ንባብ የወለደው ደራሲ

0
60

የዚህ ዕትም የበኩር እንግዳችን  ደራሲ ቴዎድሮስ ተፈራ ይባላል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ባዳበረው የንባብ ባህል ሳቢያ ወደ ደራሲነት ተሸጋግሮ  በእንግሊዝኛ ቋንቋ አራት መፃህፍትን ለንባብ አብቅቷል። ስለ ንባብ ባህል መዳከም፣ ስለ ታሪክ አጻጻፍ ግድፈቶች እንዲሁም ስለ ህትመት ኢንዱስትሪው ፈተናዎች ሰፋ ያለ ሀሳብ አጋርቶናል፡፡

መልካም ንባብ!

 

የልጅነት ህይወትህ እና የንባብ ጅማሮህ ምን ይመስል ነበር?

የተወለድኩትና ያደግኩት እዚሁ ባህር ዳር ከተማ ነው። አንደኛ ደረጃን በሰርፀ ድንግል፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በጣና ሀይቅ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ። እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ በጣም ወደ ጨዋታ የሚያደላ ልጅ ነበርኩ። ነገር ግን አባቴ ተፈራ ደምለው ሌላ ቦታ ይሰራ ከነበረበት ወደ ባህርዳር ተዘዋውሮ መምጣቱ ህይወቴን ሙሉ በሙሉ ቀየረው። አባቴ የግብርና ባለሙያ የነበረ ሲሆን አንባቢ ሰው ነበር። እሱን እያየሁ ትኩረቴ ወደ መጻሕፍት ሆነ። አባቴ ለመስክ ስራም ሆነ ቢሮ ሲሄድ ይዞኝ ይሄዳል፤ የሱ ጓደኞችም ቢሆኑ ትርፍ ሰዓታቸውን በመፃሕፍት ንባብ የሚያሳልፉ ነበሩ። በወቅቱ በእኛ ቤት አባቴ ደሞዝ በተቀበለ ቁጥር መጽሐፍ መግዛት የተለመደ ነበር። ከዛም አልፎ በ1987 ዓ.ም አካባቢ “ኒውስ ዊክ”  የተሰኘውን የውጭ መጽሔት እናነብ ነበር። “ኢትዮጵያን ሪቪው”  የሚባለውንና ሌሎችንም የፖለቲካና የመዝናኛ መጽሔቶች አባቴ አዲስ አበባ ሲሄድ ይዞልን ይመጣ ነበር። ስለዚህ የአሁኑ ማንነቴ የተገነባው በአባቴና በቤተሰቤ የንባብ መሰረት ላይ ነው።

 

ንባብን ከትምህርት ጋር እንዴ አጣጣምከው?

በፍጹም ተጽዕኖ አላመጣም፤ እንደውም የደረጃ ተማሪ ነበርኩ። የትምህርት ቤት መፃሕፍትን አጠናለሁ፤ በትርፍ ሰዓቴ ደግሞ ሌሎች መፃሕፍትን አነባለሁ። ታሪክ በጣም እወድ ነበር።

 

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባህ በኋላስ የንባብ ህይወትህ ምን ይመስል ነበር?

አሥራ ሁለተኛ ክፍልን አጠናቅቄ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ያጋጠመኝ የላይብረሪ ሳይንስ ትምህርት ነበር። ይህ ለእኔ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። በወቅቱ የ6 ኪሎው ኬኔዲ ቤተ-መፃሕፍት ለእኔ አዲስ ዓለም ከፈተልኝ። የላይብረሪ ሳይንስ ተማሪ በመሆናችን ወደ ቤተ-መፃሕፍቱ የመግባት ሙሉ መብት ነበረን። እዛም እጅግ በጣም አንባቢ የሆኑ  ተማሪዎችን አገኘሁ። እነሱን ማየቴ የንባብ አድማሴን እንዳሰፋው ረድቶኛል። ከዩኒቨርሲቲ በኋላም ጊብሰን ትምህርት ቤት ስሰራ ማይክል የተባለ የውጭ ዜጋ የምስራቅ አውሮፓ ስነ-ጽሑፎችን አስተዋወቀኝ።

 

ንባብ በህይወትህና ማንነትህ ላይ ምን አይነት ተጨባጭ ለውጥ ፈጥሯል ትላለህ?

