በቻይና ጉያንግ ከተማ በቋሚ ምሰሶዎች ላይ በተሰራው የሹኩሲ ድልድይ ከስሩ በርካታ ህንፃዎች ተገንብተው ልዩ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሰሞኑ አስነብቧል፡፡
ግንባታው በ1997 እ.አ.አ የተጠናቀቀው የሹኩሲ ድልድይ “ኦቨርፓስ” ያልተለመደ የመኖሪያ ፕሮጀክት መገንቢያ ማእከል ሊሆን ችሏል፡፡ በወቅቱ የጉያንግ ከተማ አስተደደር አካላት ለመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች የግንባታ ቦታ ለመስጠት እጥረት ስላጋጠማቸው በመፍትሄነት የድልድዩን ስር ክፍት ቦታ ለመኖሪያ ህንፃ ግንባታ ለማዋል ይወሰናሉ፡፡ ባለስልጣናት በድልድዩ ስር የሚገነቡት የመኖሪያ ህንፃዎች በትራፊክ መጨናነቅ በሚፈጠር የድምፅ ብክለት እና ንዝረት ተጠቂ ሊሆኑ እንደሚችሉም ግንዛቤው ነበራቸው፡፡ ሆኖም ከግንባታ ቦታ እጥረቱ እንደማይብስ አምነው በውሳኔያቸው ይገፉበታል፡፡ ድልድዩ ተገንብቶ ካላቀ ከሁለት ዓመት በኋላ 10 የመኖሪያ ህንፃዎች በዝቅተኛ ኪራይ ቤትነት እና በመልሶ ማስፈር መሰራታቸው ተጠቁሟል፡፡ እንደተጠበቀውም በትራፊክ መጨናነቅ እና ንዝረት ከፊሎቹ መቸገራቸውን አንስተው ሲያመለክቱ ቀሪዎቹ ከነበረባቸው የቤት እጦት እንደማይብስ በመገንዘብ ተላምደው ኑሯቸውን መቀጠላቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
የቀጣናው አስተዳደር አካላት የኗሪዎቹን ችግር በመገንዘብ በመፍትሄነት ድልድዩን ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዳይጠቀሙበት አግደዋል፡፡ በዚህም የነበረውን የድምፅ ብክለት እና ንዝረት በተወሰነ ደረጃ መቀነሱን አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም ከአራት ሚሊዬን በላይ ኗሪዎች ባሏት ጉያንግ ከተማ ለተከሰተው የመኖሪያ ቦታ እጥረት አስተዳደሩ በመፍትሄነት የወሰደው ፈጠራ የታከለበት ውሳኔ እና ተግባራዊ አፈፃፀሙ አስተማሪነቱ የጐላ መሆኑ በማደማደሚያነት ሰፍሯል- በድረ ገጹ፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


