ከማለዳው 12 ሰዓት በባሕር ዳር ከተማ ዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ከልደታ ቤተክርስቲያን ጀርባ ካለው ዋናው አስፋልት ላይ ተገኝተናል፤ በቦታው ስንደርስ ወጣት ሕይወት ብርሐንን እና የስፖርት ትጥቅ የለበሱ ሌሎች በርካታ ሰዎችን ተመለከትን፡፡ የመኪና እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት በኤሮቢክስ ስፓርት አካላቸውን ለማፍታታት እና ከበሽታ ለመጠበቅ የተገኙት 100 የሚጠጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ዕድሜ እና ጾታ ሳይገድባቸው ለስፖርት ሰውነታቸውን ማሟሟቅ ጀመሩ፡፡
በወጣትነት የእድሜ ክልል የምትገኘው አሰልጣኝ ሕይወት ብርሐን የአካል ብቃት የሚሠሩትን ሰዎች እየተዟዟረች ታበረታታለች፤ ሴት፣ሽማግሌ፣ጎልማሳ ….. እንደየ እድሜ ክልሉ እና አቅሙ ታሠራለች፡፡ ሥራው ከገቢው ባለፈ በአካል እና በጤና የሚያመጣውን ለውጥ በየጊዜው መመልከቷ የበለጠ እንድትተጋ አድርጓታል፡፡ በሳምንት ለሦሰት ቀን ስታድየም ሦስት ቀናት ደግሞ ሰፈር ውስጥ በመገኘት ታሰለጥናለች፡፡
እኛም የዕለቱ መርሐ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኟን እና ሰልጣኞችን አነጋግረናል፡፡ ቀጠሮ ይዘን ስለነበር ያስቀደምነው ወጣት ሕይወትን ነው፡፡ ወደ አሰልጣኝነት እንዴት ገባሽ? የሚለው ቀዳሚ ጥያቄያችን ነው፡፡ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ የተወለደችው ሕይወት እድገቷ ባሕር ዳር ከተማ ነው፡፡ ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ከፍተኛ የስፓርት ዝንባሌ አላት፡፡ ይሁን እንጂ አስፈላጊውን እገዛ ባለማግኘቷ የጥረቷን ያህል እንዳልተሳካላት ነው የምትገልፀው፤ “ስፓርት በባህሪው የሰዎችን እገዛ እና ትጋት የሚፈልግ ዘርፍ ነው፡፡ የፈለግሁት ደረጃ መድረስ ያልቻልኩት የሚፈለገውን ያህል የደገፈኝ አካል ባለመኖሩ ነው” በማለት ትቆጫለች፡፡
ሕይወት በስፖርት የመሳተፉ ፍላጎት ባይሳካላትም ቤት ተከራይታ እየሠራች እና ራሷን እየደገፈች ትምህርቷን አላቋረጠችም፡፡ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ /ኮበል ስቶን/ ሠርታ ባጠራቀመችው 60 ሺህ ብር በፈሳሽ ሳሙና ሥራ ተሰማርታ እንደ ነበርም ታስታውሳለች፡፡
በ2007 ዓ.ም ግን አማን ከሚባል የግል ብስክሌት አሠልጣኝ በመሰልጠን ብስክሌት መወዳደር ጀመረች፤ የብስክሌት ስፓርት እገባበታለሁ ብላ የምታስበው ዘርፍ ባይሆንም በወቅቱ አብዛኛው እንቅስቃሴዋ በብስክሌት ስለነበር ስፓርቱ ላይ ጥሩ ተሳትፎ ነበራት፡፡ ወጣቷ በ2009 ዓ.ም በክልላዊ የብስክሌት ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆነች፡፡ ውድድሩ ግን እንዳሰበችው ሳይሆን ቀርቶ በከፍተኛ ፍጥነት ስትታጠፍ በደረሰባት የመውደቅ አደጋ አገጯ ሥር አደጋ ደረሰባት፡፡ ጉዳቱ የከፋ በመሆኑም ሁለት ጊዜ ቀዶ ጥገና ተሠርቶላታል፡፡
በወቅቱ ውድድሩ ሁለት ዙር ቀርቶት እንደ ነበረ የምታነሳው ሕይወት፤ እሷ ግን በደረሰባት አደጋ ውድድሩንም ማጠናቀቅ ሳትችል ቀረች፡፡ በስፓርት መውደቅ አንዱ ፈተና ቢሆንም ቤተሰብ በጣም ድንጋጤ ተሰምቷቸው ስለነበር ደግማ ወደ ብስክሌት ስፓርት እንዳትገባ ከለከሏት፡፡ አሰልጣኟ ቤት ተመላልሶ ቢጠይቅም በቤተሰብ አንቢተኝነት ከስፓርቱ ተገለለች፡፡