ማንበብ ለእኔ እንደገና እንደ መወለድ ነው። አዲስ መጽሐፍ ስትጀምር አዲስ የህይወት ምዕራፍ እንደመጀመር ነው። ንባብ አእምሮን ሰፊ ያደርጋል፤ ከጠባብ አስተሳሰብ ያወጣሃል። ዘር፣ ብሄር ከሚቆጥር እንዲሁም “እኔ ብቻ ነኝ ትክክል” ከሚል አስተሳሰብ ያድንሃል። በንባብ ዓለም ውስጥ ሁልጊዜ ካንተ የሚበልጡ ሰዎች የጻፏቸውን ስራዎች ስለምታገኝ ሁልጊዜ ትሁት ትሆናለህ። ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ የምናየው መዘላለፍና ስድብ ካለማንበብና ካለማወቅ የመነጨ ነው። ቨርጂኒያ ዎልፍ እንዳለችው፣ አንዳንድ ሰዎች የሚያነቡት የራሳቸውን ስህተት (ለምሳሌ ዘረኝነታቸውን) ትክክል ነው ብለው ለማስረገጥ ነው። ትክክለኛው ንባብ ግን የማይመችህንም ሀሳብ መርምሮ መቀበልን ይጠይቃል።

አሁን የሚታየውን የንባብ ክፍተት እና የማህበራዊ ሚዲያ ጫና እንዴት ትገመግመዋለህ?

የቴክኖሎጂ ልዩነት እንዳለ ሆኖ፣ ትልቁ ክፍተት የቤተሰብ ነው። ልጆች አባቶቻቸውም ሆኑ እናቶቻቸው ሲያነቡ አይተው አያድጉም። አባት ከልጁ ጋር መጽሐፍ የማያነብ ከሆነ፣ ልጁ ከየት ያምጣው? በዓለም ላይ ቴክኖሎጂ ያደገባቸው እንደ አሜሪካና ቻይና ያሉ ሀገራት ዜጎች ዛሬም በከፍተኛ ሁኔታ ያነባሉ። አይስላንድ በንባብ ባህሏ ትታወቃለች፤ ኢራንና ኢራቅ በጦርነትና በቦምብ ድምጽ ውስጥ ሆነው በመንገድ ዳር መጽሐፍ ይሸጣሉ። እኛ ሀገር ግን ላይብረሪ ውስጥ ገብተው እንኳን ፌስቡክና ቲክቶክ ነው የሚያዩት። መፃሕፍትን በሞባይል አውርዶ ማንበብ እየተቻለ፣ ወጣቱ ጊዜውን በቁርጥራጭ ነገር ያጠፋል። ይህ የዜጋ ግንባታ ላይ ትልቅ አደጋ አለው።

 

ወደ ጽሑፍ ዓለም እንዴት ገባህ? ምን ምን መፃሕፍትንስ አሳትመሃል?

ወደ ጽሑፍ እንድገባ የገፋፋኝና ያበረታታኝ ስለሺ አምባው የሚባል የቴአትር ደራሲ ጓደኛዬ ነው። እኔ ያነበብኩትን ስነግረው “ለምን አትጽፍም?” ብሎ ገፋፋኝ። ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን አቋርጬ በነበረበት ጊዜ “ዘ ሪፖርተር”  እና “ሞኒተር”  በተባሉ የእንግሊዝኛ ጋዜጦች ላይ መጻፍ ጀመርኩ። በወቅቱ አንባቢው ማህበረሰብ የሚሰጠኝ ግብረ-መልስ አበረታታኝ።

ከዛም ወደ መጽሐፍ ህትመት ገባሁ። የመጀመሪያ መጽሐፌ (ጁርኒ ኦፍ ኤ ፖሽን)  ልብወለድ ሲሆን ያተኮረውም በአብዮቱ ዘመን ፖለቲካ ውስጥ አልገባም ባለችና ስነ-ጽሑፍን በመረጠች አንዲት የትምህርት ሚኒስትር አምባሳደር ልጅ ላይ ነው። ሁለተኛው መጽሐፌ “The Anatomy of ATP and  Other Essays” ይባላል። “ATP” ማለት “Atrophy of Passion” (የፍላጎት መመንመን/መሞት) ብዬ የፈጠርኩት ቃል ነው። ንባብን ትተው ወደ ሌላ ህይወት ስለገቡ ሰዎች እና ስለ ባህርዳር የድሮ ትዝታዎች የሚዳስሱ 11 መጣጥፎችን የያዘ ነው። ሶስተኛው “The Inauthentic Existence” የሚል ሲሆን፣ ሰዎች ከሌላው ጋር ለመመሳሰል ብለው ስለሚኖሩት ሀሰተኛ ህይወት ይተነትናል።

 

እስኪ ስለ አራተኛው  መጻሐፍህ ደግሞ ንገረን?

የመጨረሻውና አሁን በቅርቡ የወጣው ደግሞ የአፄ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የህይወት ታሪክ ነው።

 

ስለ አፄ ኃይለ ስላሴ ለመጻፍ ለምን መረጥክ? በመጽሐፉስ ምን አዲስ እይታ አምጥተሃል?

