የስምንት ዓመቱ ባለ ” ዲግሪ”

0
453

ገና በልጅነቱ በቤት ውስጥ አይነካካው፣ አይዘውና አይጨብጠው ነገር አልነበረም። የተረጋጋ ወይም የሰከነ ነገር የለውም፤ አንዱን ማንሳት፣ ሌላውን መጣል፣ መስበርና መረበሽ የተለመደ ተግባሩ ነበር።

ወላጅ እናቱ በልጇ ያልሰከነ እና ያልተረጋጋ ባህርይ ግራ መጋባቷ ሲበረታ ገና በአራት ዓመት ዕድሜው በአካባቢው ወደ ሚገኝ ” ፀግሽ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል” በመውሰድ ስፖርት እንዲጀምር አድርገውታል። በዚህ የቴኳንዶ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልም ለአራት ተከታታይ ዓመታት ሠርቷል፤ አሁንም እየሠራ ይገኛል።

“በልጅነቴ በጣም እረብሽ፣ አስቸግር ነበር። ብርጭቆዎችን እንክትክት እያደረኩ፣ የቤታችንን ዲኮደርና ቴሌቭዥን እየሰበርኩ ስበጠብጥ እናቴ ቴኳንዶ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል አስገባችኝ”  ይላል፤ ህፃን  አብሳሎ አማኑ።

“ዛሬ ላይ የቴኳንዶ ስፖርት በመሥራቴ ደስተኛ ነኝ” የሚለው ህፃን አብሳሎ አማኑ “የቴኳንዶ ስፖርት መሥራት ጤናን ይጠብቃል፤ ጥንካሬን ይሰጣል፤ የአዕምሮ እድገትን ይለግሳል፤ ከዚህም ባሻገር የተሻለ ሥነ ምግባርን ለመላበስ የሚጠቅም ነው” በማለት ይናገራል።

“እኔም ዛሬ ባህሪዬ ተስተካክሎ በትምህርቴም ጎበዝ ሁኛለሁ፤ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ስሆን ከክፍሌም ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ወደ ሦሥተኛ ክፍል ተሸጋግሬያለሁ። በትምህርቴ ጎበዝ በመኾኔ አስተማሪዎቼም እናቴም የሚወዱኝ  ተማሪ ሆኛለሁ። ለዚህ የረዳኝ ደግሞ የቴኳንዶ ስፖርት እንደሆነም ተረድቻለሁ” በማለትም በህፃን አንደበቱ ይገልፃል፤  አብሳሎ።

” ጎበዝ  እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት አለኝ ” የሚለው ህፃን አብሳሎ ለዚህ ውጥኑ ደግሞ የጀመረው የቴኳንዶ ስፖርት እንደሚያግዘው ያምናል። ብርቱ ስፖርተኛ ሆኖም ወላጅ እናቱንና አባቱን ከመርዳት አልፎ የጎዳና ልጆችን የማገዝም ውጥን እንዳለው ይናገራል።

በአራት ዓመቱ ገና ባልጠና ጉልበቱ እና ባልተገራ የልጅነት ዕድሜው  የቴኳንዶ ስፖርትን የጀመረው ህፃን አብሳሎ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ቴኳንዶ ስፖርት ሠርቷል፤ አሁንም በመሥራት ላይ ነው።

ህፃን አብሳሎ ገና በልጅነቱ  የቢጫ፣ የአረንጓዴ፤ የሰማያዊ እና የቀይ ቀበቶዎች ባለቤት ሆኖ ቆይቷል። ባሳለፍነው ሰኔ ወር 2018ዓ.ም ከአዲስ አበባ በመጡ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌደሬሽን  በባሕር ዳር ከተማ የቴካንዶ ስፖርት ውድድር እና ፈተና አካሂዷል። በዚህ ፈተናም ከፀጋዬ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል የተገኘው ህፃን አብሳሎ አማኑ ፈተናውን በአንደኝነት በመጨረስ በዘርፉ የመጀመሪያ “ድግሪውን” ( ፈርስት ዳን) አግኝቷል። “ፈርስት ዳን “በቴኳንዶ ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪ መኾኑን ልብ ይሏል።