“ከልጅነቴ ጀምሮ ሩጫ ተወዳዳሪዎች አሸንፈው ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቅሉ ሳይ አብሬ አለቅስ ነበር” የምትለው ሕይወት ስፓርቱን ጨርሶ ለመተው ፍላጎት ስላልነበራት ከብስክሌቱ ስትደናቀፍ ፊቷን ወደ ሩጫው አዞረች፡፡ በወቅቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አትሌቲክስ ክለብ ተቋቁሞ ስለነበር የነበራት ብቃት ተመዝኖ በ400 ሜትር የሩጫ ውድድር መሳተፍ ጀመረች፡፡ ለሩጫ ሊደግፍ የሚችል ቤተሰብ እና ተቋም ሊኖር ቢገባም በሷ በኩል ግን ቤተሰብ ብዙም ደስተኛ እንዳልነበሩ ታነሳለች፡፡
ትምህርቷን ጎን ለጎን እየተማረች ለአራት ዓመታት በክለቡ ብትሮጥም ክለቡ በበጀት እጥረት ምክንያት ፈረሰ፡፡ የሕይወት ሯጭ የመሆን ዓላማዋም ተደናቀፈ፡፡
ሕይወት ለመማር እና ኑሮዋን ለመደጎም የጀመረችውን ሳሙና የማምረት ተግባር ቀጥላ ወደ ወረዳዎች እየላከች ለመሸጥ ብትሞክርም በሰሜኑ ጦርነት ተስተጓጎለባት፡፡
በወቅቱ የተሻለ ኑሮ ለማግኘት ውጭ ሀገር ሂዶ መሥራት ይገባል የሚል ሃሳብ ስለነበራት የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ጆርዳን ለመሄድ ወሰነች፡፡ ሆኖም ከቤተሰቦቿ ”መሥራት ከተቻለ ሀገር ውስጥም ሠርቶ መለወጥ ይቻላል” የሚለው ሃሳብ በተዳጋጋሚ ቢነገራትም፤ ለሕይወት ግን የሚዋጥ አልነበረም፡፡
ሕይወት የቤተሰቦቿን ምክር በመተው ሕልሟን እውን ለማድረግ የተሻለ ነገር አገኝበታለሁ ብላ ወደ መረጠችው ስደት አቀናች፡፡ መዳረሻዋም ጆርዳን ሆነች፡፡ ይሁን እንጅ ከሀገር ወጥቶ መሥራት እንደጠበቀችው ቀላል እና አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡ የአየሩ ፀባይ ከኢትዮጵያ በጣም የተለየ እና ሞቃታማ በመሆኑ ለህመም ዳረጋት ፤ በመጨረሻም ካወጣችው እጥፍ ገንዘብ ከፍላ ወደ ሀገርዋ ለመመለስ ተገደደች፡፡
ቤተሰቦቿ በመመለሷ ደስተኛ ሁነው የፈለገችውን ህልም ሁሉ ሀገርዋ ላይ ሠርታ እንድታሳካ መከሯት፡፡ወደ ሀገሯ ከተመለሰች በኋላ በስፓርት ማዘውተሪያ ስፍራ ጊዜዋን ታሳልፋለች፡፡ የሕይወትን የስፖርት ፍቅር የተገነዘቡት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፓርት አካዳሚ መምህር የነበሩት አቶ ፋሲል አስማረ በሳምንት ስድስት ቀናት ሁለት ቦታ ስፓርት ያሠሩ ነበር፡፡ ኋላም ወጣቷን በረዳትነት አብራ እንድታሠራ ፈቀዱላት፡፡
የኤሮቢክስ ስፓርት በተለያየ ምክንያት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመቀነስ ወይም ለመከላከል የሚፈልጉ ሰዎች የሚሠሩት መሆኑን የምታነሳው ሕይወት፤ በዕድሜ ትልቅ ሆነውም በእንቅስቃሴ አለመኖር ሰውነታቸው የተሳሰሩ ሰዎች በቀላሉ ወደ ጥሩ አቋም መመለስ የሚችሉበት እንደሆነ በመመልከት በከፍተኛ ፍቅር እንደምትሠራም ገልፃለች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በፊት ዋና አሰልጣኟ እና ወደዚህ ሥራ ያስገቧት አቶ ፋሲል ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ እሷ ተተክታ ማሰልጠን ቀጠለች፡፡
ሕይዎት አሁን ህልሟ እውን ሆኖ ከምትመኘው ስፖርት ጋር ተገናኝታለች፡፡ ወደ ፊት የራሷ ጂም ቤት እስትከፍት ድረስ ጥረቷን አጠናክራ የምትሠራበት የስፓርት መሥክ እንደሚሆን ነው የምትገልፀው፡፡