አፄ ኃይለ ስላሴ ሀገሪቱን ለማዘመን የሰሩት ስራ፣ ትምህርትን ለማስፋፋት ያደረጉት ጥረት፣ ለኤርትራ ጉዳይ ያደረጉት የዲፕሎማሲ ትግል፣ ምህርት ለማስፋፋት፣ የባህር በር ለማስገኘት  ወዘተ. የሠሯቸውን መልካም ሥራዎች እንዲሁም ታሪካዊ ስህተቶችም ይተነትናል። ለምሳሌ እነ አክሊሉ ሀብተወልድ እና ልዑል ራስ አሥራተ ካሳ “እንደ እንግሊዝ ህገ-መንግስታዊ ዘውዳዊ ስርዓት (Constitutional Monarchy) ይፈጠር” ብለው ያቀረቡትን ምክር ባለመስማታቸው ለደርግ መምጣት፣ ለቀይ ሽብር እና አሁን ላለነው የዘር ፖለቲካ ጭምር በር ከፍቷል። ስለዚህ ሚዛኑን የጠበቀ ታሪክ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ።

 

አሁን ባለው የታሪክ አጻጻፍ ዙሪያ ምን ትዝብት አለህ?

አሁን ያለው የታሪክ አጻጻፍ ገደል ይዞ የሚገባ ነው። ጸሐፊዎች ባብዛኛው”              የሚጽፉት አንባቢው ምን ይፈልጋል፣ ገበያው ምን  ትርፍ ያመጣል ብለው እንጂ እውነታውን መርምረው አይደለም። ለአንድ ብሄር አድልተው፣ ሌላውን እያቆሰሉ ይጽፋሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ትህትና የላቸውም። መጽሐፋቸውን ለባለሙያ አያሳዩም። እኔ ግን እድለኛ ነኝ፤ እንደ ዶክተር ተስፋዬ ዳኛው እና ዶክተር ፋንታሁን አየለ ያሉ ምርጥ ባለሙያዎች ስራዎቼን አንብበው፣ በአርትኦት አርመውልኛል። ለምሳሌ ዶክተር ፋንታሁን የአፄ ኃይለ ስላሴን የመጨረሻ ምዕራፍ ስጽፍ፣ ቤተ- መጻሕፍት ገብቶ የ1967 ዓ.ም ጋዜጣ አቧራ አራግፎ በማንበብ፣ ንጉሱ በጤና እክል (በኦፕሬሽን) ማለፋቸውን የሚገልጽ መረጃ ፈልጎ አምጥቶልኛል። እንዲህ አይነት ትህትና እና ጥልቅ ምርምር ዛሬ ባሉ ብዙ ጸሐፊዎች ዘንድ አይታይም።

 

መጽሐፎችህን በሙሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የጻፍከው፤ ይህ ለምን ሆነ?

ሁሌ “ፈረንጆች ስለ እኛ ታሪክ ጻፉ” ብለን እናማርራለን። ታዲያ እኛ ለምን በዓለም አቀፍ ቋንቋ (በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ) ስለራሳችን አንጽፍም? ስለ ባህርዳር፣ ስለ አብዮቱ፣ ስለ ኃይለ ስላሴ የደጅ ጥናት ወዘተ. ከእኛ በላይ ፈረንጅ ሊያውቅ አይችልም። ስለዚህ የእኛን እውነተኛ ገጽታና ታሪክ ለዓለም ለማሳወቅ እኛው ራሳችን ጽፈን ማሳየት አለብን በሚል እምነት ነው።

 

የህትመት ገበያውና ኢንዱስትሪውስ ምን ይመስላል?

እጅግ በጣም ፈታኝና ተስፋ አስቆራጭ ነው። በሶስተኛውና በአራተኛው መጽሐፌ መካከል ባለው የ4 ዓመት ልዩነት የህትመት ዋጋ ከአምስት እጥፍ በላይ አድጓል። ከዚህ ላይ የአርትኦት፣ የግራፊክስ፣ የምረቃ እና ሌሎች ወጪዎች ሲታከሉበት ሙሉ በሙሉ ኪሳራ  ነው። የባህል ተቋማትም ሆኑ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት መጻሕፍትን አይገዙም። በዚህ ከቀጠለ በወረቀት ማሳተም ስለማይቻል ሙሉ በሙሉ ወደ “አማዞን”  ማምራታችን አይቀርም።

 

በመጨረሻም ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ወይም ምስጋና ካለህ?

በመጀመሪያ ስራዎቼን በማረም፣ በማማከርና ታሪክን በማካፈል ትልቅ ውለታ ለዋሉልኝ ለዶክተር ተስፋዬ ዳኛው፣ ለዶክተር ፋንታሁን አየለ እና ለስለሺ አምባው ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ። እንዲሁም የኔን ሸክም ተጋርታ ከጎኔ ለቆመችው እህቴና ቤተሰቤ ምስጋናዬ ይድረስ። በመጨረሻም ለወላጆች አደራ የምለው እባካችሁ ልጆቻችሁ   ከማሕበራዊ ሚዲያ ወጥተው የንባብ ባህል እንዲያዳብሩ እናንተ ራሳችሁ አንብባችሁ አርአያ ሁኗቸው! በማንበብና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትውልድ ካልገነባን ሀገር መገንባት አንችልም!

 

ለነበረን ቆይታ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን!

እኔም በጣም አመሰግናለሁ!

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here