“ትምህርት ንግድ ሳይሆን የትውልድ ግንባታ ነው!”

0
187

ምቹ  የመማሪያ ክፍሎች፣ የመጫዎቻ ሥፍራዎች፣ ቤተ መጻሕፍት እና የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች የትምህርት ውጤትን በእጅጉ  ያሻሽላሉ። የተሳካ የትምህርት ሂደት እንዲኖር ደግሞ የትምህርት ቤት አካባቢዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ አረንጓዴ፣ ከመንገድ አደጋ ነጻ የሆኑ እና ተማሪዎችን ለማንበብና ለመጫዎት የሚያነሳሱ አስተማሪ የሆኑ መረጃዎች በግድግዳ ላይ የሚታዩባቸው መሆን አለባቸው። እነዚህን መስፈርቶች በትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ እና አካባቢዎች  ማሟላት የተማሪዎቻቸውን ደህንነት  እና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያግዛሉ፡፡

እነዚህ መስፈርቶች ከሕጋዊ አሠራር፣ ከተጠያቂነትና ከጥራት ጋር ተጣጥመው መሄድ እንዳለበት የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ምክትል  ኃላፊ ወ/ሮ ትበይን ባንትይሁን ለበኵር በስልክ አስረድተዋል፡፡  ሆኖም የመማር ማስተማሩን ሂደት የተሻለ እና ውጤታማ ለማድረግ ሕንጻ ከመገንባት ባለፈ ትምህርትን ሊጎዱ እና ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ሊያደናቅፉ  ከሚችሉ ተግባራት ማራቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም በትምህርት ቤቶች አካባቢ ተማሪዎችን ከትምህርታቸው ሊያደናቅፉ እና ሊረብሹ  ከሚችሉ(ሙዚቃ፣ መጠጥ ቤቶች፣ ሻይቤቶች፣ የአልኮል መጠጫ ቤቶች…) እንዲሁም  ለደህንነታቸው ስጋት ከሆኑ ሌሎች ተግባራት በማራቅ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ    የሚያስችሉ ተግባራት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በፊት ከነበረው የተሻሻለ ሁኔታ ቢኖርም ሙሉ በሙሉ ጸድቷል  ማለት አያስችልም ያሉት ምክትል ኃላፊዋ፤ በቀጣይ ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላትን እየተከታተሉ በማጣራት ከክፍለ ከተማው ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እንደ ሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡

“የትምህርት ቤቶች ጥራት በግምት ወይም በዝና የሚለካ ሳይሆን በብሔራዊ የጥራት መስፈርቶች (ስታንዳርዶች) መሠረት በሚደረግ  የቁጥጥር(ኢንስፔክሽን) ምዘና ነው” በማለት  የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሙሉዓለም  አቤ(ዶ/ር) ለአሚኮ ተናግረዋል።  እንደ መምሪያ ኃላፊው ገለጻ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 24፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ 27 መመዘኛ መስፈርቶች ተዘጋጅተውላቸዋል፡፡ መመዘኛዎች   በግብዓት፣ በሂደትና በውጤት  ትምህርት ቤቶች ይመዘናሉ። በዚህም መሠረት ተቋማቱ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 4 ድረስ ይፈረጃሉ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ዓላማው ትምህርት ቤቶችን ለመቅጣት ሳይሆን የጥራት ደረጃቸውን በግልጽ መንገድ በማሳወቅ የማሻሻያ ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ነው። ከ50 በመቶ በታች ውጤት ያስመዘገቡ ተቋማት ደረጃ አንድ፣ ከ50 እስከ 69ነጥብ 99 በመቶ ያገኙት ደረጃ ሁለት፣ ከ70 እስከ 89ነጥብ 99 በመቶ ያገኙት ደረጃ ሦስት እንዲሁም ከ90 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ደረጃ አራት ይባላሉ።

