፕሮግራሞች በብዙ ሀገራት ቢስፋፉም የለውጡ ፍጥነት አሁንም በቂ አይደለም ተብሎ ይተቻል፡፡
አፍሪካም የተለየ ሁኔታ ስላላት መፍትሄዎቹም ከአህጉሪቱ ሁኔታ ጋር መጣጣም አለባቸው፡፡
በመሆኑም አፍሪካዊያን የውኃ አስተዳደርን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዝናብ ውኃን ማከማቸት፣ ዘመናዊ የመስኖ ስርዓትን መጠቀም እና የውኃ ብክነትን መቀነስ ለአህጉሪቱ ወሳኝ ናቸው፡፡
የአየር ንብረትን መቋቋም የሚያስችል ግብርናን መከተል፣ ለአርሶ አደሮች ድርቅን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎችን፣ የአፈር ጥበቃ ቴክኒኮችን እና ዘመናዊ የእርሻ ዘዴዎችን መተግበር ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም ከተሞችን አረንጓዴ ማድረግ ሲሆን የከተሞች ሙቀት እንዳይጨምርም ዛፍ መትከል፣ አረንጓዴ ቦታዎችን ማስፋፋት እና ተስማሚ የከተማ ዲዛይን መገንባት ያስፈልጋል፡፡
በዓለም ዙሪያ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የደን መጨፍጨፍ እና የመሬት መራቆት እየተባባሱ በመጡበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም አንስቶ የጀመረችው “አረንጓዴ አሻራ” (Green Legacy Initiative) በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ትኩረት የሳበ የአካባቢ ጥበቃ መርሃ ግብር ሆኗል፡፡ የመርሃ ግብሩ ዋና ዓላማ የደን ሽፋንን መጨመር፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ማልማት፣ የአፈር መሸርሸርን መቀነስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እና የምግብ ዋስትናን ማጠናከር ነው፡፡ ይህም የሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂዋ አካል ነው፡፡
ነገር ግን የወደፊቱ ትልቅ ፈተና የሚሆነው ማላመድ ነው፡፡ ማለትም የሙቀት ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን ማጠናከር፤ የውኃ ሀብትን በተሻለ ማስተዳደር፤ ለአርሶ አደሮች የአየር ንብረት መረጃን ማቅረብ፤ ከተሞቿን ከፍተኛ ሙቀትን እንዲቋቋሙ ማዘጋጀት ይጠበቅባታል፡፡
በአጠቃላይ የሰሞኑ የዓለም ሙቀት መጨመር የአየር ንብረት ቀውስ የሩቅ ጊዜ ስጋት አለመሆኑን ዛሬ ላይ በሰዎች ጤና፣ በግብርና፣ በኢኮኖሚ ላይ የሚታይ እውነታ መሆኑን አሳይቷል፡፡
የወደፊቱ ጥያቄ “ሙቀቱ ስንት ዲግሪ ይደርሳል?” ብቻ አይሆንም፤ “ዓለም ለዚህ ለውጥ ምን ያህል ተዘጋጅታለች?” የሚለው ይሆናል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