ይህም አኩሪ  ውጤት ህፃን አብሳሎ አማኑን በኢትዮጵያ በስምንት ዓመቱ የመጀመሪያ  ዲግሪ  ያገኘ ህፃን የቴኳንዶ ስፖርተኛ ያደርገዋል።

 

የህፃን አብሳሎ አማኑ የቴኳንዶ ስፖርት አሰልጣኝ  ሳቮም ጸጋዬ አንለይ ” ህፃን አብሳሎን ወላጆቹ ገና በአራት ዓመቱ ጠዋት እና ማታ እያመጡ እንዲሰለጥን ሲጀምሩ የሚፀና እና ስልጠናውን የሚቀጥል አልመሰለኝም ነበር።  በስምንት ዓመቱ የመጀመሪያ ድግሪ ያገኛል ብዬ  ብዙም አልገመትሁም  ነበር። በህፃኑ ላይ ግን ራዕይ ሰንቄ ሳግዘው ቆይቻለሁ” ሲል ያስታውሳል።

ነገር ግን ህፃን አብሳሎም ሆነ ቤተሰቦቹ ፅናትን የተላበሱ ነበሩና ህፃኑ የቴኳንዶ ስፖርት ለአራት ዓመታት በፅናት መሥራቱን ይገልፃል። በቅርቡ በባሕር ዳር ከተማ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ቴኮንዶ  ባዘጋጀው ውድድርና በሰጠው ፈተና አንደኛ በመውጣት በሀገራችን በስምንት ዓመት ዕድሜ የመጀመሪያ ድግሪ ባለቤት በመሆን የመጀመሪያው ሠልጣኝ መሆን ሲችል በጣም እንደተገረመና እንደተደሰተ ይናገራል። ይህ ህፃን ያገኘው ውጤት ዓለማቀፍ እውቅና ያለውና ተቀባይነቱም የተረጋገጠ እንደሆነም ያብራራል፤ አሰልጣኙ።

ከአሥራ ስድስት እስከ 35 ዓመት ዕድሜ ካላቸው ወጣቶችና ጎልማሶች ጋር ተፈትኖ አንደኛ በመውጣት በስምንት ዓመት ዕድሜ (በህፃንነት) የመጀመሪያ ዲግሪ ማግኘት በሀገራችን አዲስ ታሪክ እንደሆነም ይገልፃል፤ አሰልጣኙ።

ህፃን አብሳሎ ያስመዘገው አዲስ ታሪክ እና ስኬት ሌሎች ህፃናት እና ታዳጊዎች  ወደ ቴኳንዶ ስፖርት እንዲመጡ ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሆነም የህፃኑ አሳልጣን ጸጋዬ ይገልፃል።

ፈተናው የጥበብ፣ የፍልሚያ፣ ራስን የመከላከል፣ የቴክኒክ፣ የትንፋሽና የአዕምሮን ብቃት የተመለከተ እንደነበረ የሚገልፀው አሠልጣኝ ሳቮም ጸጋዬ ገና በልጅነት ዕድሜው ከታላላቆች በልጦ የመጀመሪያ ድግሪ በስምንት ዓመት ያገኘው አብሳሎ ነገ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ሀገሩን እንደሚያስጠራም ያለውን እምነት ይገልፃል።

አሠልጣኙ በቀጣይም እንደ አብሳሎም ያሉ ተስፋ የሚጣልባቸውን ስፖርተኞች ለማፍራት በክልሉ ያለውን የቴኳንዶ ስፖርት ማገዝ ፣መደገፍ እና መከታተል እንደሚገባም ይጠቁማል።

