ፓርኩ በአሜሪካ የሚገኝ ሲሆን የተመሰረተው በመጋቢት 1/1872 እ.አ.አ ነው፡፡ በዓለም በምስረታ ጊዜው የመጀመሪያም ነው፡፡ አጠቃላይ ስፋቱም 899,116 ሄክታር ወይም 8991 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡ የፓርኩ መገኛ 96% በዎሚንግ፣ 3% በሞንታና እና 1% በኢዳሆ ክልል ውስጥ ነው፡፡
የፓርኩ ከፍተኛ ቦታ 3462 ሜትር ፣ዝቅተኛው 1610 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ተለክቷል፡፡ ፓርኩ 5 በመቶ በውኃ፣15 በመቶ ሳር ለበስ 80 በመቶው ደግሞ በደን የተሸፈነ ነው፡፡ ዓመታዊ የዝናብ መጠኑ በሰሜን ቀጣና 26 ሴንት ሜትር፣ በደቡብ ምእራብ 20 ሴንቲ ሜትር ተለክቷል፡፡ የሙቀት መጠኑ ከፍተኛው 37 ዲግሪ ሴልሽየስ እንዲሁም ዝቅተኛው ኔጌቲቭ 54 ዲግሪ ሴልሽየስ ተመዝግቧል፡፡
በፓርኩ ከ200 በላይ ፏፏቴዎች፣ ሐይቆች፣ ኩሬዎች፣ ሸለቆዎች… ሲገኙ የሎውስቶን ወንዝ የታችኛው ፏፏቴ ከዱር እንስሳት 67 የአጥቢ እና 285 የዓእዋፍ ዝርያዎች መኖራቸው ተመዝቧል፡፡
ከቀጣናው ዝርያዎች የ“ካናዳ ላይናክስ እና ግሪዝሊ ቢር” ለመጥፋት ከተጋለጡት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእፅዋት ዘጠኝ የጥድ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን መጠናቸውም 80 በመቶውን ይሽፍናል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአበባ ዝርያዎች መገኘታቸውም ተሰንዶ ይገኛል፡፡
ወደ ፓርኩ ለማምራት በተሽከርካሪ ዓመቱን ሙሉ የተመቸ ነው፡፡ ለጉብኝት የደቡብ እና ምሥራቅ መግቢያዎች ከግንቦት እስከ ኅዳር ክፍት ናቸው፡፡ የሰሜን ምሥራቅ ቀጣናው ዓመቱን ሙሉ ጐብኚዎችን ያስተናግዳል፡፡
የፓርኩ የበላይ ተቆጣጣሪ አካልም የአሜሪካ ብሔራዊ የፓርክ አገልግሎት ነው፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት የሎውስቶን ናሽናል ፓርክ ዶት ኦርግ፣ ቢዩቲፉል ወርልድ ድረ ገጽ፣ የሎውስቶንና ናሽናል ፓርክ ሎጂ ድረ ገጹን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