በ2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው የቁጥጥር /የኢንስፔክሽን/ ግምገማ በተለይ አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች በደረጃ ሁለት እና ሦስት  መመደባቸውን ኃላፊው ገልጸዋል። በቅድመ አንደኛ፣ በአንደኛና በመካከለኛ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ መስፈረቱን ሙሉ በሙሉ (ደረጃ)አራት ያስመዘገበ ትምህርት ቤት እስካሁን አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡  በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 100 በመቶ ውጤት ያስመዘገበ አንድ የግል ትምህርት ቤት ወደ ደረጃ 4 ለመሸጋገር የሚያበረታታ አፈጻጸም እያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኃላፊው እንደሚሉት በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል በጥራት ምዘና የተለየ መስፈርት የለም። ሁሉም በተመሳሳይ መመዘኛ(መስፈርት)  ይለካሉ። ነገር ግን የግል ትምህርት ቤቶች ከሚሰበስቡት ገቢ ቢያንስ 50 በመቶውን ለትምህርት ጥራት ማሻሻያ፣ ለመማሪያ ግብዓትና ለማስተማር ሂደት ማሻሻል እንዲያውሉ መመሪያ መኖሩን ገልጸዋል። ይህም ትምህርት ቤቶች ትርፍ ብቻ ሳይሆን የትውልድ ግንባታን እንዲያስቀድሙ የተቀመጠ መስፈርት መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በየዓመቱ የሚነሳው የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪ ጉዳይም በሕግና በመመሪያ መሠረት መመራት እንዳለበት ኃላፊው አስገንዝበዋል። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተግባር ላይ የዋለው መመሪያ ትምህርት ቤቶች ክፍያ ከማስተካከላቸው በፊት ለወላጆች አስቀድመው ማሳወቅ፣ ውይይት ማድረግ እና የወላጆች ውክልናን በውሳኔ ሂደት ማሳተፍ እንደሚጠይቅ አብራርተዋል። ሆኖም አንዳንድ ተቋማት ይህንን አሠራር በሙሉ እንደማይከተሉ ገልጸው፣ በተመሳሳይ ወላጆችም በስብሰባዎች ላይ በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሕገ-ወጥ ምዝገባና የፈቃድ ጉዳይም ሌላው ዋና ችግር መሆኑን  ሙሉ ዓለም አቤ(ዶ/ር) አስረድተዋል። አንዳንድ ተቋማት ከተፈቀደው ጊዜ በፊት ምዝገባ በመጀመር ወይም ፈቃድ ከተሰጣቸው ቦታ ውጭ በመሥራት ሕግን ይጥሳሉ። እንዲህ ያሉ ተቋማት የተማሪ መረጃ ወደ ብሔራዊ መረጃ ቋት እንዳይገባ ሊያደርጉ ስለሚችሉ  ወላጆች ልጆቻቸውን ከማስመዝገባቸው በፊት የትምህርት ቤቱን ሕጋዊ ፈቃድ ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በቅርቡም የቦታና የመሠረተ ልማት ስታንዳርድ ያላሟሉ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ጉድለታቸው እስኪያስተካክሉ ድረስ በጊዜያዊነት እንዲያቆሙ መወሰኑን አስታውቀዋል። ይህ እርምጃ የተወሰደውም ተማሪዎችን ለመቅጣት ወይም የግል ትምህርት ቤቶችን ለመቃወም ሳይሆን የመማሪያ አካባቢው ደህንነቱንና ጥራቱን ለማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል። የትምህርት ጥራት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የትምህርት ቤቶች፣ የወላጆችና የማህበረሰቡ የጋራ ኃላፊነት ነው። ትምህርት ቤቶች ሕግንና ስታንዳርድን ማክበር፣ ወላጆች

በልጆቻቸው ትምህርት ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ መሆን፣ መንግሥትም ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ሲቀጥል ብቻ የትምህርት ጥራት በሚለገው ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል አስገንዝበዋል። “ትምህርት ንግድ ሳይሆን የትውልድ ግንባታ ነው” የሚለው እሳቤም በሁሉም ተቋማት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ ነው ኃላፊው ያስገነዘቡት።

 

መረጃ

ከተማሪዎች ደህንነት እና ከተመቹ የትምህርት አካባቢዎች ጋር የተያያዙ ዋና ዋና መስፈርቶች

  • ደህንነት የተጠበቀ መሆን፡-

ግቢው አጥሮች ያሉት፣ የሰለጠኑ የጥበቃ ሰራተኞች ያሉት እና የትራፊክ ፍሰቱ በተማሪዎች ላይ አደጋ የማያደርስ መሆን አለበት።

  • አረንጓዴ እና ተፈጥሯዊ፡- በዛፎች፣ አበባዎች እና የተለያዩ አትክልቶች የተዋበ መሆን ለአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ እና ለአእምሮ ሰላም ወሳኝ ነው።
  • ንፅሕና የተሞላበት፡- ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ በቂና ንጹህ መፀዳጃ ቤቶች እንዲሁም የእጅ መታጠቢያዎች መኖር አለባቸው።
  • የመጫወቻ እና ስፖርትሜዳ፡- ተማሪዎች አካላዊ ብቃታቸውን የሚያዳብሩባቸው ሰፊና ምቹ ሜዳዎች ሊኖሩት ይገባል።
  • አስተማሪ ገጽታዎች (Visuals)፡- ግድግዳዎች ላይ የሳይንስ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ እና ሌሎች አጠቃላይ እውቀቶችን የሚያስተምሩ ስዕሎችና ጽሑፎች መኖር አለባቸው።

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሐምሌ 20  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here