የአማራ ክልል ኢንተርናሽናል የቴኳንዶ አሶሴሽን  ጽ/ቤት ኃላፊ አማን ሞላ “ህፃናት የቴኳንዶ ስፖርትን በልጅነታቸው የሚጀምሩት ቢሆንም በስምንት ዓመት ለመጀመሪያ ዲግሪ (ፈርስት ዳን) ፈተና የቀረበ ግን ከህፃን አብሳሎ ሌላ አላውቅም” ብለዋል።

አሠልጣኙ በበኩሉ “ከኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል  ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ወደ ባሕርዳር ከተማ መጥተው ፈተና እንዲሰጡ እያደረግን ብዙ ጊዜ አስፈትነናል። በቅርቡ በተሰጠው ፈተና  ውጤት ግን የስምንት ዓመቱ ህፃን  አብሳሎ አማን ፈተናውን በብቃት አልፎ የመጀመሪያ  ዲግሪ (first Dan) ማግኘቱ ለክልሉም ኾነ ለሀገራችን በዘርፉ አዲስ ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው” ሲል ይገልፃል።

የህፃን አብሳሎ አመርቂ ውጤት በክልሉ ያለው የቴኳንዶ ስፖርት እያደገ መምጣቱን የሚያመላክት እንደሆነ የገለፁት የጽ/ቤት ኃላፊው  በቀጣይ ለበርካታ  ታዳጊዎችም ትልቅ ስንቅ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

“ስፖርት ዕድሜ የማይወስነው ቢሆንም  የበቃ አሠልጣኝ ይፈልጋል፤ የስፖርተኞችን ቁርጠኝነትም ይጠይቃል። ህፃን አብሳሎ በዚህ ዕድሜው ብዙ ውስብስብ ሥራዎችን በብቃት ሠርቶ በሀገራችን ትንሹ በቴኳንድ ስፖርት የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኘ፣ ለክልላችንም ለሀገራችንም ኩራት ለመሆን የቻለ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ፤ የጽ/ቤት ኃላፊው ።

“በአማራ ክልል ያለውን የቴኳንዶ ስፖርት ከዚህ በላይ ለማሳደግ  ውድድሮችን በየጊዜው ማካሄድ እና ለስፖርቱ ምቹ የሆኑ የማዝውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት በቀጣይ የሚጠበቅ ነው” በማለት አቶ አማን ይገልፃሉ።

በኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የቴክኒክ አማካሪና ምክትል ፕሬዝደንት  ሳቮም ዮሴፍ ገለታ በቅርቡ በባሕር ዳር ከተማ የዳን ፈተና እና  የክህሎት ማሻሻያ ሥልጠና መስጠታቸውንና በዚያ ፈተናም ህፃን አብሳሎም የማይታመን አስደናቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀዋል።

“እኔ በቴኳንዶ ስፖርት በቆየሁባቸው በርካታ ዓመታት በስምንት ዓመቱ የመጀመሪያ ድግሪ (ፈርስት ዳን) ያገኘ ከህፃን አብሳሎም ውጭ አላውቅም” ሲሉም ገልፀዋል፤  ምክትል ፕሬዝዳንቱ።

ፈተናው  ከንድፈ ሀሳብ በተጨማሪ ራስን መከላከል፣ የፍልሚያ ቴክኒክ፣ ኃይል አወጣጥና ሌሎች ክህሎቶችን ያካተተ እንደነበረ የገለፁት ምክትል ፕሬዝደንቱ     ከተፈተኑት ከ70 በላይ ሠልጣኞች መካከል ህፃን አብሳሎም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ገና በስምንት ዓመቱ የመጀመሪያ ድግሪ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

በክልሉ  በዘርፉ እምቅ ችሎታ ያላቸው በርካታ ታዳጊዎች ስለመኖራቸው የህፃን አብሳሎ ውጤት ህያው ምስክር ነው። በመኾኑም ባለድርሻ አካላት  ለታዳጊዎች ሥልጠናዎችን መስጠት ይቻል ዘንድ የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

(ግርማ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ  20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here