አረጋዊያን፣ ጎልማሶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች ካለባቸው የጤና ችግር ለመላቀቅ ወይም ለመከላከል ፍላጎት ኑሯቸው ስለሚመጡ በሰዓቱ ተገኝታ ታሠራለች፡፡ ከስልጠናው ቦታ መምጣት ለማይችሉት ደግሞ በቤታቸው ሆነው መሥራት የሚገባቸውን የስፓርት ዓይነት በራሷ ስልክ በመቅረፅ በቴሌግራም በመላክ እንዲሁም ቤት ለቤት ባላት ትርፍ ጊዜ ሄዳ በነፃም ቢሆን በማሠራት በምታየው ለውጥ እንደምትደሠት ነው የምትገልፀው፡፡
ብዙ ሰዎች በጠዋት መነሳት እንኳን ቢከብዳቸውም አንዴ ከጀመሩት ደግሞ እየወደዱ የሚሠሩት ተግባር እንደሆነ ሕይወት ከልምዷ ተገንዝባለች፡፡ በሥራው የምታገኘው ገቢ ራሷን ከማገዝ ባለፈ በፊት ወደዚህ ሥራ እንድትገባ የረዷትን የአቶ ፋሲልን ልጆች ታግዛለች፡፡
ከዕድሜዋ አንፃር ያሳለፈችው ፈተና ብዙ እንደሆነ የምትገልፀው ሕይወት፤ በቀጣይ ደግሞ በየመንገዱ ከመሥራት ይልቅ የራሷ የስፓርት መሥሪያ ጅምናዝየም ከፍታ ማህበረሰቡን የማገልገል ዓላማ አላት፡፡ አሱንም ለመፈፀም እና ያቋረጠችውን ትምህርት ለመቀጠል በማሰብ በትጋት እንደምትሠራም ነው የገለፀችልን፡፡
በስልጠና ቦታው ካገኘናቸው አንዱ የሕይወት ሰልጣኝ አቶ ማሩ መሀመድ ግፊት እና ስኳር የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ወደ ስልጠናው እንደገቡ ነው የተናገሩት፡፡ ሕይወትም በየቀኑ የምትሻሻል ጎበዝ እና ጠንካራ አሠልጣኝ መሆኗን አንስተው በስልጠናው በየቀኑ ለውጥ ለማየት በመቻላቸው ደስተኛ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ሌሎቸች ሴት አሰልጣኞች እንደዚህ ዓይነት ሥራ የመሥራት ፍላጎት ካላቸው እሷን በአርዓያነት በማየት ወደ ፊት እንዲመጡ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
አቶ ብስራት አያና በበኩላቸው በብዛት ስፓርት የምታሠራቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ነው ፤ ስፓርት በባህሪው ትህትና መላበሥ ስለሆነ እንደየ እድሜ እና ባህሪው ችላ አገልግሎት እየሠጠች በመሆኑ ምስጉን እንደሆነች ያነሳሉ፡፡ ”ምንም እንኳን ቦታው ምቹ ባይሆነም ከ100 በላይ አባላትን፣ ማንም ሴት ያልደፈረወን ሥራ ስትሠራ ስታሠራም ምርኩዝ ይዘው የመጡትን ሰዎች ሁሉ በጥሩ አቋም እንዲሄዱ ስታስችል በመመልከት እኛ እያበረታታናት ነው፤ ሰውም ሊያበረታታት ይገባል” ብለዋል፡፡
አቶ ካሳው ይርዳው በበኩላቸው ከፍተኛ የኮሌስትሮል ችግር ነበረባቸው፡፡ ወደ ስፓርቱ ሲገቡ ግን የጤና ችግራቸው ተስተካክሎ ጤናቸው ተመልሷል፤ሕይወትም ጎበዝ እና ታታሪ ሆና የስፓርት ፍላጎት ተሠምቶት ሁሉም እንዲሠራ ስለምታደረግ ልትመሰገን ይገባል ነው ያሉት፡፡
አባባል
” አንተ ጠንክረህ በዝምታ ስትሠራ ፣ ስኬትህ ጮኾ ይናገራል” -ፍራንክ ኦሽን
” በሕይወትህ ከዚህ በፊት ያልነበረህ አዲስ ነገር ለማግኘት ከፈለክ፣ አዲስ ሠርተኸው የማታውቀው ሥራ ለመሥራት መፍቀድ ይኖርብሀል” -ቶማስ ጄፈርሰን
” አንተን ሁለት ነገሮች ይገልፁሀል ፡፡ የመጀመሪያው ምንም የሌለህ ጊዜ የምታሳየው ትዕግስት ሲሆን ሁለተኛው ሁሉም ሲሟላልህ የምታሳየው ጠባይ ነው” -ኢማም አሊ
” በምድር ላይ ትልቁ አስደሳች ነገር ሰዎች አትችልም ያሉህን ሰርተህ ማሳየትህ ነው” -ዋልተር ባግሆት
” ህልምህን ለመፈፀም ብዙ ጊዜ በመውሰዱ ተስፋ አትቁረጥ ምክንያቱም ጊዜ ስለሚበር አርቀህ ያየኸው ህልም በፍጥነት መፈፀሙ አይቀርም” -አርል ኒተንጋል
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


